የቤተ ልሔም ልዕለ-ተፈጥሯዊ ኮከብ | ታሕሳስ 12

የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።

የማቴዎስ ወንጌል 2፥2

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ቦታ የተከሰቱ አንዳንድ ክስተቶች እንዴት ተከሰቱ ብለን እንድንገረም ያደርጉናል። እንዴት ነው ይህ “ኮከብ” ሰብዐ ሰገልን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም እየመራ ያመጣቸው?

በርግጥ ኮከቡ እየመራቸው ወይም መንገድ እያሳያቸው ስለመምጣቸው የሚናገር ነገር የለም። ኮከብ በምሥራቅ አይተው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ ብቻ ነው የሚለን (ማቴዎስ 2፥2)። እንዴትስ ነው ይህ ኮከብ ማቴዎስ 2፥9 ላይ እንደሚናገረው፣ ከፊታቸው እየሄደ ከኢየሩሳሌም ወደ ቤተ ልሔም ያለውን የስምንት ኪሎ ሜትር መንገድ የመራቸው? እንዴት ነው አንድ ኮከብ ህፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ መቆምስ የቻለው?

መልሱ፥ አናውቅም ነው። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ከፕላኔቶች፣ ኮሜቶች፣ ወይም ተዓምራዊ ብርሃኖች መገጣጠም አኳያ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ሆኖም ግን በርግጥ የምናውቀው ነገር የለም። እናም በስተ መጨረሻ ምንም መንፈሳዊ ጥቅም በሌላቸው በእነዚህ ጊዜያዊ መላምቶች አእምሯችሁን እንዳታጨናንቁ ወይም እንዳትተክሉ ልመክራችሁ እወዳለሁ።

በዚህ ጉዳይ እናንተን ለማሳሰብ ስል በጅምላ መናገር ሊኖርብኝ ይችላል፤ ሆኖም ግን በእንደነዚህ ዐይነት – ማለትም – ከዋክብቱ እንዴት ሊመሯቸው እንደቻሉ፣ የቀይ ባህር እንዴት እንደተከፈለ፣ መና እንዴት እንደወረደ፣ ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ እንዴት እንዳደረ፣ ጨረቃ ወደ ደም እንዴት እንደምትቀየር እና በመሳሰሉት ነገሮች አእምሮአቸውን የሚያጨናንቁ ሰዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ ዳር ላይ ላሉ ነገሮች ትኩረት መስጠት የሚወዱ ሰዎች ናቸው።

ታላላቅ እና ማዕከላዊ ለሆኑት የወንጌል እውነቶች ጥልቅ ፍቅር ሲኖራቸው አይታዩም። ስለ እግዚአብሔር ቅድስና፣ ስለ ኀጢአት አስከፊነት፣ ስለ ሰው አቅም አልባነት፣ ስለ ክርስቶስ ሞት፣ በእምነት ብቻ ስለሚገኘው ጽድቅ፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ የመቀደስ ሥራ፣ ስለ ክርስቶስ በክብር መመለስ፣ እና ስለ መጨረሻው ፍርድ ግድ ሲላቸው ብዙም አይታዩም። ሁልጊዜ ልባቸውን የሚያነቃቃው እና በተመስጦ የሚያነቡት ርዕስ፣ ከዋናው መንገድ የወጣና የጎንዮሽ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ወይም አጭር ጽሑፍ ነው። በታላላቆቹ እና ማዕከላዊ በሆኑት የወንጌሉ እውነታዎች እምብዛም አይደነቁም።

ሆኖም ግን፣ በዚህ ኮከብ ዙሪያ ግልጽ የሆነው ነገር በራሱ ከሚያደርገው እና ከተለመደው ውጪ እያደረገ መሆኑ ነው። ይህ ኮከብ ሰብዓ ሰገል የእግዚአብሔርን ልጅ የሆነውን ያመልኩ ዘንድ እየመራቸው ይገኛል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው አረዳድ ደግሞ የከዋክብትን ፈቃድ የሚመራ አንድ አካል ብቻ ነው፤ እርሱም እግዚአብሔር ነው።

በመሆኑም ከዚህ የምንማረው ዋነኛ ነገር፣ አሕዛብ ክርስቶስን ያመልኩ ዘንድ እግዚአብሔር እየመራቸው መሆኑን ነው። ይህንንም እያደረገ ያለው ዓለም ዓቀፍ ተጽእኖን በመፍጠር እና ሥልጣኑን በመጠቀም ነው።

ማንም የማያውቃት አንዲት ድንግል ሴት በምትወልድበት ጊዜ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በተመሳሳይ ወቅት እና ሰዓት፣ እግዚአብሔር ጠቅላላውን የሮምን ግዛት በቆጠራ እንዲንቀሳቀስ እንዳደረገ ሉቃስ ያሳየናል። ማቴዎስ ደግሞ በሰማይ ያሉት ከዋክብት በምድር ያሉ ጥቂት የውጭ አገር ሰዎች ልጁን ያመልኩ ዘንድ እንዴት አድርገው ወደ ቤተ ልሔም እንደመሯቸው ይገልፅልናል።

ይህ የእግዚአብሔር አሠራር ነው። በዚያን ጊዜ ይህ እንዲሆን አድርጎ ነበር። አሁንም ደግሞ ይህንን ይሠራል። ትኩረቱ ሕዝቦች ላይ ነው። የእግዚአብሔር ፍላጎት ሁሉም ሕዝቦች ልጁን ያመልኩት ዘንድ ነው (ማቴዎስ 24፥14)።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ለሥራ ባልደረቦቻችሁ፣ አብረዋችሁ ለሚማሩት፣ ለጎረቤቶቻችሁ፣ እና ለቤተሰቦቻችሁ ይህ ነው። ዮሐንስ 4፥23 ላይ እንደሚል፤ “ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና።

በማቴዎስ ወንጌል ጅማሮ ላይ፣ የ”ኑ እና እዩ” ድግምግሞሽ እናገኛለን። በወንጌሉ ፍፃሜ ላይ ግን ወደ “ሂዱ አና ንገሩ” ተቀይሮ እናገኘዋለን።

በዚህ ሁሉ መካከል የእግዚአብሔር ዓላማ አልተቀየረም። አሕዛብን ሁሉ ለልጁ አምልኮ የሚሰበስብበት ኀይሉም አልደከመም። ይህ ዓለም የተፈጠረው እና እስካሁንም የቆየው ክርስቶስ እንዲከብር፣ እንዲገንን፣ እና በሕዝብ ሁሉ እንዲመለክ ነው።