በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን። (ኤፌሶን 1፥4-5)
በበርካታ ክርስትያኖች ዘንድ እውቅ የሆነውና “የሰባኪዎች ልዑል” ተብሎ የሚጠራው ቻርልስ ስፐርጅን የነበረውን የሕይወት ልምድ፣ ሁሉም ክርስቲያን ሊለማመደው ይችላል።
ከ1826 እስከ 1884 ዓ.ም የኖረው ስፐርጅን፣ የጆርጅ ሙለር እና የሀድሰን ቴይለር ጓደኛ ነበር። እነዚህም በአማኞች ዘንድ እውቅ የሆኑ ሰዎች ናቸው። በለንደን ከተማ ትገኝ በነበረች ሜትሮፖሊታን ታበርናክል በተባለች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለ30 ዓመታት ያህል አገልግሏል። በጊዜውም እጅግ የታወቀ መጋቢ ነበር።
ከስብከቱ ኃይል የተነሣ በየሳምንቱ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ይመጡ ነበር። ስብከቶቹ ዛሬም ድረስ ይታተማሉ። በብዙዎች ዘንድ የወንጌል ስብከት ምሳሌ ተደርጎ ይታያል።
ስፐርጅን በ16 ዓመቱ ስለገጠመው እና ሕይወቱንና ተልዕኮውን ስለቀየረው ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦
“ወደ ክርስቶስ በመጣሁበት ወቅት ሁሉንም ነገር በራሴ ያደረኩት ይመስለኝ ነበር። አምላኬን ከልቤ ብፈልገውም፣ እውነታው ግን እርሱ እየፈለገኝ መሆኑን ፈፅሞ አልተረዳሁም ነበር። ሁሉም አዲስ አማኝ ይህንን በመጀመሪያ ሰሞን ላይረዳ ይችላል።
ሉዓላዊ ስለሆነው አሸናፊ ፀጋው እውነቱን የተረዳሁበትን ቀን እና ሰዓት አሁንም አስታውሰዋለሁ። ጆን በንያን እንዳለው፣ እውነቱ በጋለ ብረት በልቤ እንደተቀረጸ እስኪሰማኝ ድረስ፤ ከጨቅላነት ወደ ሙሉ አዋቂነት በቅጽበት ያደግሁበትን እና መንፈሳዊ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የተሞላሁበትን ጊዜ አስታውሰዋለሁ።
አንድ ቀን ምሽት ላይ በእግዚአብሔር ቤት ተቀምጬ ስብከት እየሰማሁ እንደነበር አስታውሳለሁ። ነገር ግን ሰባኪው እያስተላለፈ የነበረውን መልዕክት ስላላመንኩበት ከልቤ እያደመጥኩት አልነበረም።
ከዛ ግን ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ አለብኝ፦ እንዴት ክርስቲያን ልሆን ቻልኩ? ጌታን ከልቤ ስለፈለኩት። እሺ ግን ከጅማሬውስ እንዴት ልፈልገው ቻልኩ? እውነታው ድንገት ብልጭ አለልኝ — እግዚአብሔርን እንድፈልገው የሚያደርገኝ ነገር በአእምሮዬና በልቤ ውስጥ ተደርጎ ካልነበረ በቀር፣ የሆነ ለውጥ ካልተከሰተ በስተቀር፣ በራሴ አቅም ፈፅሞ እግዚአብሔርን ልፈልገው አልችልም። “በእርግጥ ጸልዬ ነበር” አልኩ። አሁንም ግን፣ እንዴት ልፀልይ ቻልኩ? ወደ ፀሎት የመራኝ ቃሉን ማንበቤ ነበር። ቆይ ታዲያ ወደ ቃሉስ ማን መራኝ?
በዚያም ቅፅበት፣ እግዚአብሔር ከሁሉም ነገር ጀርባ እንደነበር በራልኝ። የእምነቴ ደራሲ እርሱ ነበር። እናም የፀጋ አስተምህሮ ያኔውኑ ተገለጠልኝ። እስከዛሬም ከዚያ ውብ መንገድ ወጥቼ አላውቅም። ‘የመዳኔና የመለወጤ ብቸኛ ምክንያት እግዚአብሔር መሆኑን ለማወጅ ዘወትር እተጋለሁ፣ ከዚያ ሌላም ስብከት አይኖረኝም።”
እናንተስ? የመዳናችሁ ብቸኛ ምክንያት እግዚአብሔር መሆኑን ታውጃላችሁ? ከሁሉ ነገር ጀርባ ያለው እርሱ መሆኑንስ ታምናላችሁ? ይህስ እውነት ሉዓላዊና አሸናፊ የሆነውን የፀጋውን ክብር እንድታመሰግኑት ያደርጋችኋል?