ከመዝሙር መጽሐፍ የምንወስደው ትምህርት
ምንባብ:- መዝሙር 73፥25–26 ርዕሰ ጉዳይ፦ ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም
የመዝሙር መጽሐፍ ስሜታችን ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ትእዛዛት ላይ አጽንኦት የሚሰጠው ለምንድን ነው?
እንዲህ ያሉ ክፍሎችን ለምን እናነባለን?
- እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት! መዝሙር 31፥23
- በዓለም የሚኖር ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ይንቀጥቀጥ። መዝሙር 33፥8
- ልበ ቅኖችም ሁሉ ደስ ይበላቸው። መዝሙር 64፥10
- በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ መዝሙር 37፥4
- እናንተ ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ (መዝሙር 97፥12)
- ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ (መዝሙር 32፥11)
- ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤ (መዝሙር 42፥5)
- እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤(መዝሙር 33፥2)
ውደዱት፣ በአድናቆት በመንቀጥቀጥ ቁሙ፣ ተደሰቱ፣ ፈንድቁ፣ ሐሴት አድርጉ፣ ተስፋ አድርጉ፣ አመሥግኑት።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ የግል ምስክርነቶች ባይሆኑም በመዝሙራት ውስጥ ስለ ስሜታችን የተሰጡ ብዙ ምስክርነቶች አሉ፦ “እግዚአብሔርን ወደድሁት” (መዝሙር 116፥1)፤ “በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም” (መዝሙር 73፥25)፤ “ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው!” (መዝሙር 119፥103)።
ከላይ የተጠቀሱት አንዳቸውም የተስፋ ቃል አይደሉም። በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ግን ስለ ስሜቶቻችን የተገቡ ብዙ የተስፋ ቃሎች አሉ፦ “እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና” (መዝሙር 107፥9)፤ “ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል” (መዝሙር 69፥32)፤ “ጻድቃን በቀልን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል” (መዝሙር 58፥10)።
ከላይ የተጠቀሱት አንዳቸውም ጸሎት ባይሆኑም በመዝሙር መጽሐፍ ስለ ስሜቶች የቀረቡ ብዙ ጸሎቶች አሉ፦
“ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፤ ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው” (መዝሙር 51፥8)፤ “የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፤” (መዝሙር 86፥4)፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ እንዲለን፣ ሐሤትም እንድናደርግ፣ ምሕረትህን በማለዳ አጥግበን (መዝሙር 90፥14)።
የሚጠበቅብን ደስታ
ውደዱ፣ በአድናቆት በመንቀጥቀጥ ቁሙ፣ ተደሰቱ፣ ፈንድቁ፣ ሐሴት አድርጉ፣ ተስፋ አድርጉ፣ አመሥግኑ። እነዚህ ምስክርነቶች ወይም የተስፋ ቃሎች ወይም ጸሎቶች አይደሉም፤ ትእዛዛት ናቸው። በቀጥታ ለስሜት፤ በተለይም ደግሞ አዎንታዊ ለሆነ የደስታ ስሜቶች የተሰጡ ትእዛዛት ናቸው። ደግሞም በሰፊው ስላለ አጠቃላይ ደስታ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ስላለ ደስታ ያትታሉ። ሁሉም እግዚአብሔርን ስለ መውደድ፣ በእግዚአብሔር ተደንቆ ስለ መቆም፣ በእግዚአብሔር ስለ መፈንደቅ፣ በእግዚአብሔር ስለ መደሰት፣ በእግዚአብሔር ሐሴት ስለ ማድረግ፣ በእግዚአብሔር ተስፋ ስለ ማድረግና እግዚአብሔርን ስለ ማመሥገን በመናገር እነዚህን ነገሮች ለእግዚአብሔር እንድናደርጋቸው ያዙናል።
የመዝሙር መጽሐፍ ስሜታችን ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ትእዛዛት ላይ አጽንኦት የሚሰጠው ለምንድን ነው? በተለይም ደግሞ በተደጋጋሚ በእግዚአብሔር ደስ እንድንሰኝ ለምን ታዘዝን?
በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ(መዝሙር 32፥11)፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ (መዝሙር 97፥12)፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ(መዝሙር 37፥4)።
ለነፍሳችሁ ስትሉ ሐሴት አድርጉ
ከመዝሙር 1 የምናገኘው አንደኛው መልስ ይህ ነው። እግዚአብሔር በእርሱ ደስ እንድንሰኝ እኛን የሚያዝበት ምክንያቱ፣ በእርሱ ደስ ካልተሰኘን ስለምንጠፋ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ እኛን ከጥፋት ለመጠበቅ ከሁሉ በላይ በእርሱ ደስ እንድንሰኝ ያዘናል። መዝሙር 1 ሁለት ዐይነት ሰዎችን ይገልጻል። በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው ምሥጉን ሰው አለ (መዝሙር 1፥2)።
ይህ ሰው ምላሱን በእግዚአብሔር ቃል ጣፋጭነት ላይ በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን መልካምነት ከብርና ወርቅ ይልቅ የሚያጓጓ፣ ከማር ይልቅ ጣፋጭ መሆኑን የሚያጣጥም ነው (መዝሙር 19፥10)። ነገር ግን በመቀጠል መዝሙር 1፥4፣ “ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም” ይላል። በእግዚአብሔርም ሆነ በቃሉ ደስ አይሰኙም። ስለዚህም፣ “ክፉዎች በፍርድ ፊት …አይቆሙም…የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች” (መዝሙር 1፥5–6)።
ስለዚህ የመዝሙር መጽሐፍ ለምንድን ነው በተደጋጋሚ በእግዚአብሔር ደስ እንዲለንና በእርሱ ሐሴት እንድናደርግ የሚያዘን ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ ከጥፋት ሊታደገን የሚል ነው። እግዚአብሔርን ከሌሎች ሰዎችና ከሌሎች ነገሮች ሁሉ በላይ የከበረ፣ ውድ ፣ ብርቅዬና የሚያረካ ሆኖ ካላገኘነው እንጠፋለን።
ሐዋርያው ጳውሎስ በ 1 ቆሮንቶስ 16፥22 እንዲህ አስቀምጦታል፤ “ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን፡፡” ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ የተናገረውን በራእይ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ጠቅሶልናል፤ “እንግዲህ ለብ ያልህ ብቻ እንጂ ትኵስ ወይም ቀዝቃዛ ስላልሆንህ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው” (ራእይ 3፥16)።
ስለዚህ እግዚአብሔር በመጨረሻው ፍርድ እንዳንጠፋና ከእርሱ ጋር በማይነጥፍ ደስታ እንንኖር ዘንድ፣ በተደጋጋሚ ከሁሉም ነገሮች በላይ በእርሱ ደስ እንዲለን፣ በእርሱ ሐሴት እንድናደርግ፣ እርሱ ፍስሓችንና መፈንደቂያችን እንዲሆን፤ አብልጠን እንድንወደው፣ እንድንመርጠውና ከሁሉ በላይ የሚያረካ መሆኑን እንድንለማመደው ያዘናል።
ከሁሉ በላይ ውድና ክቡር የሆነውን አምልኩ
ይህ ጥያቄውን አንድ ደረጃ ወደ ኋላ መለስ ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። በእግዚአብሔር ባለመደሰታችን ለምን እንጠፋለን? ወደ እግዚአብሔር የመጨረሻ ፍርድ ቀርበን በእርሱ ደስ ባለመሰኘታችን ምክንያት ለምን ወደ ውጪ እንጣላለን? በዚያች ዕለት ኢየሱስ፣ “ከእኔ ይልቅ እናቱን ወይም አባቱን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድድ ለእኔ ሊሆን አይገባም” (ማቴዎስ 10፥37) ብሎ ሲናገር ለምን እንሰማዋለን? ሌላ ሰውን ከእግዚአብሔር በላይ ዋጋ በመስጠት፣ በመውደድ እና ከእግዚአብሔር ይልቅ በሌላ ሰው በመደሰት ምክንያት ለምን ተቀባይነት እናጣለን?
መልሱ ሁለት ክፍል አለው። አንደኛው እግዚአብሔር ከሁሉ የላቀ የከበረ ሀብት መሆኑ ነው። እርሱ ከሁሉ ይልቅ የከበረ፣ ከሁሉ ይልቅ የሚፈለግ፣ ደስ የሚያሰኝና ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የሚያረካ ነው። ቃሉ እንደሚል እርሱ፣ “ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣ እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤ ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤ ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል” (መዝሙር 19፥10)። “አምላክ ሆይ፤ ምሕረትህ እንዴት ክቡር ነው!” (መዝሙር 36፥7)። እግዚአብሔር ወሰን አልባ በሆነ መልኩ ክቡር፣ ውድና የሚያረካ ነው። ይህ ስለ እግዚአብሔር እውነት ነው፤ ማንም በዚህ መንገድ ቢለማመደውም ባይለማመደውም እውነተኛ የማይቀየር ባሕርይው ነው። ይህ የመልሱ የመጀመሪያው ክፍል ነው። እግዚአብሔር ከማንምና ከምንም ነገር ይልቅ ውብ የሆነና የሚተካከለው የሌለ የአጽናፈ ዓለሙ ትልቁና ክቡር ሀብት ነው።
በእግዚአብሔር ደስ ካልተሰኘን የምንጠፋበት ምክንያት ላይ ያለው የመልሱ ሁለተኛ ክፍል ይህ ነው። እግዚአብሔር በርግጥም ከሁሉ በላይ ውድ፣ ክቡር፣ ውብና የሚያረካ እንደ ሆነ ስናምን፣ በማንነቱ የራሱ የሆነው ብርቅዬነቱ በተሞክሯችን የምንለማመደው እውነት ይሆናል። ያ በራሱ ያለው ክብርና ልእቀት፣ በልባችንና በኑሮአችን ውስጥ ተሞክሮአዊ ነጸብራቅ ሆኖ ይገለጣል። እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረውም ለዚህ ነው። ከዚህ የተነሣም ይህ ዘላለማዊና በማንነቱ ውስጥ ያለው ውድነት፣ ውበትና ብርቅዬነት ከሁሉ የላቀ እርካታቸው በሆነላቸው ሰዎች ልቦና እና ኑሮ ተሞክሮአዊ፣ ዉጫዊና በይፋ ገኖ የሚታይ ይሆናል።
ዘላለም የተንጠለጠለበት
በሰው ስሜት ውስጥ የምንወራረደው ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ነው (በሰው ስሜት ውስጥ ዋናው ጉዳይ የእግዚአብሔር ክብር ነው)። በእርሱ ደስ የማንሰኝ ከሆነ አናከብረውም። ከሁሉ ይልቅ በእርሱ ደስ ካልተሰኘን የምንጠፋው ለዚህ ነው። ለዚህ ነው፣ እግዚአብሔር በተደጋጋሚ በእግዚአብሔር እንድንደሰት፣ ፍሥሓችን እንዲሆን በእርሱም ሐሴት እንድናደርግ የሚያዘን። በእግዚአብሔር መደሰት እግዚአብሔርን ያከብረዋል። ፍስሓችን ሲሆን ይከብራል። በእግዚአብሔር ላይ ያለ የኛ ፍሥሓ፣ ደስታና ሐሴት እርሱ የከበረ፣ ብርቅዬ፣ ውድና ውብ መሆኑን ይጠቁማል።
መዝሙረኛው አሳፍ በመዝሙር 73፥25–26
“በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም። ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው።”
ከእነዚህ ቃላት በላይ እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የሚችሉ ቃላት የሉም።
እግዚአብሔርን እንደምትወዱት ዕድል ፈንታችሁ በጥልቀትና በደስታ ከመለማመዳችሁ የተነሣ፣ የተቀሩት ሁሉም መሻቶች በንጽጽር ከንቱ ሆነው ሲቆጠሩ፣ እግዚአብሔር የበለጠ ክቡር ሆኖ እንዲታይ ያደርጉታል።
ደስታን የተሞላ መሥዋዕትነት
ኢየሱስ በአንድ ቁጥር ይህን ምሳሌ ተናግሮ ነበር፦
“መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የዕርሻ ቦታ ገዛ።” ( ማቴዎስ 13፥44)
ይህ ምሳሌ የሀብቱን ውድነት ለማመላከት ያለንን ሁሉ መሸጥን እንደማያስተምር አስተውሉ። ይህ ከዛ ይልቅ ሥር ነቀል ነው። የሀብቱን ውድነት የምንጠቁመው፣ ሀብቱን ለማግኘት ያለንን ሁሉ በደስታ ስንሸጥ መሆኑን ያስተምረናል። ጫና ያለው አስገዳጅና ጨለምተኛ የሆነ ለእግዚአብሔር የሚከፈል መሥዋዕትነት እግዚአብሔርን መጥፎ ያስመስለዋል። የቀደሙት የተሰጡ ክርስቲያኖች በዕብራውያን 10፥34 ላይ ክቡር አድርገው እግዚአብሔርን አሳይተውታል።
“እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ።”
ቤታቸው ሲዘረፍ ምን የዘመሩ ይመስላችኋል? በ16ኛው ክፍለ ዘመን ቢኖሩ ኖሮ “ንብረትንና ዘመድን መተው” እያሉ ማርቲን ሉተር የጻፈውን፣ “አምላካችን ኀያል ምሽግ ነው” የሚለውን መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ምናልባትም ከመዝሙር መጽሐፍ ምዕራፍ 73፥25–26 የዘመሩ ይመስላል፦
“በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለን?
በምድርም ከአንተ ሌላ የምንሻው የለንም።
ሥጋና ልባችን ሊደክሙ ይችላሉ፤
እግዚአብሔር ግን የልባችን ብርታት፣
የዘላለም ዕድል ፈንታችን ነው።
በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው ይህ ዐይነት ደስታ ስቃይን ሲቋቋሙ፣ የእግዚአብሔር ውበትና የእርሱ ክቡርነት በእንባ የተሞላ ፍልቅልቅ ፊታቸው ላይ እንደ ፀሓይ አብርቷል።
ክብር አማራጭ የለውም
በሰው ስሜት ውስጥ የምንደራደረው ከእግዚአብሔር ክብር ጋር ነው (በሰው ስሜት ውስጥ ዋናው ጉዳይ የእግዚአብሔር ክብር ነው)። በእግዚአብሔር ደስ ካልተሰኘን አናከብረውም። ከምንም በላይ በእርሱ ስንረካ፣ ከመቼውም ይልቅ በእኛ ይከብራል። የመዝሙር መጽሐፍ በእግዚአብሔር ደስ እንድንሰኝ የሚያዘን ከዚህ የተነሣ ነው።
እግዚአብሔር ክብሩን በእኛ ውስጥ መፈለጉ አማራጭ እንዳልሆነው ሁሉ በእግዚአብሔር መደሰትን መፈለጋችን ሌላ አማራጭ የለውም። ለፍጥረትና ለቤዝዎት ዐላማ ሁለቱም በዋናነት አስፈላጊ ናቸው። በተዋጁ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ደግሞ ሁለቱም አንድ ላይ ይከሰታሉ። እግዚአብሔር ነፍሳችንን በራሱ ማንነት በማርካት ውስጥ ክብሩን ማጉላት ይፈልጋል።
በዚህ መንገድ የመዝሙር መጽሐፍ መንፈሳዊ ስሜቶች እግዚአብሔርን ለሚያከብር እውነተኛ አምልኮ ያላቸውን አስፈላጊነት ግልጽ ያደርግልናል። አማራጭ የላቸውም ምክንያቱም የእግዚአብሔር ክብር አማራጭ የለውምና።
ተጋድሎ የበዛበት ደስታ
በተጨማሪ የመዝሙር መጽሐፍ ለሕይወትና ለአምልኳችን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ያደርግልናል። ይኸውም የወደቀ፣ ኀጢአተኛ፣ ውስንና በባህል የተገደበ ሰው ሊሰሙት ስለሚችሉ ስሜቶች አጉል የዋህ ከሆነ ተስፈኝነት ይጠብቀናል። ጦርነት የተሞላውን ከባዱን የስሜታችንን ባሕር እንድንሻገር በመምራት ያግዘናል።
ዳግም ስንወለድና የእግዚአብሔር መንፈስ የልቦናችንን ዐይኖች ሲያበራ፣ እግዚአብሔርን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ከምንም ነገር ይልቅ የከበረ፣ ውድና ዋጋ ያለው መሆኑን እናያለን። ይህንን ክብር የምንመለከትበት እይታ ጥርት ብሎ ስለሚቀጥልና ልባችን ምላሽ የሚሰጥ ስለሚሆን፣ ቀሪው ሕይወታችን በሙሉ ብዥታ በሌለው ሁናቴ እግዚአብሔርን እናየዋለን፤ በእርሱም ያለን ደስታ ያልተገደበ ነው ብሎ ማሰብ ግን አጉል የዋህነት እና ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ያ ለማንም አይሆንም። የመዝሙር መጽሐፍ ከሌሎቹ ቅዱሳት መጻሕፍት በበለጠ መንገድ ይህንን እውነታ በምሳሌ ግልጽ ያደርገዋል።
መዝሙረኛው እግዚአብሔርን የሚያይበት እይታ ብዙ ጊዜ ደብዛዛና ብዥታ ያለበት ነው። የልቡ ደስታ ብዙ ጊዜ ተግዳሮት እና ቅራኔ አለበት። ጥቂት ምሳሌዎችን እንይ፦
ልወድቅ ተቃርቤአለሁ፤ ከሥቃዬም ከቶ አልተላቀቅሁም (መዝሙር 38፥17)።
እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣ ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ (መዝሙር 25፥16–17)።
ከቍጣህ የተነሣ ሰውነቴ ጤና አጥቷል፤ ከኀጢአቴም የተነሣ ዐጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። በደሌ ውጦኛል፤ እንደ ከባድ ሸክምም ተጭኖኛል (መዝሙር 38፥3–4)።
ነፍሴ ሆይ፤ ለምን ትተክዢያለሽ? ለምንስ በውስጤ ትታወኪያለሽ? ተስፋሽን በአምላክ ላይ አድርጊ፤ (መዝሙር 42፥5)።
አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤ ከሰራዊታችንም ጋር አትወጣም። ከጠላት ፊት እንድናፈገፍግ አደረግኸን፤ ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን። እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በሕዝቦችም መካከል በተንኸን። ውርደቴ ቀኑን ሙሉ በፊቴ ነው፤ ፊቴም ዕፍረትን ተከናንቧል(መዝሙር 44፥9-11፣ 15)።
ከመቃተቴ የተነሣ ዝያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ (መዝሙር 6፥6–7)።
መዝሙርን የሙጥኝ የምንለው ከዚህ የተነሣ ነው። መዝሙራቱ እኛን ናቸው/ እኛን ይመስላሉ/። ህመም፣ ብቸኝነት፣ ስቃይ፣ ችግር፣ ጸጸት፣ ቀንበር/ ሸክም/፣ ጤና ማጣት፣ ሐዘን፣ ሁከት፣ ኀፍረት፣ መቃተት፣ ማንባት፣ በእንባ የተጥለቀለቁ ሌሊቶች።
ክርስቲያኖችም በመከራ ያልፋሉ
የሆነ ልዝብ የብልጽግና ሰባኪ በተቃውሞ፣ “እነዚህ ሁሉ መከራዎች እና ያ ሁሉ ግጭት የነበሩት ከክርስቶስ በፊትና ከመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ በፊት ነበር። ክርስቲያኖች የሚኖሩት በሌላ መድረክ/ በሌላ ደረጃ ነው” ብሎ ከተናገረ የእኛ ምላሽ፣ “አይደለም። ከግጭትና ከመከራ አናመልጥም” የሚል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስን አስቡ፦
ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ (ሮሜ 9፥2)።
በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ ሐዘንተኞች ስንሆን ሁልጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው (2 ቆሮንቶስ 6፥8–10)
እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን (ሮሜ 8፥23)።
ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ (2 ቆሮንቶስ 4፥16)
ስለዚህ የመዝሙር መጽሐፍ የስሜትን እውነታ እንዳለ አድርጎ የማሳየቱ ምክንያት፣ ከክርስትና ዘመን በፊት ከመሆኑ የተነሣ አይደለም። ከክርስቶስ በፊትም በኋላም በእግዚአብሔር ላይ ያለ ደስታ ተጋድሎ ውስጥ ነው። እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ለደስታ እንጋደላለን።
ሊታለሙ በሚችሉ ተስፋ አስቆራጭ ሞገዶች ሁሉ ውስጥ እንጓዛለን። የመዝሙር መጽሐፍም በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያለው ይህንን ጉዞ እንድንወጣው እኛን ለመርዳት ነው።
ባላችሁ ነገር ሁሉ ተዋጉ
ነገር ግን አትሳሳቱ፤ ይህ ለደስታ የሚደረግ ውጊያ ነው። በእግዚአብሔር ላይ ያለ ደስታ። ሕይወታችን በዚያ ላይ ጥገኛ ነው። ሕይወት በእርሱ ከምንደሰተው በላይ በምንም ነገር ላለመደሰት የምንታገለው ፍልሚያ ነው። መዝሙረኞቹ በተደጋጋሚ የሚያሳዩን ጉዞው እንዴት የተረጋጋ እንደ ሆነ አይደለም። በማይቻሉ የተግዳሮት ሞገዶች ውስጥ እንዴት ተፋልመው እንደ ወጡ ነው። ለደስታቸው እንዴት እንደ ታገሉ ያሳዩናል፦
- ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንደ ተመለከቱ (መዝሙር 34፥5)
- ድንቅ ሥራዎቹን እንዴት እንደሚያስታውሱ (መዝሙር 105፥5)
- ሌሊቱን በሙሉ እንዴት እንደሚያሰላስሉ (መዝሙር 63፥6)
- ኀጢአታቸውን እንዴት እንደተናዘዙና እንዴት ይቅርታን እንደ ተቀበሉ (መዝሙር 130፥3–4)
- ከታላቁ ጉባኤ ጋር ለአምልኮ እንዴት እንደሚሰበሰቡ (መዝሙር 42፥4),
- ወደ እግዚአብሔር እንዴት በሁሉም ዐይነት ፀሎት እንደ ጮኹ (መዝሙር 51፥8–12) እና
- እግዚአብሔርን እንዴት እንደ ጠበቁ (መዝ 130፥5) እንዴት በእርሱ ተስፋ እንዳደረጉ (መዝ 39፥7).
በኢየሱስ ደም መገዛትና በመንፈሱ ዳግም መወለድ ማለት ኢየሱስን ፍጹም እንደሚያረካችሁ የከበረ ዕንቁ አይታችሁታል፣ ተቀብላችሁታል ማለት ነው። የተቀረው ሕይወት ጦርነት ነው። ይቅር ለመባል አንታገልም። ይቅር እንደ ተባለ ሰው እንታገላለን። የመዝሙር መጽሐፍ ያለውን ስልቶች ሁሉ በመጠቀም ለደስታችን እንፋለማለን።
በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም።ሥጋዬና ልቤ ሊደክሙ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን የልቤ ብርታት፣የዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው (መዝ 73፥25–26) ማለት እስክንችል እንታገላለን።
ከዚያም ደግመን ማለት እስክንችል እንጋደላለን። ለመምጣት ቢዘገይም እንኳ ወደ ቀዳዳ የውሃ ማጠራቀሚያና እና ባዶ ጉድጓድ ዘወር ብለን አንከጅልም። እግዚአብሔርን እንጠብቀዋለን። እንጠብቃለን። እናምናለን።