ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና። (ማቴዎስ 6፥31-34)
ባለፉት ሁለት ቀናት፣ በማቴዎስ 6፥25-34 ካለማመን ጋር ያለውን መልካሙን ገድል ለመጋደል እና ከጭንቀት ነፃ ለመውጣት፣ ኢየሱስ የሚያስተምራቸውን ተስፋዎች ስንመለከት ቆይተናል። ዛሬ የመጨረሻዎቹን ሦስት ተስፋዎች እንመለከታለን።
ተስፋ 5፦ “ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” (ማቴዎስ 6፥31-32)።
እግዚአብሔር የእናንተን ፍላጎት የማያውቅ እንዳይመስላችሁ። ሁሉንም ያውቃል። እርሱ “የሰማዩ አባታችሁ” ነው። በግዴለሽነት ከሩቅ አይመለከትም። ስለ እናንተ ያስባል። ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ የሚያስፈልጋችሁን ይሰጣችኋል።
ተስፋ 6፦ “ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ፤ እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” (ማቴዎስ 6፥33)።
ስለ ግል ቁሳዊ ፍላጎቶቻችሁ ከመጨናነቅ ይልቅ፣ በዓለም ላይ ላለው ለእግዚአብሔር ዓላማ ራሳችሁን ከሰጣችሁ፣ ፈቃዱን ለማድረግና ለእርሱ ክብር ለማምጣት የሚያስፈልጋችሁን ነገር ሁሉ ይሰጣችኋል። “እነዚህ ሁሉ ይጨመሩላችኋል” የሚለውን የምረዳው፣ ፈቃዱን ለማድረግ እና እርሱን ለማክበር የሚያስፈልጓችሁን ምግቦች፣ መጠጦች፣ ልብሶች እና ሌሎች ነገሮች ሁሉ ይጨመሩላችኋል በሚል ነው። ይህ ማለት የእርሱ ዓላማ ለእርሱ እንድትሞቱ ሊሆን ይችላል፤ ይህንንም ለክብሩ ማድረግ እንድትችሉ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሰጣችኋል።
ይህ የተስፋ ቃል ከሮሜ 8፥32 የተስፋ ቃል ጋር ተመሳሳይ ነው፦ “ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን?” ቀጥሎም እንዲህ ይላል፦ “ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ ‘ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን’ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” (ሮሜ 8፥35-37)። ረሀብ እና ዕራቍትነት ሊመጡ ይችላሉ። ነገር ግን ከአሸናፊዎች በላይ ለመሆን የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ይኖረናል።
ተስፋ 7፦ “ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና” (ማቴዎስ 6፥34)
እግዚአብሔር በየትኛውም ቀን ከምትችሉት በላይ እንዳትፈተኑ መውጫ መንገድ ያዘጋጅላችኋል (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥13)። ኅይላችሁ በዘመናችሁ ሁሉ እንዲሆን ለእናንተ ይሠራል (ዘዳግም 33፥25)።
እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ ችግር አለው። ነገር ግን ልትሸከሙ ከምትችሉበት ጸጋ በላይ ሊሆን አይችልም። እያንዳንዱ ቀን በየማለዳው አዲስ የሆነ ምሕረት ይኖረዋል፤ ለዚያ ቀን ችግር በቂ የሆነ ምሕረት አለ (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3፥22-23)። የሚያስፈልጋችሁን ጸጋ ሳይሰጣችሁ መልካምን ሥራ ከእናንተ አይጠብቅም (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥8)።