ራሳችሁን በተስፋ አስታጥቁ | መጋቢት 2

“ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።” (ማቴዎስ 5፥8)

ጳውሎስ የሥጋ ሥራን “በመንፈስ” ግደሉ ሲል (ሮሜ 8፥13)፣ ለመግደል ጥቅም ላይ የሚውለውን፣ ከመንፈስ መሣሪያዎች አንዱ የሆነውን የመንፈስን ሰይፍ ወይም የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቀሙ ማለቱ ነው ብዬ እረዳዋለሁ (ኤፌሶን 6፥17)።

እናም ሥጋችን በፍርሀት እና በምኞት ተነድቶ ወደ ኅጢአት ሲሄድ፣ በመንፈሱ ሰይፍ እነዚያን ፍርሀቶች እና ምኞቶች ልንገድላቸው ይገባል። በእኔ ልምድ፣ ይህ ማለት የኅጢአት ሥር የሆነውን ተስፋ፣ ከእርሱ በሚበልጠው የተስፋ ኅይል መቁረጥ ማለት ነው።

ለምሳሌ፦ አንድ ያልተገባ ወሲባዊ ደስታ ስፈልግ፣ ይህንን ምኞት የሚገድለው ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና” በሚለው የደስታ ተስፋ ይሆናል። እግዚአብሔርን በንጹሕ ሕሊና እና በቅርበት ሳየው የተሰማኝን ደስታ አስታውሳለሁ፤ ከዚያ ደግሞ በኅጢአት የሚገኘው ደስታ ጨቋኝ፣ ጊዜያዊ እና የውሸት እንደሆነ ራሴን አስታውሳለሁ። በዚህም ሊረታኝ የነበረውን የኀጢአት ክንድ እግዚአብሔር ይሰብርልኛል።

በየጊዜው ለሚገጥሙን ፈተናዎች የሚሆኑ ተስፋዎችን በእጃችን መያዝ፣ ከኅጢአት ጋር ለምናደርገው ጦርነት ስኬታማ ለመሆን ቁልፍ ነው።

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ከሁኔታችን ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋዎች ላናገኝ እንችላለን፤ በእንደዚህ ዐይነት ጊዜ ለየትኛውም ዐይነት ሁኔታ የሚጠቅሙንን ጥቅሶች መያዝ ያስፈልጋል።

እነዚህ አራት የተስፋ ቃላት ከኅጢአት ጋር በማደርገው ትግል ብዙ ጊዜ የምጠቀምባቸው ናቸው፦

  • እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ።“ (ኢሳይያስ 41፥10)
  • “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል።“ (ፊልጵስዩስ 4፥19)
  • “ከዚህም በላይ ለእርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጒድለት እቈጥረዋለሁ።” (ፊልጵስዩስ 3፥8)
  • በመጨረሻም፣ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና።“ (ማቴዎስ 5፥8)

ሁልጊዜም የተስፋ ምሽጎቻችሁን በእግዚአብሔር ቃል ገንቡ፣ ሆኖም ግን እግዚአብሔር በሕይወታችሁ የሰጣችሁን ጥቂት ጥቅሶች ደግሞ የሙጥኝ በሉ። ሁለቱንም አድርጉ፤ የቀድሞዎቹን የጥቅስ ስንቆች አጥብቃችሁ ያዙ፣ ከዚያም በየዕለቱ አዳዲስ ተስፋዎችን ፈልጉ።