መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች!። (መዝሙር 31፥19)
በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ የሚሰጠንን ጸጋ መለማመድ የሚወሰነው እግዚአብሔርን መሸሸጊያ ማድረጋችን እና አለማድረጋችን ላይ ነው። በእርግጥ በእርሱ ከለላ ስር እንታመናለን? ወይስ የእርሱን እንክብካቤ በመጠራጠር ሌሎች መጠለያዎች ስር ለመሸሸግ እንሮጣለን?
እግዚአብሔርን መጠጊያ ላደረጉ አማኞች፣ ይህ ጸጋ እጅግ የከበሩ ብዙ ተስፋዎችን ይሰጠናል። አንዳንዶቹን እንመልከት፦
- እርሱንም መጠጊያ ያደረገ አይፈረድበትም። (መዝሙር 34፥22)
- ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው። (2ኛ ሳሙኤል 22፥31)
- እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው። (መዝሙር 2፥12)
- እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው። ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል። (ናሆም 1፥7)
እግዚአብሔርን መጠጊያ ስላደረግን እና በክንፎቹ ጥላ ስር ስለተሸሸግን የምናገኘው ወሮታ ወይም የሚሰጠን ክብር የለም። ደካሞች ስለሆንን እና ከለላ ስለሚያስፈልገን መደበቃችን ራሳችንን መቻላችንን የሚያሳይና የሚያስመሰግነን ሥራ አይደለም። ይህ የሚያሳየው አቅመ ቢስነታችንን መቀበላችንን ሲሆን፣ የተሸሸግንበት ቦታ ደግሞ የመማጸኛ እና የማምለጫ ምሽግ እንደሆነ ነው።
በተጠቀሱት ተስፋዎች ሁሉ ውስጥ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ በረከትን ለመቀበል ከእኛ የሚጠበቀው እርሱን መጠጊያ ማድረግ ብቻ ነው። ይህም ደግሞ በጭራሽ ሊያስመሰግነን የሚገባ የሥራችን ውጤት አይደለም። ይልቁንም እርዳታ መፈለግን፣ ደካማነትን፣ መቸገርን እና እምነትን የሚያሳይ ነው።
አማራጭ ያጣ ሰው አንዳች ነገር ይገባኛል፣ ይሰጠኝ አይልም። ነገር ግን ምሕረትን ለማግኘት ይለምናል፣ ጸጋንም ለመቀበል በተሰበረ ልብ ይማጸናል።