1. ገላጭ ስብከት | Expositional Preaching

ገላጭ ስብከት ምንድን ነው?

ገላጭ ስብከት የአንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ዋና ነጥብ ወስዶ የስብከቱ ዋና ነጥብ ያደርገዋል፤ አያይዞም ዛሬ ባለው ሕይወት ላይ ተግባራዊ ያደርጋል።

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  • ቅዱስ ቃሉ እንደሚለው፣ እግዚአብሔር ሊያደርግ የፈለገውን ነገር የሚፈጽመው በቃሉ (በንግግሩ) ነው (ዘፍጥረት 1፥3፣ ኢሳይያስ 55፥10-11፣ የሐዋሪያት ሥራ 12፥21)። ይህም ማለት ሰባኪያን ስብከታቸው በእግዚአብሔር ኃይል የተሞላ እንዲሆን ከፈለጉ፣ እግዚአብሔር የተናገረውን መስበክ ግድ ይላቸዋል።
  • መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የመሰሉ ብዙ ስብከቶችን እና ትምህርቶችን ለአብነት ይዟል – የሌዋውያን ካህናት ሕግን አስተምረዋል (ዘዳግም 33፥10)፤ ዕዝራ እና ሌዋውያኑ ከሕግ መጽሐፍት እያነበቡ ፍችውን ሰጥተዋል (ነህምያ 8፥8)፤ ጴጥሮስ እና ሐዋርያቱም መጽሐፍን እያብራሩ ሰሚዎቻቸውን በንስሓ እና በእምነት ምላሽ እንዲሰጡ አሳስቧል (የሐዋሪያት ሥራ 2፥14-41፣ 13፥16-47)።
  • በሌላ በኩል፣ እግዚአብሔር “ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ” የሚናገሩትን ይረግማቸዋል።

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

ገላጭ ስብከት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት የእግዚአብሔር ሕዝብን ሊገሥጽ፣ ሊለውጥ፣ ሊያንጽ እና ሊቀድስ የሚችለው የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ነው (ዕብራውያን 4፥12፣ 1ኛ ጴጥሮስ 1፥23፣ 1ኛ ተሰሎንቄ 2፥13፣ ዮሐንስ 17፥17)። የሚሰበከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ዋና መልእክት የስብከቱ ማዕከል ሲሆን፣ ቤተ ክርስቲያኗን የሚዘውረው የሰባኪው አጀንዳ ሳይሆን የእግዚአብሔር አጀንዳ ይሆናል።      

2. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት | Biblical Theology

 

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት ማለት ጤናማ አስተምህሮ ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አብሮ የሚሄድ፣ ስለ እግዚአብሔር ያለ ትክክለኛ እምነት ወይም አስተምህሮ ነው።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  1. መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ ጤናማ አስተምህሮን ያስተምራል።
  2. እንደ የሮሜ እና የኤፌሶን መልእክት፣ አብዛኛው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት በብዙ የአስተምህሮ ዝርዝሮች ከአፍ እስከደገፉ የታጨቁ ናቸው።
  3. የአዲስ ኪዳን ጸሐፊያን ጤናማ አስተምህሮ ለክርስቲያን መንፈሳዊ ጤንነት እና ለቤተ ክርስቲያን ጤንነት አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት አስፈላጊ የሆነበት ምክንያቶች፦

  1. ለወንጌል ስርጭት ወንጌል በራሱ አስተምህሮ ነው። ስለዚህ ጤናማ አስተምህሮ ለወንጌል ስርጭት አስፈላጊ ነው።
  2. ደቀ መዝሙርነት ኢየሱስ በዮሐ. 17፥17 ላይ “ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ ቀድሳቸው” ብሎ ጸልዪል። ክርስቲያኖች እውነትን በመማር እና በመኖር፣ ማለትም በጤናማ አስተምህሮ ያድጋሉ።
  3. አንድነት በአዲስ ኪዳን መሠረት፣ እውነተኛው አንድነት በእውነት ላይ አንድነት ብቻ ነው (1ኛ ዮሐንስ 1፥1 4፣ 2ኛ ዮሐንስ 10፣ 11)
  4. አምልኮ እግዚአብሔርን ማምለክ ማለት ታላቅነቱን ማወጅ (1ኛ ጴጥሮስ 2፥9 10) እና ስለ ማንነቱ ከፍ ከፍ ማድረግ ነው (መዝሙር 29፥2)። እውነተኛ አምልኮ ለጤናማ አስተምህሮ የሚሰጥ ምላሽ ነው።
3. ወንጌል | The Gospel

 

ወንጌል ምንድን ነው?

የምሥራቹ (ወንጌል) ይህ ነው፦

  • አንድና ቅዱስ የሆነው አምላክ እርሱን እንድናውቀው በመልኩ ፈጠረን (ዘፍጥረት 1፥26፣ 28)።
  • እኛ ግን ኅጢአትን በማድረግ ራሳችንን ከእርሱ ለየን (ዘፍጥረት 3፤ ሮሜ 3፥23)።
  • ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ እግዚአብሔር በኢየሱስ ሰው ሆነ፤ ፍጹም ሕይወትን ኖረ፤ ደግሞም በመስቀል ላይ ሞተ። በዚህም ሕጉን ራሱ ፈጽሞ፣ ከኃጢአታቸው ዘወር ብለው በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ የኃጢአታቸውን ቅጣት በራሱ ላይ ወሰደ። (ዮሐንስ 1፥14፤ ዕብራውያን 7፥26፤ ሮሜ 3፥21-26፣ 5፥12-21)።
  • እግዚአብሔር የክርስቶስን መሥዋዕትነት እንደተቀበለ እና በእኛ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳበቃ በማሳየት ከሙታን ተነሣ (ሐዋሪያት 2፥24፣ ሮሜ 4፥25)።
  • እግዚአብሔር አሁን ከኃጢአታችን ንስሓ እንድንገባ እና ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ላይ ብቻ እንድንታመን ይጠራናል (ሐዋሪያት 17፥30፣ ዮሐንስ 1፥12)። ከኃጢአታችን ንስሓ ከገባንና በክርስቶስ ከታመንን ወደ አዲስ ሕይወት ተወልደናል፤ ይህም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም መኖር ነው (ዮሐንስ 3፥16)።
  • ለክርስቶስ ጌትነት የተገዙትን ሁሉ እንደ አንድ አዲስ ሕዝብ አድርጎ ወደ ራሱ እየሰበሰበ ነው (ማቴዎስ 16፥15-19፤ ኤፌሶን 2፥11-19)።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

ሮሜ 1-4 በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት የተሟላ የወንጌል ትንተና አንዱን ይዟል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥1-4 ደግሞ የወንጌልን አጭር ጭብጥ ይዟል።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

  • መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የወንጌል መረዳት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ወንጌል ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ሲሆን፣ ኃጢአተኛ ሰዎች ከቅዱሱ አምላክ ጋር የሚታረቁበት ብቸኛው መንገድ ነው።
  • ይህ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ስብከት ሆነ የማማከር አገልግሎት፣ ደቀ መዝሙርነት ሆነ ዝማሬ፣ የወንጌል ስርጭት ሆነ ተልእኮ እና የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ የሚመነጩት ወንጌልን ከመረዳት ነው።
4. መለወጥ | Conversion

 

መለወጥ ምንድን ነው?

ስለ መለወጥ ያለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረዳት በድነት ውስጥ እግዚአብሔር የሚፈጽመውን እና ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ ይጠቀልላል። በመለወጥ ውስጥ እግዚአብሔር፦

  • ለሙታን ሕይወትን ይሰጣል (ኤፌሶን 2፥5)
  • ለዕውሮችን ያበራላቸዋል (2ኛ ቆሮንጦስ 4፥3-6)
  • በተጨማሪም የእምነት እና የንስሓ ስጦታዎችን ይሰጣል (ፊልጵስዩስ 1፥29፤ ሐዋሪያት 11፥18)።

ሰዎች ደግሞ በመለወጥ ውስጥ፦

  • ከኃጢአታቸው ንስሓ ይገባሉ (ማርቆስ 1፥15፣ የሐዋሪያት ሥራ 3፥19)
  • በኢየሱስ ያምናሉ (ዮሐንስ 3፥16፤ ሮሜ 3፥21-26)።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው የመለወጥ መረዳት እግዚአብሔር ብቻ እንደሚያድን ያስገነዝባል። ሰዎችንም የሚያድናቸው ከኃጢአት ንስሓ በመግባት እና በክርስቶስ በመታመን ለወንጌል መልእክት ምላሽ እንዲሰጡ በማስቻል ነው።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  • ኢየሱስ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡና በእርሱ እንዲያምኑ ጥሪ አድርጓል (ማርቆስ 1፥15)። ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ወደ መንግሥተ ሰማያት ሊገባ እንደማይችል ተናግሯል (ዮሐንስ 3፥1-8)።
  • በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ፣ ሐዋርያቱ ሰዎች ከኃጢአታቸው እንዲመለሱና በክርስቶስ እንዲታመኑ ጥሪ አቅርበዋል (ሐዋሪያት 2፥38፣ 3፥19-20፣ 10፥43፣ 13፥38-39፣ 16፥31፣ 17፥30)።
  • አብዛኛው የአዲስ ኪዳን መልእክት ንሰሐ መግባት እና በክርስቶስ ማመን እንደሚያስፈለገን ሲያትቱ፣ ይህም በእግዚአብሔር ተአምራዊ ሥራ እንደሚፈጽም ይናገራሉ (ሮሜ 6፥1-23፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 2፥14-15፤ 2ኛ ቆሮንጦስ 4፥3-6፤ ኤፌሶን 2፥1-10፣ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥9-10፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥25-26)።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው የመለወጥ መረዳት ለአብያተ ክርስቲያናት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም፦

  1. አብያተ ክርስቲያናት ዓለማውያንን እንዴት መናገር እንዳለባቸው ያብራራል—ክርስቲያን ያልሆኑትን ለኃጢአት ንስሓ እንዲገቡ እና በክርስቶስ እንዲታመኑ ጥሪ ማቅረብ አለባቸው።
  2. አብያተ ክርስቲያናት በወንጌል ሥርጭት ጥረታቸው ሁሉ በእግዚአብሔር መታመን እንዳለባቸው ያሳስባል። አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት (ዳግም ውልደት) መስጠት የሚችለው እርሱ ብቻ ነው።
  3. አብያተ ክርስቲያናት በራሳቸውና በዓለም መካከል ያለውን ግልጽ ልዩነት እንዲጠብቁ ያስተምራል።
  • የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ሕይወት በተለወጠ የሕይወት ፍሬ መታወቅ አለበት።
  • አብያተ ክርስቲያናት ጥምቀትን እና የጌታን እራት መስጠት ያለባቸው የለውጥን ፍሬ ለሚያሳዩት ብቻ ነው።

አብያተ ክርስቲያናት ወንጌልን ሲሰብኩ እና ስለ ክርስቲያናዊው ሕይወት ሲያስተምሩ ሥር ነቀል የሆነውን የሕይወት ለውጥ ያለ መታከት አጽንዖት በመስጠት መሆን አለበት።

5. ወንጌል ስርጭት | Evangelism

 

ወንጌል ስርጭት ምንድን ነው?

የወንጌል ስርጭት አማኝ ላልሆኑ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ስለ ሠራው ሥራ የምሥራች መንገር እና ንስሓ እንዲገቡና እንዲያምኑ ማሳሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መልኩ ወንጌል ለመናገር የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል፦

  1. አስጨናቂ ዜና የሆነውን፣ ማለትም በኃጢአታችን ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ሳታስቀር ሙሉ ወንጌሉን ስበክ።
  2. ሰዎች ከኀጢአታቸው ንሰሓ እንዲገቡ እና በክርስቶስ እንዲታመኑ ጥሪ አቅርብ።
  3. ክርስቶስን ማመን ዋጋ እንደሚያስከፍል፣ ግን ደግሞ ትርፍ እንዳለው ግልጽ አድርገህ ተናገር።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወንጌል ስርጭት ያሉ አስተምህሮዎችን (ማቴዎስ 28፥19-20፤ ሮሜ 10፥14-17፤ 1 ጴጥሮስ 3፥15-16 ) እና የወንጌል ስርጭት ስብከት ምሳሌዎችን (ተመ. ሐዋሪያት ሥራ 2፥14-41፣ 3፥12-26፣ 13:16-49፣ 17፥22-31) ይዟል። ከዚህም ባለፈ መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜውም ስለወንጌል ሲናገር፣ በወንጌል ስርጭት ጊዜ ማስተላለፍ ስላለብን ነገር እያስተማረን ነው (ለምሳሌ፦ ሮሜ ምዕራፍ 1-4 እና 1ኛ ቆሮንጦስ 15፥14)።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

  • ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ የወንጌል ግንዛቤ ሲኖራት፣ ወንጌልን አትሰብክም፤ በአሳሳች ወይም በአማላይ መንገድ ትሰብካለች፤ ወይም ደግሞ ወንጌል ያልሆነን መልእክት ታካፍላለች።
  • በሌላ በኩል፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው የወንጌል ስርጭት ግንዛቤ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን በሰጠው ተልእኮ ውስጥ ያለንን ሚና (ድርሻ) ግልጽ ያደርጋል። ተልዕኮውም ክርስቶስ ስላደረገው ነገር የምሥራችን መስበክ እና እግዚአብሔር ሰዎችን በዚህ ወደ ማመን እንዲያመጣቸው መጸለይ አለብን።
6. የቤተ ክርስቲያን አባልነት | Church Membership

 

የቤተ ክርስቲያን አባልነት ምንድን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የቤተ ክርስቲያን አባልነት፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአካል ለመገኘት፣ ፍቅርን ለማሳየት፣ ለማገልገል እና ለመገዛት የሚወስንበት ነው።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  • በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ እና በዓለም መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት አድርጓል (ተመ. ዘሌዋውያን 13፥46፣ ዘኁልቁ 5፥3፣ ዘዳግም 7፥3)።
  • ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ማለት “በምድር ላይ” ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋር መጣመር እንደሆነ ተናግሯል (ማቴዎስ 16፥16-19፤ 18፥17-19)። በምድር ላይ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን የት ነው የምናያት? አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን።
  • አዲስ ኪዳን በግልጽ አንዳንድ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሆኑ እና አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ውጭ መሆናቸውን ያመላክታል (1ኛ ቆሮንጦስ 5፥12-13)። ይህ ከመደበኛ ማኅበር የበለጠ ነው።
  • የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን አማኞች ያቀፈች በመሆኗ ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ስለሚደርስ ቅጣት ይናገር ነበር (2ኛ ቆሮንጦስ 2፥6)።
  • አዲስ ኪዳን ስለ ቤተ ክርስቲያን አባልነት እውነታ መናገሩ ብቻ ሳይሆን፣ በደርዘን የሚቆጠሩ የ“እርስ በርስ” አንድምታ ያላቸው መልእክቶች የተጻፉት ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ነው፤ ይህም የቤተ ክርስቲያን አባልነት በተግባር ምን መምሰል እንዳለበት ያለንን ግንዛቤ ይቀርጻል።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤተ ክርስቲያን አባልነት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ስለ ራሱ የመሰከረውን ምስክርነት በዓለም ውስጥ ስለምታውጅ ነው። ክብሩን ታሳያለች። ስለዚህም በቤተ ክርስቲያን አባልነት ውስጥ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እግዚአብሔር ቅዱስና ቸር እንደሆነ፣ ወንጌሉም ኃጢአተኞችን ለማዳን እና ለመለወጥ ኃያል መሆኑን በእግዚአብሔር በተለወጠው ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ማየት አለባቸው።

7. የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ | Church Discipline

 

የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ (Church Discipline) ምንድን ነው?

  • ሰፋ ባለ መልኩ ስናየው፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ቤተ ክርስቲያን አባሎቿ ቅድስናን እንዲከተሉ እና ለኃጢአት እጅ እንዳይሰጡ ለመርዳት የምታደርገውን ነገር ሁሉ ያጠቃለለ ነው። ስብከት፣ ትምህርት፣ ጸሎት፣ የአንድነት (የእሁድ) አምልኮ፣ ደቀ መዝሙርነት፣ እና የመጋቢዎች እና የሽማግሌዎች መንፈሳዊ ክትትል ሁሉ የተግሣጽ ዓይነቶች ናቸው።
  • ጠበብ ባለ መልኩ ስናየው ደግሞ፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ማለት በአካሉ ውስጥ ያለን ኅጢአት የማረም ተግባር ነው። ይህም ከአደገኛ ኅጢአት ንሰሓ ባለመግባቱ ምክንያት፣ አንድ ክርስቲያን ነኝ ባይ ሰውን ከአባልነት መሰረዝ እና ከጌታ እራት ማገድን ያጠቃለለ ነው (ማቴዎስ 18፥15-20፣ 1ኛ ቆሮንጦስ 5፥1-13)።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  • አዲስ ኪዳን የእርማት ተግሣጽን (ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት የሚታገዱበት ተግሣጽን ማለት ነው) ማቴዎስ 18፥15-17፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5፥1-13፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 2፥6 እና 2ኛ ተሰሎንቄ 3፥6-15 ባሉት ምንባቦች ላይ ያዛል።
  • አዲስ ኪዳን ስለ የማደግ ተግሣጽ (በቅድስና እና በአንድነት ለማደግ የምናደርገውን ጥረት የሚያግዝ ተግሣጽ) ስፍር ቁጥር በሌላቸው፣ ቅድስናን ስለ መከተል እና እርስ በርሳችን በእምነት ስለ መታነጽ በሚያትቱ ምንባቦች ውስጥ ይናገራል። ለምሳሌ ኤፌሶን 4፥11-32 እና ፊልጵስዩስ 2፥1-18።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

ተግሣጽን፣ ዛፉ ቀጥ ብሎ እንዲያድግ እንደሚረዳው ዘንግ፣ በብስክሌት ላይ እንዳሉ ደጋፊ ጎማዎች፣ ወይም የሙዚቀኛው ማለቂያ እንደ ሌለው የልምምድ ሰዓት እንድጎ ማስብ ይቻላል። ያለ ተግሣጽ፣ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው አናድግም። በተግሣጽ ውስጥ በእግዚአብሔር ጸጋ ታግዘን፣ ሰላም የሞላውን የጽድቅ ፍሬ እናፈራለን (ዕብራውያን 12፥5-11)።

8. ደቀ መዝሙርነት | Discipleship

 

ደቀ መዝሙርነት ምንድን ነው?

ቅዱሳት መጻሕፍት ሕያው ክርስቲያን እድገትን የሚያሳይ ክርስቲያን እንደሆነ ያስተምራል (2ኛ ጴጥሮስ 1፥8-10)። የምናድገው ደግሞ በትምህርት/በትዕዛዛት ብቻ ሳይሆን በመምሰል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል (1ኛ ቆሮንጦስ 4፥16፤ 11፥1)። ስለዚህ አብያተ ክርስቲያናት አባሎቻቸውን በቅድስና እንዲያድጉ እና ሌሎች እንዲያድጉ ማገዝ እንዳለባቸው ሊያስተምሩ ይገባል።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

  • ጴጥሮስ አንባቢዎቹን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እንዲያድጉ አሳስቧቸዋል (2ኛ ጴጥሮስ 3፥18)።
  • ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎች እርስ በርሳቸው በፍቅር በመነጋገር እንዲያድጉ አሳስቧቸዋል (ኤፌሶን 4፥15)።
  • ብዙ የቅዱሳት መጻሕፍት ምንባቦች ጌታን የሚመስሉ መሪዎችን እንድንመስል ያስተምሩናል (ፊልጵስዩስ 4፥9፤ ዕብራውያን 13፥7)።

ዋና ነጥቡ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት፣ ሁሉም ክርስቲያኖች በክርስቶስ ማደግ፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ክርስቲያኖች መምሰል እና ሌሎች ክርስቶስን በመምሰል እንዲያድጉ ማበረታታት አለባቸው።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

  1. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ደቀ መዝሙርነትን እና እድገትን ማስረጽ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ማናችንም ብንሆን የተጠናቀቁ ምርቶች አይደለንም። እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ሁሉም ክርስቲያኖች ከኃጢአት ጋር ይታገላሉ፤ በዚህም ውጊያ ላይ ማንኛውንም እርዳታ እንፈልጋለን።
  2. ቤተ ክርስቲያን ደቀ መዝሙርነትን እና እድገትን ችላ ካለች ወይም የተዛባና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ልምምድ ብታስተምር፤ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ተስፋ ያስቆርጣል፤ ብሎም ሐሰተኛ ክርስቲያኖችን በተሳሳተ መንገዳቸው እንዲቀጥሉ የልብ ልብ ይሰጣቸዋል። በሌላ በኩል፣ ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያን ደቀ መዝሙርነት እና የማደግ ባህልን ካዳበረች፣ አማኞች በቅድስና ለማደግ የሚያደርጉትን ጥረት በእጥፍ ድርብ ያበዛል።
  3. በእምነት እያደገች ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ለዓለም የምትሰጠው ምስክርነት በጥቅሉ ጤናማ ያልሆነ ነው።
9. የቤተ ክርስቲያን አመራር | Church Leadership

 

የቤተ ክርስቲያን አመራር ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን “ሽማግሌዎች” ተብለው በሚጠሩ፣ ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ብዙ (ከአንድ በላይ በሆኑ) ሰዎች መመራት እንዳለበት ያስተምራል።

 

ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?

ጳውሎስ የሽማግሌዎችን መመዘኛዎች በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥1-7 እና ቲቶ 1፥5-9 አስቀምጧል። በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሽማግሌዎች እንዳሉ የሚያሳዩ ጥቅሶች የሐዋርያት ሥራ 14፥23፣ የሐዋርያት ሥራ 20፥17፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥14፣ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥17 እና ያዕቆብ 5፥14 ይገኙበታል።

 

ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?

እግዚአብሔር ሽማግሌዎችን ለቤተ ክርስቲያን እንደስጦታ ሲሰጥ፣ ሽማግሌዎች፦

  • የእግዚአብሔርን በጎች በእግዚአብሔር ቃል እንዲመግቡ (ዮሐንስ 21፥15-17)፣
  • በጎቹን እንዲመሩ (1ጢሞ. 4፥16፣ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥3፣ ዕብራውያን 13፥7)፣
  • በጎቹን ከተናጣቂዎች እንዲጠብቁ (ሐዋሪያት 20፥27-29፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥3-4፤ ቲቶ 1፥9)፣
  • በብዙ ሆነው በመምከር ራሳቸውንም ሆነ በቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ ነው (ምሳሌ 11፥14፤ 24፥6)።

ታዲያ ዋና ማስመር የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የቤተ ክርስቲያን አመራር አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ያለዚያ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እረኛ እንደሌላቸው በጎች ናቸውና።

"Nine Marks of a Healthy Church" ከተሰኘው የማርክ ዴቨር መጽሐፍ ለአንባቢ እንዲመች ተደርጎ የተወሰደ።