“አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል፤ ሆኖም እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። ሊጠቅሟችሁ ወይም ሊያድኗችሁ የማይችሉ ምናምንቴ ነገሮችን አትከተሉ፤ ከንቱ ናቸውና። እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም።” (1 ሳሙኤል 12፥20–22)
እስራኤላውያን በፍርሃት ተውጠው እና እንደሌሎች አሕዛብ እንዲሆኑ ንጉሥ የሚሆንን ሰው እንዲሰጣቸው ሳሙኤል በመጠየቃቸው ንስሐ በገቡ ጊዜ፣ መልካሙ የምሥራች ወደ እነርሱ መጣ፦ “አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል።” እንዴት ተገላቢጦሽ እንደሚመስል ይታያችኋል — የሚያስደንቅ ተገላቢጦሽ? “ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋልና ፍሩ” እንዲል ልትጠብቁ ትችላላችሁ። ከእግዚአብሔር ሌላ፣ ሌላ ንጉስን በመጠየቅ ታላቅ የሆነን ክፋት ሰርታችኋልና፣ ለመፍራት በቂ ምክንያት አላችሁ። ነገር ግን ሳሙኤል ያላቸው ያንን አይደለም። “አትፍሩ፤ ይህን ሁሉ ክፋት አድርጋችኋል።”
ከዚያም ይቀጥልና፣ “ሆኖም እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። ሊጠቅሟችሁ ወይም ሊያድኗችሁ የማይችሉ ምናምንቴ ነገሮችን አትከተሉ፤ ከንቱ ናቸውና” ይላል።
ወንጌል ይህ ነው፦ ምንም እንኳን ታላቅ ኃጢአትን ብትሠሩና ጌታን እጅግ ብታዋርዱትም፣ ምንም እንኳን ለንጉሥ መለመናችሁ ኅጢያት ቢሆንም ደግሞም አሁን ላይ ንጉሥ ቢኖራችሁም፣ ምንም እንኳን ኀጢአቱን ወይም የሚመጣውን የኀጢአቱን አሳዛኝ መዘዝ መቀልበስ ባይቻልም፣ የይቅርታ ተስፋ ግን አለ። ምሕረት አለ።
አትፍሩ!
ከዚያም በ1ኛ ሳሙኤል 12፥22 ላይ ያለው ታላቁ የወንጌል መሠረት — ማስረጃ እና መገኛ — ይመጣል። ይህን ሁሉ ክፉ ነገር ብታደርጉም ለምንድን ነው መፍራት የማያስፈልጋችሁ? “እግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ስለ ወደደ፣ ስለ ታላቅ ስሙ ሲል እግዚአብሔር ሕዝቡን አይተውም።”
የወንጌል መሠረት እግዚአብሔር ለራሱ ስም ያለው ቁርጠኝነት ነው። ሰማችሁኝ? ኃጢአት ብትሠሩም አትፍሩ፤ “እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሲል ሕዝቡን አይጥልም።” ይህ በእናንተ ላይ ሁለት ተጽእኖዎችን ሊያሳድር ይገባል፦ ልብን የሚሰብር ትህትና እና በአውራ ጣት የሚያስቆም ደስታ። ትሁት ልትሆኑ ይገባል፤ ምክንያቱም የመዳናችሁ መሠረት የእናንተ ዋጋ አይደለም። ደግሞም እጅግ ደስተኛ ልትሆኑ ይገባል፤ ምክንያቱም ድነታችሁ እግዚአብሔር ለስሙ ባለው ታማኝነት ላይ የተረጋገጠ ስለሆነ። ከዚህ የበለጠ እርግጥ ሊሆን አይችልም።