እውነተኛ ወይስ አስመሳይ እምነት | ግንቦት 28

ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኗል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም። (ዕብራውያን 9፥28)

ክርስቶስ ኅጢአታቸውን ከተሸከመላቸው፣ ‘ብዙ ሰዎች’ ከተባሉት መካከል እንገኝ ይሆን? በዳግም ምፅዓቱ ጊዜስ መዳናችን የተረጋገጠ ነው? ይህ በሁላችንም ዘንድ የሚቀጣጠል ጥያቄ ነው።

ዕብራውያን 9፥28 መልስ ግልጽ ነው። በጉጉት የምንጠባበቀው ከሆነ፣ “አዎን” ብሎ ይመልሳል። ዳግመኛ መምጣቱን እንድንጠባበቅ በሚያደርገን መልኩ በክርስቶስ ከታመንን፣ ኅጢአታችን ከእኛ መወሰዱን እና ከፍርድ ነጻ መሆናችንን ማወቅ እንችላለን።

“በክርስቶስ አምናለሁ” የሚል፣ ነገር ግን ክርስቶስን እንደ እሳት አደጋ መድን ብቻ የሚመለከት አስመሳይ እምነት አለ። እንዲህ ያለው እምነት ከሲዖል ለማምለጥ ብቻ ሲባል የሚደረግ ነው። ክርስቶስን ከልብ አይፈልግም። እንደውም የዚህን ዓለም ደስታ እስከ ጥግ ድረስ ያጣጥም ዘንድ፣ ክርስቶስ ዳግመኛ ባይመጣ ደስ ይለዋል። ይህ የሚያሳየው እንዲህ ያለው ልብ ከዓለም ጋር እንጂ ከክርስቶስ ጋር እንዳይደለ ነው።

ስለዚህ፣ የእምነታችንን እውነተኛነት የሚፈትነው ጥያቄ ይህ ነው፦ የክርስቶስን መምጣት በጉጉት እንጠብቃለን? ወይስ ከዓለም ጋር ያለንን ፍቅር እናጣጥም ዘንድ እንዲዘገይ እንፈልጋለን?

እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን፣ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጕጕት በመጠባበቅ” እንኑር (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥7)። ደግሞም ከፊልጵስዩስ ሰዎች ጋር፣ “እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን” በማለት እንትጋ (ፊልጵስዩስ 3፥20)።

ወሳኙ ጥያቄ ይህ ነው፦ ዳግመኛ መምጣቱን እንናፍቃለን? ወይስ የእርሱ መምጣት ምድራዊ ዕቅዶቻችንን እንዳያበላሽብን እንሰጋለን? ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታችን ለዚህ ጥያቄ በምንሰጠው ልባዊ መልስ ላይ ይንጠለጠላል።