“እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣ ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው?” ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። (ሮሜ 11፥35-36)
ስለ ታዛዥነት ስንናገር፣ መልሶ ለመክፈል ያለ ተነሳሽነት አደገኛ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እንደ ተበዳሪ ወይም እንደ ባለእዳ ራሱን ለመግለጥ ይሞክራል። ለምሳሌ ሰዎች፣ “እግዚአብሔር ያደረገልህን ሁሉ ተመልከት። እርሱ ይህን ሁሉ አድርጎልህ፣ አንተ ብዙ ልትሆንለት አይገባም?” ወይም “የሆንከው እና ያለህ ነገር በሙሉ የእግዚአብሔር ነው። በምላሹ ምን አደረግህለት?” ሲሉ እንሰማለን።
እንዲህ ባለ ተነሳሽነት ላይ ቢያንስ ሦስት ችግሮች አሉ።
የመጀመሪያው፣ እግዚአብሔር ላበዛልን ጸጋ ምላሽ የሚሆንን ክፍያ ፈጽሞ ልንከፍል አንችልም። ለመክፈል አንድ እርምጃ እንኳን መሄድ አንችልም። ምክንያቱም ሮሜ 11:35-36 እንዲህ ይለናል፦ “’እግዚአብሔር መልሶ እንዲሰጠው፣ ለእግዚአብሔር ያበደረ ከቶ ማን ነው?’ መልሱ፦ ማንም ነው! ሁሉም ከእርሱ፣ በእርሱ፣ ለእርሱ ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን።” ጥረታችን እንኳ ሳይቀር፣ ሁሉ የእርሱ ነውና፣ አንዳች ልንከፍለው አንችልም።
ሁለተኛው ምክንያት፣ እግዚአብሔር ላበዛልን ጸጋ ምላሽ የሚሆንን ክፍያ መክፈል ብንችል እንኳ፣ ይህ ክፍያ በጸጋ የሆነ ግንኙነታችንን ወደ ንግድ ይቀይረዋል። መልሰን ልንከፍለው ከቻልን፣ ጸጋ አልነበረም ማለት ነው። ጸጋን ጸጋ የሚያደርገው ነጻ መሆኑ ነው። የሆነ ሰው ለእናንተ ካለው ፍቅር የተነሳ እራት ጋብዟችሁ ሂሳቡን ሲከፍል፣ “በቀጣይ ሳምንት እኔም እጋብዝህና ውለታህን እመልሳለሁ” ካላችሁት፣ የዛን ሰው ፍቅር በመሻር ግንኙነታችሁን ወደ ንግድ ቀየራችሁት ማለት አይደል? በተመሳሳይ መልኩ፣ እግዚአብሔርም ጸጋው ሲሻርበት ደስ አይለውም። ጸጋው እንዲከብር እና እንዲመሰገን ይፈልጋል (ኤፌሶን 1:6፤ 12፤ 14)።
ሶስተኛው ምክንያት፣ የመታዘዛችን ዋነኛ ምክንያት መልሶ ከመክፈል ስሜት የመነጨ ልብ ከሆነ፣ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ (future grace) ላይ ሊኖረን የሚገባውን እምነት ያስረሳናል። ብድር መላሽ የሆነ ልብ፣ ወደ ኋላ ዞሮ በመመልከት ስለተደረገለት ነገር ያመሰግናል። እምነት ግን የተገባውን የተስፋ ቃል ይጠባበቃል — የሚፈጸመው ከአምስት ደቂቃ በኋላም ይሁን ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ — እምነት ተስፋው ሙሉ ነው። “እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም ርግጠኛ የምንሆንበት … ነው” ይለናል (ዕብራውያን 11:1)።
ይህ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ ያለ እምነት ከልብ ለሆነ መታዘዝ ትክክለኛ ተነሳሽነት ነው። መታዘዝ እግዚአብሔር ላደረገልን ነገር መልሶ መክፈልን፣ ወይም ጸጋን ወደ ንግድ መቀየርን ፈጽሞ አያካትትም። መታዘዝ የሚመጣው፣ በማያልቀው የእግዚአብሔር ጸጋ ላይ በመታመን ነው። ይህም ወሰን የሌለውን ፍቅሩን፣ ምሕረቱን እና ኀይሉን አጉልቶ ያሳያል። እምነት ወደ ተስፋው በመመልከት፣ “በምትሄድበት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ከአንተ ጋር ነውና አይዞህ” የሚለውን ቃል ሰምቶ፣ በታዛዥነት ለመውረስ ይጓዛል (ኢያሱ 1:9)።