በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። (ፊልጵስዩስ 4፥6)
ልመናችንን በእግዚአብሔር ፊት ስናሳውቅ ከምናመሰግንባቸው ነገሮች መካከል አንዱ የሰጠን ተስፋዎች ናቸው። እነዚህ ጭንቀት የሚፈጥረውን አለማመን የሚያስወግዱ መሣሪያዎቻችን ናቸው። በእነዚህ ተስፋዎች እንዴት እንደምታገል ተመልከቱ።
አገልግሎቴ ከንቱ እና ባዶ ስለመሆኑ ስጨነቅ፣ በኢሳይያስ 55፥11 የተስፋ ቃል አለማመንን እታገላለሁ፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዓላማ ይፈጽማል።”
ሥራዬን ለመሥራት ደካማ ስለመሆኔ ስጨነቅ፣ አለማመንን በክርስቶስ የተስፋ ቃል እዋጋለሁ፦ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥9)።
ወደፊት ማድረግ ስላለብኝ ውሳኔዎች ስጨነቅ፣ አለማመንን በዚህ ተስፋ እዋጋለሁ፦ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” (መዝሙር 32፥8)።
ጠላቶቼን ስለመግጠም ስጨነቅ፣ አለማመንን በዚህ የተስፋ ቃል እዋጋለሁ፦ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል?” (ሮሜ 8፥31)።
ስለምወዳቸው ሰዎች ደኅንነት ስጨነቅ፣ እኔ ክፉ ሳለሁ ለልጆቼ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቅሁ፣ የሰማዩ አባትማ “ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?” በሚለው ቃል እዋጋለሁ (ማቴዎስ 7፥11)።
ስለ ክርስቶስ ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ ”አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት” በሚለው ማስታወሻ መንፈሳዊ ሚዛኔን ለመጠበቅ እጋደላለሁ (ማርቆስ 10፥29–30)።
ስለመታመም ስጨነቅ፣ አለማመንን በዚህ ተስፋ እዋጋለሁ፦ “የጻድቅ መከራው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉም ያድነዋል” (መዝሙር 34፥19)። “መከራ ትዕግሥትን እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ትዕግሥት ጽናትን፣ ጽናት የተፈተነ ባሕርይን፣ የተፈተነ ባሕርይ ተስፋን፤ ይህም ተስፋ ለዕፍረት አይዳርገንም፤ እግዚአብሔር በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ ፍቅሩን በልባችን አፍስሶአልና” የሚለውን ቃል በትኩረት አሰላስላለሁ (ሮሜ 5፥3-5)።