እንዴት ሁሉም ነገር እንደ ጉድለት ይቈጠራል?

ስለ ክርስቶስ ሲባል ሁሉን እንደ ጉድለት መቍጠር ምን ማለት ነው? ስለ ክርስቶስ ስንልስ ያለንን ነገር ሁሉ መካድ ምን ማለት ነው?

ጳውሎስ ይህን እንደሚያደርግ ተናግሯል። “… ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እቈጥረዋለሁ፤” (ፊልጵስዩስ 3፥8)።  ከጥቂት ጥቅሶች በኋላም እንዲህ ይላል፤ “ወንድሞች ሆይ፤ የእኔን አርኣያነት በመከተል … ” (ፊልጵስዩስ 3፥17)።

ስለዚህ ይህ ለአማኞች ሁሉ የቀረበ ትእዛዝ ነው።

መሠረታዊ ክርስትና

ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው፤ የላቀ ደቀ መዝሙርነት ሳይሆን መሠረታዊ ክርስትና። ኢየሱስም ይህን አስረግጦ ተናግሯል፤ “ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” (ሉቃስ 14፥33)። ያለንን ሁሉ መተው፣ “ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት ከመቍጠር” ጋር አንድ ነው። ስንለወጥ (at conversion) የሚሆነውም ይህ ነው። ያለ እርሱ ደቀ መዝሙር መሆን አይቻልም። ይህንንም ኢየሱስ በምሳሌ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፥ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የእርሻ ቦታ ገዛ” (ማቴዎስ 13፥44)። የመንግሥቱን ጥሪት ለማግኘት ያለንን ሁሉ በደስታ መሸጥ ስንል፣ ክርስቶስን ለማግኘት ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት መቍጠር የሚለውን ሐሳብ በምሳሌ እየገለጽን ነው።

ስለዚህ ክርስቲያን መሆን ከመንፈሳዊ ሞት መታወር መንቃት እና ኢየሱስን በቂና ሁሉን የሚያረካ ሆኖ ማግኘት ማለት ነው፤ ያን ጊዜም፣ (1) ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እንቈጥራለን፤ (2) ንብረታችንን ሁሉ እንተዋለን፤ በምሳሌው አገላለጽ ደግሞ (3) የክርስቶስን ሀብት ለማግኘት ያለንን ሁሉ እንሸጣለን።

እንዴት ሁሉም ነገር እንደ ጉድለት ይቈጠራል?

በዕለት ተዕለት ተግባራዊ አገላላጽ፣ ይህን ማድረግ ምን ማለት ነው? ቢያንስ እነዚህን አራት ነገሮች ማለት ነው።

  1. ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቍጠር) ማለት፣ ከክርስቶስ እና ከሌላ ከምንም ነገር መምረጥ ቢኖርብን፣ ክርስቶስን እንመርጣለን ማለት ነው።

ይህ ማለት፣ ምንም እንኳ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ይሄ-ወይስ-ያ እያለ የምርጫ ቀውስ ውስጥ ባያስገባንም፣ ምርጫ ማድረግ ካለብን ግን፣ ክርስቶስን ለመምረጥ በልባችን ዝግጁ ሆነን ወስነናል ማለት ነው።

  1.  ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቍጠር) ማለት ወደ ሕይወታችን የሚመጡትን ማንኛውንም ነገሮች፣ ወደ ክርስቶስ ለመቅረብና የበለጠ ክርስቶስን እንድናተርፍ፣ በእርሱም እንድንደሰት እንዲረዱን እንጠቀምባቸዋለን ማለት ነው።

ማለትም፣ ደስ የሚያሰኝን ነገር ሁሉ ክርስቶስን በማመሥገን እንቀበላለን፤ እንዲሁም ሊጎዳንን የሚችልን ነገር ሁሉ በክርስቶስ በኩል በመታገሥ እንቋቋማለን።

  1. ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቍጠር) ማለት፣ የዚህ ዓለም ነገሮች የእኛ ሀብት እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ክርስቶስ ውዱ ሀብታችን መሆኑን በሚያሳይ መንገድ ለመያዝ ከልብ እንጥራለን ማለት ነው።

ማለትም፣ ነገሮችን ሳንጨነቅ እንይዛለን፤ በልግስና እናካፈላለን፤ ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ዋጋ እንሰጣለን። በ1 ቆሮንቶስ 7፥30-31 እንደ ተጻፈው ለመኖር እንተጋለን፦ “[ክርስቲያኖች] ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቁጠሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ።”

  1. ሁሉንም መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቍጠር) ማለት፣ ይህ ዓለም ሊሰጥ የሚችለውን ማንኛውንም ወይም ሁሉንም ነገር ብናጣ ደስታችንን፣ ጥሪታችንን፣ ወይም ሕይወታችንን አናጣም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ የእኛ ጥሪት፣ የእኛ ሐሴትና ሕይወታችን ስለ ሆነ ነው።

ይኸውም በትንንሽ ኪሳራ አናጉረምርም (ፊልጵስዩስ 2፥14)፤ ምናልባት በታላላቅ ኪሳራዎች ልናዝን እንችላለን፤ ነገር ግን ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አንሆንም (1 ተሰሎንቄ 4፥13)።

የተረጋጋ፣ ደስታ የሞላበት፣ ወሳኝ መፍትሔ

በእኔ እምነት ኢየሱስን ፍጹም በቂና ፈጽሞ የሚያረካ ሆኖ ማግኘት ማለት፦ (1) ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት  እንቈጥራለን (ፊልጵስዩስ 3፥8)፣ (2) ንብረታችንን ሁሉ እንተዋለን (ሉቃስ 14፥33) እና፣ (3) የክርስቶስን ሀብት ለማግኘት ያለንን ሁሉ እንሸጣለን ማለት ነው (ማቴዎስ 13፥44)።

ማናችንም ብንሆን ክርስቶስን እንደዚህ ፍጹም በሆነ መንገድ አንወደውም፤ ወይም በዘላቂነት እንዲህ አንኖርም። ነገር ግን እውነተኛ ክርስቲያን፣ የኢየሱስ ተከታይ መሆን ማለት፣ እነዚህ አራት “ከሁሉም ነገር” ጋር የተቆራኙ መንገዶች ለሕይወታችን የተረጋጉ፣ ደስታ የሞላባቸው፣ ወሳኝ መፍትሔዎች እንዲሆኑ እናደርጋለን ማለት ነው።

ከጳውሎስ ጋር፣ “ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እቈጥረዋለሁ” ስንል ይህንን ማለታችን ነው።

ጆን ፓይፐር