ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? (ሮሜ 8፥32)
እግዚአብሔር የመከራና የሕመምን አጥፊነት ነጥቆታል። ይህንን ማመን አለባችሁ፤ ካልሆነ በዚህ ዓለም ሕይወት በክርስትናችሁ ልታድጉም ሆነ እንደ ክርስቲያን ልትቀጥሉ አትችሉም።
በዚህ ምድር እጅግ ብዙ ችግሮች፣ ሕመሞች፣ ወደኋላ የሚይዙ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች፣ እና ጭንቀቶች አሉ። ታዲያ ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ አበሣ እኔን የማውደም አቅም እንደሚያሳጣው፣ ከዚያም አልፎ ለደስታዬ እንደሚቀይረው ባላምን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር?
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 3፥21-23 ላይ የሚናገረውን አስገራሚ ቃል ተመልከቱ፦ “እንግዲህ ማንም በሰው አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤ ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ፣ ዓለምም ሆነ ሕይወት ወይም ሞት፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው፣ ሁሉ የእናንተ ነው፤ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።” ዓለም ሁሉ የእኛ ነው፣ ሕይወት ሁሉ የእኛ ነው፤ ሞት የእኛ ነው። ምን እያለን ነው? ዓለምን ሁሉ በሉዓላዊነት የሚገዛው እግዚአብሔር፣ የመረጣቸው ልጆቹ እርሱን በመታዘዝና በማገልገል ሲኖሩ የሚገጥማቸውን መከራ ሁሉ በታላቅ ክንዱ አስገዝቶ ለዘለዓለም በእርሱ የሚደሰቱበትን የቅድስና ግዛት ይመሠርታል።
እግዚአብሔር በእርግጥም አምላክ ከሆነ፣ ይህም አምላክ ለእኛ ከሆነ፣ ምንም ነገር በእኛ ላይ አይሰለጥንም። ለገዛ ልጁ ያልራራለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንም ነገር ከእርሱ ጋር አትረፍርፎ በልግስና ይሰጠናል። ዓለምን፣ ሕይወትን፣ ሞትን፣ ራሱን እግዚአብሔርን ጨምሮ፣ አንዳች ሳያስቀር ይሰጠናል።
ስለዚህም፣ ሮሜ 8፥32 እንደ ውድ ጓደኛ የሚሆነን ጥቅስ ነው። የእግዚአብሔር የወደፊት ተስፋ እጅግ ከአቅም በላይ ነው። ዋናው ነገር ደግሞ መሠረቱ ነው። የመንግሥተ ሰማይ ስሌት ልንለው እንችላለን። ከየትኛውም እንቅፋት ተጠብቀን የምንቆምበት መሠረት ዐለታችን ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል፣ ለገዛ ልጁ አልሳሳም። ስለዚህ … በሰማዩ ስሌት መሠረት፣ ሁሉ ነገሩ የሆነው ልጁን ሳይሳሳ ለሰጣቸው ልጆቹ፣ ውድ ልጁ የሞተለትን ነገር ሁሉ እንዴት አትረፍርፎ አይሰጣቸውም? በጎውን ሁሉ ይሰጠናል፣ ክፋትንም ሁሉ ለመልካማችን ይሰራዋል።
የእኛ መወደድ፣ እግዚአብሔር ልጁን እንደወደደበት ፍቅር ሁሉ የተረጋገጠ ነው!