ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን? “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? (ማቴዎስ 6፥27-30)
ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ 6፥25-34 ካለማመን ጋር ያለውን መልካሙን ገድል ለመጋደል እና ከጭንቀት ነፃ ለመውጣት፣ ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ቢያንስ ሰባት ተስፋዎች ይጽፍልናል። ትላንት ተስፋ 1 እና 2ን አይተናል። ዛሬ ደግሞ 3 እና 4ን እንመለከታለን።
ተስፋ 3፦ “ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?” (ማቴዎስ 6፥27)
ይህ የተስፋ ቃል ነው፤ ጭንቀት ምንም አይጠቅምም። ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ ከራሳችን ጋር ጠንካራ ንግግር ማድረግ አለብን፦ “ነፍሴ ሆይ! ይህ ምሬት ከንቱ ነው። ምንም ተስፋ የለውም። የራስሽን ቀን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ሰዎችንም ቀን እያበላሸሽ ነው። ተይው። ለእግዚአብሔር ተይው። ሥራሽንም ቀጥይ” ልንላት ይገባል።
ጭንቀት ምንም ፋይዳ የለውም። ይህን የተስፋ ቃል እመኑት። በተስፋው ቃል መሠረት ተመላለሱ።
ተስፋ 4፦ “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ?” (ማቴዎስ 6፥28-30)
ከሜዳ አበባዎች ጋር ስትነጻጸሩ፣ በፊቱ እጅግ የላቀ ቦታ አላችሁ። ምክንያቱም ዘላለማዊ ስለሆናችሁ እና ለዘላለም ከመኖራችሁ የተነሣ እንደ ተወደዱ ልጆች ያለማቋረጥ ምስጋናን ለእርሱ ማቅረብ ስለምትችሉ ነው።
ሆኖም እግዚአብሔር ልዩ የሆነ የመፍጠር አቅም እና የተትረፈረፈ የመንከባከብ ባህርይ ስላለው፣ ለጥቂት ቀናት ብቻ የሚቆዩ አበቦችን እንኳ ያለብሳል። ስለዚህ ያንኑ ጉልበትና የመፍጠር ችሎታ ወስዶ፣ ለዘላለም የሚኖሩ ልጆቹን ለመንከባከብ ይጠቀምበታል። ስለዚህ ይህን የተስፋ ቃል በማመን ጭንቀትን እናስወግድ!