እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለእርሱ የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶናል። (ሐዋርያት ሥራ 15፥14)
የእግዚአብሔር ስምና ዝና የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮን በማነቃቃት እና በማቀጣጠል ረገድ ያለውን ማዕከላዊነት ልናሳንሰው አንችልም።
በሐዋርያት ሥራ 10 ላይ፣ እግዚአብሔር የጴጥሮስን ዓለም ሲገለባብጠው እናገኛለን። ንፁህ ያልሆኑ እንስሳትን እንዲበላ ራእይን በማሳየት፣ ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለአሕዛብ ጭምር ወንጌልን እንዲሰብክ ሲያዝዘው፣ ጴጥሮስ ወደ እየሩሳሌም በመመለስ፣ ይህን ሁሉ እግዚአብሔር ለስሙ ካለው ቅንዓት የተነሳ እንዳደረገው ለሐዋርያቱ ይነግራቸዋል። ይህንንም ያዕቆብ ጠቅለል አድርጎ ይስቀምጠዋል፦ “ወንድሞች ሆይ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለእርሱ [ለስሙ] የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶናል” (ሐዋርያት ሥራ 15፥13-14)።
ጴጥሮስ “የእግዚአብሔር ዓላማ ለስሙ የተጠሩ ሕዝቦችን መሰብሰብ ነው” ማለቱ አይገርምም። ምክንያቱም ከዓመታት በፊት ኢየሱስ ጴጥሮስን የማይረሳ ትምህርት አስተምሮታል።
ኢየሱስን ለመከተል ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረውን የዚያን ሀብታም ሰው ታሪክ አስታወሳችሁት? ጴጥሮስ ለኢየሱስ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እኛ [ከዚህ ሃብታም ሰውዬ ተሽለን] ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” (ማቴዎስ 19፥27)። ኢየሱስም ጴጥሮስን በመገሰጽ፣ “ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል” በማለት ለክርስቶስ የተኖረ ሕይወት እና የተሞተ ሞት ትርፍ አልባ መሥዋዕትነት እንዳለሆነ አስረድቶታል (ማቴዎስ 19፥29)።
እውነቱ በግልፅ ተቀምጧል፦ ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር፣ በፍጹም ደስታ ለስሙ የተጠሩ ህዝቦችን ከነገድ፣ ከቋንቋና ከወገን ሁሉ እየሰበሰበ ነው (ራእይ 5፥9፤ 7፥9)። ስሙ በዓለም ሁሉ እንዲታወቅ ከልቡ ይፈልጋል።
ስለዚህ፣ እኛም ፍላጎቶቻችንን ከእርሱ ፍላጎት ጋር ስናጣምር፣ ስለ ስሙም ብለን ምድራዊ ምቾታችንን በመተው ዓለም አቀፋዊ ለሆነው ተልዕኮ ስንገዛ፣ ለስሙ ያለው ትጋት ከፊታችን እንደ ሰንደቅ ይውለበለባል። ድካማችን ሁሉ ስለ ስሙ ስለሆነ በመከራ ውስጥ ብናልፍም፣ ፈፅሞ ልንሸነፍ አንችልም። (ሐዋርያት ሥራ 14፥22፤ ሮሜ 8፥35-39)