በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን፣ ለማሳየት ነው። (ሮሜ 3፥25-26)
ምናልባት ሮሜ 3፥25-26 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ አስፈላጊው ጥቅስ ሊሆን ይችላል።
እግዚአብሔር ፍጹም ፍትሐዊ ነው! ታዲያ እንዴት ኅጢአተኛውን ሳይቀጣ ያልፋል? ወንጀለኛውን ነፃ የሚያወጣ ፍትሐዊው ዳኛ ምን ዓይነት ዳኛ ነው?
ፍትሐዊ ነው፤ ኅጢአተኛውንም ነፃ ያወጣል! ወንጀለኞችን ባለመቅጣቱ ግን ፍትሕን ያጓደለ ወንጀለኛ ዳኛ አይሆንም። ይህ በእውነት ትልቅ ዜና ነው!
- “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው” (2 ቆሮንቶስ 5፥21)። እርሱ ኅጢአታችንን ይወስዳል፤ እኛ ፅድቁን እንወስዳለን።
- “ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ” (ሮሜ 8፥3)። የማንን ሥጋ? የክርስቶስን ስጋ! በዚህ ሥጋ የተኮነነው ኅጢአት የማነው? የእኛው ኅጢአት! ሥጋው ምን አስገኘልን? ከኩነኔ ነፃ ወጣን!
- “እርሱ (ክርስቶስ) ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥24)።
- “እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቶአልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ፣ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥18)።
- “በሞቱ ከእርሱ ጋር እንደዚህ ከተባበርን፣ በትንሣኤው ደግሞ በርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” (ሮሜ 6፥5)።
በዓለም ላይ አስፈሪው ዜና በፈጣሪያችን ኩነኔ ውስጥ መውደቃችን እና እርሱም በፃድቅነቱ ምክንያት፣ ከክብሩ ታላቅነትም የተነሳ ቁጣውን በኛ ላይ ማውረዱ የማይቀር መሆኑ ከሆነ…
…እግዚአብሔር የክብሩ ታላቅነት ሳይቀንስ፣ የተመረጡት ሰዎች በልጁ በክርስቶስ በኩል ለዘላለም የሚድኑበትን መንገድ ማበጀቱ እና መፈጸሙ በዓለም ላይ ያለ ምርጡ ዜና (ወንጌል!) ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ኅጢአተኞችን ሊያድን ወደ አለም መጣ።