ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? (ማቴዎስ 6፥25-26)
ይህን የኢየሱስ የተራራ ስብከት በሦስት ተከታታይ ቀናት እንዳስሳለን። በማቴዎስ 6፥25-34 ውስጥ ኢየሱስ ስለ ምግብ እና ልብስ መጨነቅ ላይ አተኩሮ እየተናገረ ነው። ነገር ግን ከሁሉም ጭንቀት ጋር ይዛመዳል።
የደህንነት ሥርዓቱ ጠንካራ በሆነበት በአሜሪካ ውስጥ እንኳ ስለ ገንዘብ፣ ቤት፣ ምግብ እና ልብስ ያለው ጭንቀት በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ድኅነት ለሕይወት አደጋ በሚያጋልጥበት ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ስናይ ደግሞ ጭንቀቱ የበለጠ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ በቁጥር 30 ላይ እንደተናገረው፣ የምንጨነቀው አባታችን በገባው የጸጋ ተስፋ ላይ እምነታችን ሲጎድል ነው፦ “እናንተ እምነት የጐደላችሁ“ ብሏል።
እነዚህ ቁጥሮች (ቁ. 25-34) ካለማመን ጋር ያለውን መልካሙን ውጊያ ለመዋጋት እና ከጭንቀት ነፃ ለመውጣት ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ቢያንስ ሰባት ተስፋዎች ይይዛሉ። (ለዛሬ ተስፋ 1 እና 2ን እንመለከታለን፤ ከዚያም በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ቀሪዎቹን እናያለን)።
ተስፋ 1፦ “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?” (ማቴዎስ 6፥25)
ሰውነታችን እና ነፍሳችን ከምግብና ከልብስ በላይ ውስብስብ ብሎም አይተኬ ሆነው ሳለ፣ እነዚህን ሁሉ የሰጠን ደግሞ እግዚአብሔር ከሆነ፣ በርግጥ ምግብና ልብስ ለመስጠት ፈቃዱም አቅሙም አለው።
ከዚህም ያለፈ ምንም የከፋ ነገር ቢፈጠር፣ እግዚአብሔር አንድ ቀን ሰውነታችንን ከሞት ያስነሣዋል፤ ሕይወታችንን እና ሰውነታችንን ለዘላለማዊ ኅብረቱ ይጠብቃል።
ተስፋ 2፦ “እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” (ማቴዎስ 6፥26)
እግዚአብሔር እንደ እኛ አርሰው ምግባቸውን ማምረት የማይችሉትን ወፎች መመገብ ከቻለ፣ ከወፎች ለምትበልጡት ለእናንተ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሰጣችኋል። ወፎቹ ማድረግ በማይችሉት መንገድ እግዚአብሔርን በማመን፣ በመታዘዝና በማመስገን እርሱን የማክበር አቅሙ አለን።