ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው (ዘፀአት 3፥15)።
የእግዚአብሔር ስም በአማርኛ ሲተረጎም ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር ተብሎ ነው የሚተረጎመው። ነገር ግን የዕብራይስጡ “ያህዌ” የሚለው “እኔ ነኝ” በሚለው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው።
ስለዚህ ሁልጊዜ ያህዌ የሚለውን ቃል ስትሰሙ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ስታነቡ፣ “እኔ ነኝ” በሚለው ቃል ላይ የተመሰረተ፣ እንደ ጴጥሮስ ወይም ዮሐንስ የመጠሪያ ስም እንደሆነ ልታስተውሉ ይገባል። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ፍጹም ያለና የሚኖር መሆኑን ያስታውሰናል።
የያህዌ “እኔ ነኝ” የሚለው ስም በጥቂቱ 10 ነገሮችን ስለእግዚአብሔር ማንነት ይናገራል፦
1. እርሱ ጅማሬ አልነበረውም። ሁሉም ልጅ፣ “እግዚአብሔርን ማን ፈጠረው?” ብሎ ይጠይቃል። አስተዋይ የሆነ ወላጅ ደግሞ “እግዚአብሔርን ማንም አልፈጠረውም። እግዚአብሔር እንዲሁ አለ። ድሮም ነበር፣ ወደፊትም ይኖራል፣ ጅማሬ የለውም” ብሎ ይመልሳል።
2. እግዚአብሔር ፍጻሜ የለውም። ካለመኖር ወደ መኖር ካልመጣ ከመኖር ሊወጣም አይችልም፣ መኖር ማለት ራሱ ነውና።
3. እግዚአብሔር ፍጹሙ እውነታ ነው። ከእርሱ በፊት ምንም አይነት እውነታ (reality) አልነበረም። እርሱ ካልፈቀደውና ካልሰራው በስተቀር ከእርሱ ውጪ እውነታ የለም። ከዘላለም የነበረው እርሱ ብቻ ነው። ምንም ዓለም፣ ምንም ጠፈር አልነበረም። ባዶነት እንኳ አልነበረም። ሁሌም የነበረው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
4. እግዚአብሔር በማንምና በምንም ነገር ላይ በፍጹም ጥገኛ አይደለም። እርሱን ወደ መኖር ያመጣው፣ የደገፈው ወይም ያማከረው ማንም የለም።
5. እግዚአብሔር ያልሆነ ነገር ሁሉ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ይደገፋል። ዓለም በጠቅላላ ሙሉ በሙሉ ጥገኛና ተከታይ ነው እንጂ ቀዳማይ አይደለም። ወደ መኖር የመጣው በእግዚአብሔር ነው፤ በእያንዳንዱ ቅጽበትም መኖር የሚቀጥለው በእግዚአብሔር ውሳኔ ነው።
6. ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጻጸር ዓለም በሙሉ ምንም ነው። ጊዜያዊ እና ጥገኛ የሆነው ዓለም የፍጹሙ እና ጥገኛ ያልሆነው አምላክ ጥላ ነው። በዓለም ውስጥም ቢሆን በጋላክሲዎች ውስጥ የምንገረምበት ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጻጸር ምንም ነው።
7. እግዚአብሔር አይለዋወጥም። እርሱ ትናንት ዛሬም ለዘላለም ያው ነው። እርሱ ሊሻሻል አይችልም። ወደ ምንም ነገር አይለወጥም። እርሱ ራሱ ነው።
8. የእውነት፣ የመልካምነት፣ እንዲሁም የውበት ፍጹም መለኪያው እግዚአብሔር ነው። ትክክል የሆነውን ለማወቅ የሚያየው የሕግ መጽሐፍ የለም። እውነታዎችንም ለመመስረት ማጥኛዎችን ማገላበጥ አያስፈልገውም። ከሁሉ የላቀ እና ውብ የሆነውን ለመወሰን መመሪያ አያስፈልገውም። ትክክል፣ እውነት እና ውብ የሆነውን ነገር የሚወስነው እና የሚለካው እርሱ ራሱ ነው።
9. እግዚአብሔር የወደደውን ያደርጋል። የሚያደርገውም ነገር ሁሉ ሁልጊዜ ትክክል፣ ሁልጊዜ ውብ እና ሁልጊዜ እውነት ነው። ከእርሱ ውጪ የሆነውን እውነታ ሁሉ እርሱ እንደ ፍጹም እውነታ ፈጥሮ ያስተዳድረዋል። ስለዚህ ከራሱ ምክር እና ፈቃድ ውጪ የሚገድበው አንዳች ነገር የለም።
10. እግዚአብሔር በአጽናፈ ዓለሙ ካሉት አካላት ሁሉ እጅግ የከበረው እውነታ እና ማንነት ነው። አጽናፈ ዓለሙን ጨምሮ በሚታየው እና በማይታየው ዓለም ሁሉ ካሉት ከሌሎች እውነታዎች ሁሉ ይልቅ ትኩረታችን፣ አድናቆታችንና ደስታችን ሁሉ የሚገባው ለእርሱ ነው።