ለእግዚአብሔር ሁሉ ይቻላል | ጳጉሜ 4

“ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ” (ዮሐንስ 10፥16)።

እግዚአብሔር ከዓለም ሕዝቦች ሁሉ ውስጥ የራሱ የሆኑ ሰዎች አሉት። በወንጌሉም አማካይነት በኀይሉ ይጠራቸዋል። አቤት ብለው ይመጣሉ፣ ያምኑታልም! ወንጌል ባልደረሰባቸው ቦታዎች ያለውን ተስፋ መቁረጥ ለማሸነፍ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለውን ዕምቅ ኀይል መረዳት ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ፒተር ካሜሮን ስኮት የተባለው የታዋቂ ሚስዮናዊ ታሪክ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። እ.ኤ.አ. በ1867 በግላስኮው ተወለደ። አፍሪካ ኢንላንድ ሚሽን የተሰኘ ግዙፍ የሚስዮናዊያን ሚኒስትሪ መስራች ነው። ይሁን እንጂ በአፍሪካ የነበረው ጅማሬ ጥሩ አልነበረም።

ወደ አፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገው ጉዞ በከባድ የወባ በሽታ ምክንያት ተቋረጠ እና ወደ አገሩ ተመለሰ። ከተሻለው በኋላ ለመመለስ ቆርጦ ነበር። ጆን ከተባለው ወንድሙ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በደስታ ቢመለስም ብዙም ሳይቆይ ጆን በከባድ ትኩሳት ታሞ ሞተ።

ፒተር ብቻውን ሆኖ ወንድሙን አፍሪካ ውስጥ ቀበረ። በታላቅ ሐዘን ውስጥ ሆኖም ወንጌልን ለመስበክ በድጋሚ ወሰነ። ነገር ግን አሁንም ጤናው ታወከና ወደ ኢንግሊዝ ለመመለስ ተገደደ።

ያንን አስቸጋሪ እና አሳዛኝ ጊዜ እንዴት መሻገር ይችላል? ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጥቷል፤ ነገር ግን ወደ አፍሪካ የሚመለስበትን አቅም ከየት ያግኝ? ይህ በእርግጥም በሰው ዘንድ የማይቻል ነበር!

ለጊዜው የሚያስፈልገውን ብርታት የዴቪድ ሊቪንግስተን መቃብር በሚገኝበት በዌስትሚኒስትር አቢ ቤተ ክርስቲያን አገኘው። ስኮት ቀስ ብሎ በመግባት በመቃብሩ ፊት ለመጸለይ ሲንበረከክ፣ በላዩ ላይ የተቀረጸውን ጥቅስ አነበበ። እንዲህ ይላል፦

“ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ።

ስኮት በአዲስ ተስፋ ተሞልቶ ከተንበረከከበት ተነሳ፤ ወደ አፍሪካም ተመለሰ። እናም ዛሬ እርሱ የመሠረተው የሚስዮናውያን ድርጅት በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ብርቱ የወንጌል ኀይል ሆኗል።

የእግዚአብሔርን ጸጋ መለማመድ እና ለሌሎች ማካፈል እጅግ የሚያስደስታችሁ ከሆነ መልካም ዜና እነሆ፤ እግዚአብሔር ያልተደረሱትን ሕዝቦቹን ለማዳን ሲል የማይቻለውን ነገር እንኳ በእናንተ በኩል ያደርጋል።