ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው (ዕብራውያን 2፥14-15)።
ክርስቶስ ከሞት ፍርሃት ነጻ አውጥቶን፣ ንብረት ዘመዶቻችንን ከዚያም አልፎ ሕይወታችንን እንኳ ብናጣ ያለ ምሬት መኖር እንድንችል የሚያደርገን እንዴት ነው? እስቲ ይህንን ጥቅስ እየከፋፈልን እንመልከት፦
ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ …
“ልጆቹ” የሚለው ቃል የተወሰደው ቀደም ካለው ቁጥር ሲሆን፣ የሚያመለክተው የመሲሑ የክርስቶስን መንፈሳዊ ልጆች ነው። እነዚህም ደግሞ “የእግዚአብሔር ልጆች” ናቸው። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር ክርስቶስን በመላኩ፣ “የልጆቹን” ድነት ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶታል። “ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ …”
እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ [በሥጋና በደም]ተካፈለ …
በሥጋ ከመገለጡ በፊት በዘላለማዊ ቃልነት ሲኖር የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ (ዮሐንስ 1፥1)፣ ሥጋና ደምን በመካፈል አምላክነቱ ላይ ሰውነትን ጨመረ። መለኮትነቱን ሳይለቅ ፍጹም ሰው ሆነ።
በሞት …
ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመጣበት ምክንያት ለመሞት ነው። ሰው ሆኖ ከመገለጡ በፊት በነበረው መለኮታዊ ባህርይ ለኃጢአተኞች መሞት አይችልም። ነገር ግን ሥጋን ከለበሰ በኋላ ይችላል። ዓላማው መሞት ስለነበር፣ ሟች የሆነውን ሰውን ሆኖ መወለድ ነበረበት።
ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው …
ክርስቶስ በሞቱ ዲያቢሎስን አሸነፈው። እንዴት? ኃጢአታችንን ሁሉ በመሸፈን (ዕብራውያን 10፥12)። ይህ ማለት ሰይጣን እኛን በእግዚአብሔር ፊት የሚከስበት ምንም አይነት መሠረት የለውም ማለት ነው። “እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው” (ሮሜ 8፥33)። በምን መሠረት ነው የሚያጸድቀው? በኢየሱስ ደም አማካይነት ነው (ዕብራውያን 9፥14፣ ሮሜ 5፥9)።
ሰይጣን እኛን የሚያጠቃበት የመጨረሻ መሣሪያው የራሳችን ኃጢአት ነው። የኢየሱስ ሞት ይህንን አስወገደ ማለት የሰይጣን ዋና መሳሪያው ከእጁ ተነጠቀ ማለት ነው። ይህም ማለት ኀይሉን ሁሉ አጥቷል። ይሄ ሁሉ ታዲያ ለምን ሆነ?
በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።
ስለዚህ ከሞት ፍርሃት ነጻ ወጥተናል። እግዚአብሔር አጽድቆናል። ከፊታችን ያለው ያልተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው። ይህንንም አዋጅ ሰይጣን ሊቀለብሰው አይችልም። የመጨረሻው ደኅንነታችን የተረጋገጠው ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እንዲሆን እግዚአብሔር ወስኗል። የመጨረሻው ደስታ አሁን ያለውን ባርነት እና ፍርሃት እንዲያስወግድ እግዚአብሔር ይፈልጋል።