ደስታው የማይናወጥ አምላክ | ነሐሴ 21

“ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሐንስ 15፥11)። 

እግዚአብሔር ፍጹም ሉዓላዊ ነው።

“አምላካችንስ በሰማይ ነው፤ እርሱ ደስ የሚለውን ያደርጋል” (መዝሙር 115፥3)።

ስለዚህ እርሱ አይጨነቅም፣ ግራም አይጋባም። ሰዓሊ በሥራዎቹ እንደሚደሰት፣ በመቤዠት ታሪክ ውስጥ ያረፉትን ድንቅ የቀለማት ውህድ ሲመለከት እርሱም እንዲሁ ይደሰታል። በጽኑ መሰረት ላይ የተመሰረተ ደስተኛ አምላክ ነው።

ደስታው ደግሞ የተመሠረተው በራሱ ማንነት ላይ ነው። ከፍጥረት በፊት፣ በእርሱ ደስ በሚለው ልጁ ውስጥ ባለው የእርሱ ክብር ደስ ይለው ነበር (ማቴዎስ 3፥17)። ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ደስታ በፍጥረት እና በማዳን ሥራው ይፋ ወጥቷል።

እነዚህ ሥራዎች ክብሩን ስለሚያንጸባርቁ የእግዚአብሔርን ልብ ደስ ያሰኛሉ። ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ (መዝሙር 19፥1)። “የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው“ (መዝሙር 104፥31)። እግዚአብሔር የሚያደርገውን ሁሉ የሚያደርገው ይህን አስደናቂ ክብር ለመጠበቅና ለማሳየት ነው፤ በዚህም ደግሞ ነፍሱ ሐሴት ታደርጋለች። 

በመጨረሻም፣ የእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ የሚደመደመው በዋጀው ሕዝብ ምስጋና ነው። “ስለ ብርቱ ሥራው አመስግኑት፤ እጅግ ታላቅ ነውና ወድሱት” (መዝሙር 150፥2)። ያዳናቸው ቅዱሳን በልዕልናው ከፍታ ተደንቀው ሲያወድሱት የደስታው ከፍታ ይሆናል። ዙፋኑ በምስጋናቸው ሲሞላ፣ እልልታቸው በማደሪያው ሲያስተጋባ ያኔ እግዚአብሔር ይከብራል። “እርሱ በፈረስ ኀይል አይደሰትም፤ በሯጭም ብርታት ላይ ደስታውን አያደርግም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል” (መዝሙር 147፥10-11)።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የሚደሰተው እና የሚረካው እርሱ ብቻ አይደለም፤ የእኛም የደስታችን ጣራ እና የእርካታችን ጥግ ያለው በዚህ ነው። ምስጋና የእግዚአብሔርን ታላቅነት የምናይበት እና የምናጣጥምበት የደስታችን መደምደሚያ ነው። የተፈጠርነውም ለዚህ ነው።

ስለዚህም፣ እግዚአብሔር ከእኛ ምስጋናን መፈለጉ እና እኛ ደግሞ በእርሱ ውስጥ ደስታን መፈለጋችን ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው፣ አይጋጩም። በክርስቶስ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ክብር ወንጌል ትልቁ ውጤት ይህ ነው!