ወንጌልን የሚያብራሩ ስድስት ነጥቦች | መጋቢት 19

“እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ…” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥18)

ወንጌሉን ለራሳችሁ እንድትረዱ እና ለሌሎች እንድታስረዱ የሚረዳ አጭር ማብራሪያ እነሆ!

1) እግዚአብሔር ለክብሩ ፈጠረን

“ሰሜንን፣ ‘አምጣ’፣ ደቡብንም፣ ‘ልቀቅ’ እላለሁ፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ” (ኢሳይያስ 43፥6-7)። እግዚአብሔር በአምሳያው የፈጠረን የእርሱን ውብ ባሕርይ እንድናንጸባርቅ ነው።

2) ስለዚህ ሁሉም ሰው ለእግዚአብሔር ክብር መኖር አለበት

“እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31)። ለእግዚአብሔር ክብር የመኖሪያው መንገድ እርሱን መውደድ (ማቴዎስ 22፥37)፣ በእርሱ መታመን (ሮሜ 4፥20)፣ እርሱን ማመስገን (መዝሙር 50፥23)፣ ለእርሱ መታዘዝ (ማቴዎስ 5፥16) እና ከምንም በላይ እርሱን ወደር የለሽ ማድረግ ናቸው (ፊልጵስዩስ 3፥8ማቴዎስ 10፥37)። እነዚህን ስናደርግ የእግዚአብሔርን ክብር እናንጸባርቃለን።

3) ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ፣ ሁላችንም ኅአትን ሠርተናል፤ ከእግዚአብሔርም ክብር ጎድለናል

“ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፥23)። “እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። … የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረት መልክ መስለው ለወጡ” (ሮሜ 1፥21-23)። ሁላችንም እግዚአብሔርን እንደሚገባው አልወደድነውም፤ አላመንነውም፤ አላመሰገንነውም።

4) ስለዚህ ሁላችንም ዘላለማዊ ቅጣት ይገባናል

“የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የዘላለም ሕይወት ነው” (ሮሜ 6፥23)። ጌታ ኢየሱስን የማይታዘዙ “እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ” (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥9)። “እነዚህም ወደ ዘላለም ፍርድ፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ” (ማቴዎስ 25፥46)።

5) ነገር ግን በታላቅ ምህረቱ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለኅጢአተኞች የዘላለም ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ላከው

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐንስ 3፥16)፤ “ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል” (ገላትያ 3፥13)፤ “እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥18)።

6) የዘላለም ሕይወት ክርስቶስ አምላክ እና አዳኝ እንደሆነ ለሚያምኑ ሁሉ ነፃ ስጦታ ነው

“በጌታ በኢየሱስ እመን፤ አንተም ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” (ሐዋርያት ሥራ 16፥31)፤ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ” (ሮሜ 10፥9)። “በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም” (ኤፌሶን 2፥8-9)። “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው“ (ገላትያ 2፥20)። “ከዚህም በላይ ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለእርሱ ስል ሁሉን አጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጒድፍ እቈጥራለሁ” (ፊልጵስዩስ 3፥8)።