እግዚአብሔርን ስታገለግሉ ተጠንቀቁ | ጥቅምት 6

“ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም” (ሐዋርያት ሥራ 17፥24-25)።

እግዚአብሔርን የምናከብረው የሚያስፈልገውን እና የጎደለውን በማሟላት አይደለም። እንደውም የምናከብረው ለኛ የሚያስፈልገንን እንዲያሟላልን በመፀለይ፣ እንደሚመልስልን በመታመን እና በዚህ ውስጥ በደስታ በመኖር ነው።

ይህ የክርስቲያን ሄዶኒዝም የልብ ትርታ ነው። የክርስቲያን ሄዶኒዝም ዋናው መልካም ዜና፣ እርዳታን ከአርያም ስንማጸን እግዚአብሔር ይከብራል የሚለው ነው። “በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤ አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ” (መዝሙር 50፥15)። ይህ ቃል ለእርሱ እናስፈልገዋለን ብለን እንዳናስብ ያስጠነቅቀናል። እርሱን ስናገለግል መጠንቀቅ አለብን። እርሱ እኛን እንዲያገለግለን ልባችንን ካልከፈትን ክብሩን እንነጥቀዋለን። “እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም” (ሐዋርያት ሥራ 17፥25)።

ይህ እንግዳ ነገር ሊሆንብን ይችላል። ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ማገልገል ፍፁም መልካም ነገር ነው የሚመስለን። አገልግሎታችን ስድብ ሊሆንበት እንደሚችል አስበነው አናውቅም። ነገር ግን ጸሎት ምን ማለት እንደሆነ ስናሰላስል ይህ ግልጽ ይሆንልናል።

ሮቢንሰን ክሩሶ በተባለ ልብ ወለድ መጽሐፍ ላይ ዋናው ገፀ ባሕርይ በአንድ ደሴት ላይ ብቻውን ቀርቶ ሳለ፣ በመዝሙር 50፥12-15 ላይ ያለውን ቃል እንደ ተስፋ ወሰደ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ብራብ ለአንተ አልነግርህም፤ ዓለምና በውስጧ ያለውም ሁሉ የእኔ ነውና።… በመከራ ጊዜ ወደ እኔ ጩህ፤ አድንሃለሁ፤ አንተም ታከብረኛለህ።”

ይህ ማለት፣ እግዚአብሔርን የሚያሳንስ የአገልግሎት ዐይነት አለ ማለት ነው። ይህ እንዳይሆን፣ በክርስቶስ የተገለጠውንም ታላቁን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳናራክስ እጅግ ጠንቃቃ መሆን አለብን። ኢየሱስ “የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና” ብሎናል (ማርቆስ 10፥45)። አገልጋይ ለመሆን ፈቅዷል። በማገልገል ክብርን ሊቀዳጅ ፈልጓል።