1. ማነው የፈጠረን? ተጠያቂነታችንስ በማን ፊት ነው?
2. ችግራችን ምንድን ነው? በሌላ አነጋገር፣ ችግር ውስጥ ነን ወይ? ከሆንንስ ለምን?
3. ለዚያ ችግር የእግዚአብሔር መፍትሔ ምንድን ነው? ከዚያ ችግር እኛን ለማዳን እግዚአብሔር ምን አደረገ?
4. አሁን፣ በዚህ ሰዓት እና በዚህ ቦታ፣ እኔ ራሴ የዚህ ድነት ተካፋይ መሆን የምችለው እንዴት ነው? ይህንን የምሥራች ከሌላ ሰው አልፎ ለእኔ መልካም ዜና የሚያደርገው ምንድን ነው?
ወንጌል | The Gospel
ወንጌል ምንድን ነው?
የምሥራቹ (ወንጌል) ይህ ነው፦
- አንድና ቅዱስ የሆነው አምላክ እርሱን እንድናውቀው በመልኩ ፈጠረን (ዘፍጥረት 1፥26፣ 28)።
- እኛ ግን ኅጢአትን በማድረግ ራሳችንን ከእርሱ ለየን (ዘፍጥረት 3፤ ሮሜ 3፥23)።
- ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ እግዚአብሔር በኢየሱስ ሰው ሆነ፤ ፍጹም ሕይወትን ኖረ፤ ደግሞም በመስቀል ላይ ሞተ። በዚህም ሕጉን ራሱ ፈጽሞ፣ ከኃጢአታቸው ዘወር ብለው በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ የኃጢአታቸውን ቅጣት በራሱ ላይ ወሰደ። (ዮሐንስ 1፥14፤ ዕብራውያን 7፥26፤ ሮሜ 3፥21-26፣ 5፥12-21)።
- እግዚአብሔር የክርስቶስን መሥዋዕትነት እንደተቀበለ እና በእኛ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳበቃ በማሳየት ከሙታን ተነሣ (ሐዋሪያት 2፥24፣ ሮሜ 4፥25)።
- እግዚአብሔር አሁን ከኃጢአታችን ንስሓ እንድንገባ እና ይቅርታን ለማግኘት በክርስቶስ ላይ ብቻ እንድንታመን ይጠራናል (ሐዋሪያት 17፥30፣ ዮሐንስ 1፥12)። ከኃጢአታችን ንስሓ ከገባንና በክርስቶስ ከታመንን ወደ አዲስ ሕይወት ተወልደናል፤ ይህም ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም መኖር ነው (ዮሐንስ 3፥16)።
- ለክርስቶስ ጌትነት የተገዙትን ሁሉ እንደ አንድ አዲስ ሕዝብ አድርጎ ወደ ራሱ እየሰበሰበ ነው (ማቴዎስ 16፥15-19፤ ኤፌሶን 2፥11-19)።
ይህንን መረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እናገኘዋለን?
ሮሜ 1-4 በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት የተሟላ የወንጌል ትንተና አንዱን ይዟል፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥1-4 ደግሞ የወንጌልን አጭር ጭብጥ ይዟል።
ለምንድን ነው አስፈላጊ የሆነው?
- መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የወንጌል መረዳት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ወንጌል ለሚያምን ሁሉ ለድነት የሚሆን የእግዚአብሔር ኀይል ሲሆን፣ ኃጢአተኛ ሰዎች ከቅዱሱ አምላክ ጋር የሚታረቁበት ብቸኛው መንገድ ነው።
- ይህ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ስብከት ሆነ የማማከር አገልግሎት፣ ደቀ መዝሙርነት ሆነ ዝማሬ፣ የወንጌል ስርጭት ሆነ ተልእኮ እና የመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ የሚመነጩት ወንጌልን ከመረዳት ነው።