ጠላቶቹ ነበርን | ሰኔ 8

ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በአሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን . . . በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። (ቈላስይስ 1፥21–22)

በዓለም ላይ ካሉ ዜናዎች ሁሉ እጅግ ምርጥ የሆነው ዜና፣ ከእግዚአብሔር መራቃችን አብቅቶ፣ የዓለም ሁሉ ፈራጅ ከሆነው አምላክ ጋር መታረቃችን ነው። ከእንግዲህ እግዚአብሔር የእኛ ወገን እንጂ ጠላታችን አይደለም። ሁሉን ቻይ በሆነው ፍቅሩ ለእኛ ወግኗል። ይህ ደግሞ ነፍሳችንን እንደብረት ያጠነክራታል። በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ እጅግ ጠንካራ የሆነው አካል ከጎናችሁ በሚሆንበት ጊዜ፣ ሕይወታችሁ በፍጹም ነፃነት እና ድፍረት የተሞላ ይሆናል። 

ነገር ግን በቆላስይስ 1፥21 ላይ ያለውን ቃል ላልተቀበሉ የጳውሎስ የድነት መልእክት መልካም የምስራች አይደለም። እናንተ “ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በአሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ” ይላቸዋል።

“የእግዚአብሔር ጸጋ አግዞኝ ነው እንጂ፣ በአሳቤ ለእግዚአብሔር ጠላት ነኝ” የሚሉ ምን ያህል ሰዎችን ታውቃላችሁ? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች “እግዚአብሔርን እጠላዋለሁ” ብለው አይናገሩም። ታዲያ፣ ጳውሎስ በክርስቶስ ደም ከመታረቃቸሁ በፊት ለእግዚአብሔር “በአሳባችሁም ጠላቶች” ናችሁ ሲል ምን ማለቱ ነው?

ሊሆን የሚችለው፣ በሰዎች ልብ ውስጥ የእውነተኛው አምላክ ጥላቻ በእርግጥ አለ። ነገር ግን፣ ስለ እውነተኛው አምላክ ለማሰብ ለአእምሯቸው አይፈቅዱለትም። በምናባቸው የሚስሉት እግዚአብሔር ትክክለኛው እግዚአብሔር እንዲሆንላቸው ይፈልጋሉ፤ የራሳቸውንም አምላክ መሳላቸው ከእርሱ ጋር የምር ሊጋጩ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በጣም ይቀንስላቸዋል።

ነገር ግን መከራን፣ በሽታን እና የተለያዩ አደጋዎችን ጨምሮ፣ በሁሉ ነገር ላይ ሉዓላዊ ስለሆነው እውነተኛ አምላክ ካነሳን፣ እኛ ሁላችን ጠላቶቹ እንደነበርን ጳውሎስ ይነግረናል። በውስጥ ልባችን ፍጹምነቱን፣ ቅድስናውን፣ ኃይሉን እና ሥልጣኑን እንጠላው ነበር።

ታዲያ በክርስቶስ የመስቀል ላይ ስራ አምነን የዳንን ሁላችን፣ ክፉ ልባችንን እግዚአብሔር በጸጋው አሸንፎ እንጠላው የነበረውን አምላክ እንድንወድድ አድርጎናል። ይህንንም ጸጋ ላገኘንበት አስደናቂ ለሆነው የክርስቶስ ሞት እውነታ ባለዕዳዎች ነን።

አሁንም ቢሆን ብዙዎች ለእግዚአብሔር ጠላት አለመሆንን እየተማሩ ነው። የእግዚአብሔር ትዕግስት የተትረፈረፈ መሆኑ እጅግ መልካም ዜና ነው።