ከኤቨረስት ተራራ የተሻለ | ሚያዚያ 3

እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። (ሮሜ 8፥28)

በዚህ ግዙፍ በሆነው የተስፋ ቃል ውስጥ የምትኖሩ ከሆነ፣ በዓለም ረጅሙ እና ግዙፉ ከሆነው ከኤቨረስት ተራራ የበለጠ ሕይወታችሁ ጠንካራ እና የተረጋጋ ይሆናል።

ሮሜ 8፥28 ቅጥር ውስጥ ስትሆኑ፣ እናንተን ማናወጥ የሚችል ምንም ነገር አይኖርም። ከሮሜ 8፥28 ውጪ ግን ያለው ግራ መጋባት፣ ጭንቀት፣ ፍርሃትና እርግጠኛ አለመሆን ብቻ ነው። ከዚህ ሁሉን-ዓቀፍ የእግዚአብሔር ጸጋ ተስፋ ውጭ፣ በአደንዛዥ ዕፅና ፓርኖግራፊ ሱስ የተሰሩ የጭድ ቤቶች አቅጣጫ ሊያስቱ በየቦታው አሉ። የማይረቡ የመበልጸጊያ ስልቶች፣ ጊዜያዊ የኢንሹራንስ ሽፋኖች፣ እርባና ቢስ የጡረታ ዕቅዶች በጭካ እንደተሰሩ ፈራሽ ቤቶች በየቦታው የማያዋጣ ዋስትና ሊሰጡ ተደርድረዋል። እንደ ፌስታል ዘላቂ ያልሆኑ ካዝናዎች፣ ሌባ መከላከያ አላርሞችና የፀረ ሚሳኤል ምሽጎች ሞልተዋል። ለሮሜ 8፥28 ተተኪ ነን የሚሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ቀቢጸ-ተስፋዎች አሉ።

አንዴ ግን በፍቅር በር አልፋችሁ ወደ ሮሜ 8፥28 ግዙፍና የማይናወጥ መዋቅር ከገባችሁ፣ ​​ሁሉም ነገር ይለወጣል። መረጋጋት፣ ሥር መስደድ እና ነፃነት ወደ ህይወታችሁ ይመጣል። ከዚያም በኋላ በቀላሉ የምትናወጡ አትሆኑም። ሉዓላዊው አምላክ የምታልፉበትን ህመም እና ደስታ ሁሉ ለእናንተ ጥቅም እንደሚቆጣጠረው በማወቅ ያላችሁ መተማመን ያለ ልክ ይጨምራል። በህይወታችሁ ውስጥ ወደር የለሽ መሸሸጊያ፣ ደህንነት፣ ተስፋና ኀይል ይሆናችኋል።  

የእግዚአብሔር ህዝብ፣ በየትኛውም መከራ ውስጥ፣ በበሽታም ሆነ በሞት፣ ከኩፍኝ አንስቶ እስከ ሬሳ ማቆያ ድረስ ባሉ ሁኔታዎች መካከል፣ በሮሜ 8፥28 የወደፊት ፀጋ ላይ ታምነው ሲኖሩ፣ በዓለም ላይ እጅግ ነፃ፣ ጠንካራ እና ለጋስ ሰዎች ይሆናሉ። 

ብርሃናቸው ላይጠፋ ይበራል፣ ሰዎችም ሁሉ በሰማያት ያለውን አባታቸውን ያከብራሉ (ማቴዎስ 5፥16)።