እውነተኛው እምነት የክርስቶስን መምጣት ይናፍቃል | ጥር 17

“ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።” (ዕብራውያን 9፥28)

ኀጢአታችሁ በክርስቶስ ደም እንደተወሰደና፣ ሲመጣም ከእግዚአብሔር ቁጣ እንደሚከልላችሁ፣ እንዲሁም ወደ ዘላለም ህይወት እንደሚያደርሳችሁ ለማወቅ ምን ማድረግ አለባችሁ? መልሱ፦ የእርሱን መምጣት በጉጉት እንድትጠብቁ በሚያደርጋችሁ መንገድ በክርስቶስ እመኑ የሚል ነው።

ይህ ክፍል የሚጠባበቁትን ለማዳን እንደሚመጣ ይነግረናል። ስለዚህ እንዴት ትዘጋጃላችሁ? የእግዚአብሔርን ምህረት በክርስቶስ በኩል በመቀበል፣ ልታገኙት እንዴት ዝግጁ መሆን ትችላላችሁ? ለመምጣቱ እንድትጓጉ በሚያደርጋችሁ እምነት እርሱን በማመን ነው።

ክርስቶስን በጉጉት መጠበቃችን እርሱን በእውነት መውደዳችንንና ከልብ በእርሱ ማመናችንን የሚያሳይ ምልክት ነው።

ከሲኦል ማምለጥን ብቻ የሚፈልግ ክርስቶስን ግን የመፈለግ መሻት የሌለው ሐሰተኛ እምነት አለ። የዚህ ዓይነት እምነት አያድንም። ለክርስቶስ መምጣት መጓጓትንም አይፈጥርም። እንደውም፣ ይህንን ዓለም አብዝቶ ያተርፍ ዘንድ ክርስቶስ የተቻለውን ያህል ሳይመጣ ቢቆይ ይመርጣል።

ነገር ግን ከርስቶስን እንደ አዳኝ እና አምላክ፣ እንደ ብቸኛ ተስፋ እና የደስታ ምንጭ፣ ደግሞም እንደ ውድ ሀብት የሚየው እምነት፣ ለክርስቶስ መምጣት እንድንጓጓ የሚያደርገን እምነት ነው። የሚያድነውም እምነት እርሱ ነው።

ስለዚህ ከዓለምና ከኀጢአት ፊታችሁን እንድታዞሩ አበረታታችኋለሁ። ወደ ክርስቶስ ተመልከቱ። እንደ እሳት አደጋ መድን ሳይሆን በጉጉት እንደሚጠበቅ ሀብት፣ እንደ ጓደኛና አምላክ ወድዳችሁ ተቀበሉት፣ አስገቡት።