ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ። (ዕብራውያን 10፥35)
ዓለም ሊሰጠን ከሚችለው ነገር ሁሉ በላይ የእግዚአብሔር የበላይነት ታላቁ ሽልማታችን እንደሆነ ልናሰላስል ይገባናል። እንደዚያ ካልሆነ፣ ልክ እንደማንኛውም ሰው ዓለምን እንወድዳለን፤ ኑሯችንም እንደ ማንኛውም ሰው ይሆናል።
እስቲ ዓለምን የሚነዱትን ነገሮች ውሰዱና እግዚአብሔር ምን ያህል የተሻለ እና የበለጠ ጽኑ እንደሆነ አስቡ። ገንዘብን ወይም ጾታዊ ግንኙነትን ወይም ስልጣንን ውሰዱ፣ ከዚያም ከሞት አንጻር አስቧቸው። ሞት እያንዳንዳቸውን ያጠፋቸዋል። የምትኖሩት ለዚያ ከሆነ፣ ብዙም አታተርፉም፤ ያገኛችሁትንም ታጡታላችሁ።
ነገር ግን የእግዚአብሔር ሀብት የላቀ ነው፤ ደግሞም ዘላቂ ነው። ከሞት በላይ ይሻገራል። ከገንዘብ ይሻላል፤ ምክንያቱም ገንዘብ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤ እርሱም ደግሞ አባታችን ነው። የእርሱ ወራሾች ነን። “ሁሉ የእናንተ ነው፤ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥22-23)።
ከፆታዊ ግንኙነትም የተሻለ ነው። ኢየሱስ ፆታዊ ግንኙነት አልነበረውም፣ ነገር ግን እንደ እርሱ ፍጹምና ሙሉ ሰው ኖሮ አያውቅም፣ አይኖርምም። ፆታዊ ግንኙነት የትልቅ እውነታ ጥላ ነው — በጣም አስደናቂ ተብሎ የሚታሰበውን የግብረ ሥጋ ግንኙነትን እንደማዛጋት የሚያስመለው ወደፊት የሚመጣው ህብረትና ደስታ — ምስል ነው።
የእግዚአብሔር ሽልማት ከሥልጣን የተሻለ ነው። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ከመሆን የሚበልጥ የሰው ስልጣን የለም። “በምድራዊ ሕይወት ጒዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን?” (1ኛ ቆሮንቶስ 6፥3)? “እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በእርሱ ዙፋን ላይ እንደ ተቀመጥሁ፣ ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ” (ራእይ 3፥21)።
እንደዚህ እያለ ይቀጥላል። ዓለም ከምትሰጠው ተስፋ ሁሉ እግዚአብሔር የሚሰጠው ተስፋ የተሻለ፣ የላቀና የበለጠ ነው።
ምንም ዓይነት ንጽጽር የለውም። ሁልጊዜ እግዚአብሔር ያሸንፋል። ጥያቄው፦ ከዚህ ከሚያታልለው ዓለም ፍዘት ነቅተን እውነት የሆነውን፣ የከበረውንና የዘላለሙን እውነታ ማየት፣ ማመንና መውደድ፣ በዚያም ደግሞ መደሰት እንችላለን ወይ የሚል ነው።