መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንድነት እና ሴትነት

ዘፍጥረት 1፥26-31

እግዚአብሔር ፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው። እግዚአብሔርም፣ እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ። እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ። እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ። መሸ፤ ነጋም፤ ስድስተኛ ቀን።

“ኮምፕልመንታሪያን” ለረዥም ጊዜ የሚታወቁበት አንዱ መለያቸው፣ ወንዶች እና ሴቶች በቤተ ሰብ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በማኅበረሰብ ውስጥ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሚና የሚረዱበት መንገድ ነው። “ኮምፕልመንተሪያን” የሰው ሥነ ጾታ የእግዚአብሔር ክብር ታላቁ ማሳያ እና የሰው ግንኙነቶች ታላቁ ደስታ ነው ይላሉ፤ ደግሞም በአገልግሎት ትልቁ ፍሬያማነት የሚመጣው፣ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያሉ ጥልቅ ልዩነቶች ተቀባይነት ሲያገኙና እርስ በርሳቸው ተመጋጋቢ እንደ ሆኑ ሲታወቅ ነው በማለት ያምናሉ። ምክንያቱም እነዚህ ልዩነቶች አንዳቸው ሌላውን ሙሉ የሚያደርጉና የሚያስውቡ ናቸው።

ስለዚህ “ኮምፕልመንታሪያን”፣ አመለካከታችንንና የአኗኗር ዘይቤያችንን ከሁለት ጽንፎች ለማረም ይህንን መለያ ይጠቀማሉ። የመጀመሪያው ጽንፍ፣ በወንዶች የበላይነት ሳቢያ ሴቶች ላይ የሚደርሱ የተለያዩ ጭቆናዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ውብ ጠቀሜታ ያላቸውን የፆታ ልዩነቶች አለመቀበል ነው።

ይህ ማለት፣ በአንድ በኩል “ኮምፕልመንታሪያን” በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በግል ሆነ በተለያየ ሥልታዊ መንገድ የሚደርስ እንግልት፣ ንቀት፣ ማጎሳቆል እና ጭቆና እንዳለ ዕውቅና ይሰጣሉ፤ ይቃወማሉ፤ በጉዳዩም ከልብ ያዝናሉ። በሌላ በኩል፣ እግዚአብሔር በወንዶችና በሴቶች መካከል ያሰመረውን ልዩነት የሚያደበዝዙትን የ”እንስታዊነት እንቅስቃሴ” እና የእኩልነት ግፊቶችን ይቃወማሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ግፊቶች፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ልምላሜ የተነደፈውን የእግዚአብሔርን ሥርዐት ለማፍረስ የሚጥሩ ስለሆነ ነው።

“ኮምፕልመንተሪያን” አድሏዊ እና ጨቋኝ ባህልን ይቃወማሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ የፆታ ጭፍንነትን፣ የፆታ ደረጃንና ሁለቱን ወደ አንድ ጾታ የሚጨምቅ አስተሳሰብን ይቃወማሉ። በእነዚህ ሁለት የሕይወት ጽንፎች መካከል አቋምን እንይዛለን። መካከለኛው ቦታ አስተማማኝ ስለ ሆነ አይደለም (በጭራሽ!)፤ ይልቅ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ለወንዶች እና ለሴቶች ያዘጋጀው መልካም ዕቅድ እንደሆነ ስለምናስብ ነው። በዘፍጥረት 1 ላይ “እጅግ መልካም” ብሎ እንደ ተናገረው ማለት ነው።

እንዲያውም “የእንስታዊነት እንቅስቃሴ” የፆታ ልዩነትን በማፍረስ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የወንድ ጥቃት ለማስተካከል ያደረገው ሙከራ መዘዝን ይዞ መጥቷል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጨቋኝ ወንዶችን፣ ወይም ደግሞ “ሴታ ሴት” ወንዶችን በማፍራት መልሶ ሴቶችን ተጎጂ አድርጓል። በ“ኮምፕልመንታሪያን” እይታ፣ ወንዶች እና ሴቶችን ስለ ተፈጥሮአዊ ልዩነቶቻቸው እውነት፣ ውበት፣ እና ዋጋ ካላስተማርናቸው፣ በተጨማሪም እንዴት በዚህ መንገድ እንደሚኖሩ ማስተማር ካልቻልን፣ ልዩነቶቻቸው ጤናማ ባልሆኑ መንገዶች ያድጋሉ። ውጤቱም፣ የበሰለ ወንድ ወይም ሴት መሆን ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ የማያውቅ ሌላ አዲስ ትውልድ መምጣቱ ነው። ለዚህ የምንከፍለው ዋጋ አስከፊ ነው።

ስለዚህ አሁን ሰው ስለ መሆን ምንነት በመናገር፣ ወንድ እና ሴት ስለ መሆን ገላጭ ምሳሌ በመስጠት፣ ከዚያም በመቀጠል የ“ኮምፕልመንተሪያን”ን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ለማሳየት የተመረጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማቅረብ፣ ከጥቅሉ ሐሳብ ወደ ዝርዝሩ እሻገራለሁ።

ሰው የመሆን ታላቅነት

ሐምሌ 13፣ 1980 ምሽት፣  በቤተ ልሔም ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዬ እሁድ፣ “ሕይወት ተራ ነገር አይደለም!” በሚል ርዕስ መልእክት አቀረብኩ። በመልእክቱ እንዲህ አልኩ፦

እያንዳንዱ ሰው፣ ሕይወት ግጣሙ እንደተባለሸና እንደሚያንጠባጥብ ቧንቧ እንዳትሆንበት ይፈልጋል። የዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ፣ እንዲሁ የባዶ ቃላት ድግግሞሽ ከመሆን ያለፈ እንዲሆን የተመኛችሁበትን ጊዜ ሁላችሁም ታስታውሳላችሁ። ምናልባት ግጥም እያነበባችሁ እያለ፣ መኝታ ክፍላችሁ ተንበርክካችሁ ሳለ፣ ወይም ፀሓይ ስትጠልቅ በሐይቁ ዳርቻ በቆማችሁበት እንደዚያ አስባችሁ ይሆናል። በተለይ ደግሞ በውልደትና በሞት ወቅት ይከሰታል። ሙሴንም ከዘዳግም 32፥46 ጠቅሼዋለሁ፦ “እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም።”

ሕይወት ትርጉም የለሽ፣ የማትጠቅም፣ የማትረባ እና ተራ ነገር እንዳትሆን የሚፈልግ ጥልቅ መሻት፣ በእግዚአብሔር አምሳል በተፈጠረው በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ውስጥ አለ። ደራሲ አጋታ ክሪስቲ (1896–1976) የተናገረችውን ይህን ሐሳብ ተመልከቱ፦ “ሕይወትን መኖር እወዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ በሐዘን እየተሰቃየሁ፣ በተመሰቃቀለ ሁኔታ እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኜ የለየለት ምስኪን እሆናለሁ፤ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ በሕይወት መኖር በራሱ ትልቅ ነገር እንደሆነ በርግጠኝነት አውቃለሁ።”

ይህ አስደናቂ እውነት ይመስለኛል። ሕያው ሰው መሆን በራሱ የከበረ ነገር ነው። ምናልባት ልክ እንደ እኔ፣ አልፎ አልፎ እንደምደሰትባቸው ብርቅዬና አስደናቂ ጊዜያት አሳልፋችሁ ይሆናል። መስኮት፣ ወይም በር ወይም የሆነ ቦታ ቆሜ ሳለ በድንገት ይህ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣል፦ “እኔ ሕያው ነኝ። በሕይወት አለሁ። እንደ ዛፍ ወይም እንደ እንስሳ ሳይሆን እንደ ሰው አለሁ። እያሰብኩ፣ እየተሰማኝ፣ እየናፈቅኩ፣ እየተፀፀትኩ፣ እያዘንኩ ነው፤ በእግዚአብሔር አምሳል የተሠራሁ ሕያው ሰው። አዎ! ይሄ የከበረ ነገር ነው።“

በርግጥም የከበረ ነው። እናም በዚህ የከበረ፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሕያው ሰው በመሆን ውስጥ፣ ወንድ ወይም ሴት ናችሁ። “ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍጥረት 1፥27)። የተለየ፣ ከሁለቱም ጎራ ያልሆነ የሰው ልጅ የለም። የተለየ ጎራ የለም፤ እግዚአብሔርም የዚህ ዐይነት ምድብ እንዲኖር ፈጽሞ አልፈለገም። እግዚአብሔር የፈጠረው ወንድ እና ሴት ሰዎችን ነው። ይሄ ደግሞ የከበረ ነገር ነው።

ይሁን እንጂ፣ እግዚአብሔር ጾታዊ ልዩነቶችን የመሠረተበት ዐላማ፣ እነዚህ ሁለት ሰብዓዊ ፍጡሮች ልጆችን እንዲወልዱ እና እንዲንከባከቡ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማሳየት ስሕተት ነው። ለእንደዚህ ዐይነቱ ምናባዊ ማብራሪያ፣ ልዩነቶቹ እጅግ በጣም ብዙ እና በጣም ጥልቅ ናቸው። አንዲት ሴት እስከ ሰብአዊነቷ ጥልቀት ድረስ ሴት ናት። አንድ ወንድ ደግሞ እስከ ሰብአዊነቱ ጥልቀት ድረስ ወንድ ነው። እናም ይሄ ትልቅ ነገር ነው። ስለዚህ የመጀመሪያ ነጥቤ እግዚአብሔር በመልኩ እኛን ወንድና ሴት በማድረጉ ታላቅ ሥራ ሠርቷል። ይህን አታሳንሱ። ይልቅ በዚህ ደስ ይበላችሁ። እንደ ወንድ ወይም ሴት፣ ሰው ሆናችሁ በሕይወት በመኖራችሁ ክብርን ስጡ።

የልዩነቶች ምሳሌ

በወንድነት እና በሴትነት መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት አንድ ምሳሌ ልፍጠር። አንድ ምሳሌ የሺህ ቃላት ዋጋ ሊኖረው ይችላል፤ ምስል ከሳች ቃልም እንዲሁ ነው።

ከተማ ውስጥ ባለ ቤተ ክርስቲያን፣ 20ዎቹ አካባቢ ያሉ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ከአምልኮ በፊት ሲነጋገሩ ራሳቸውን አገኙ ብላችሁ አስቡ። በሁኔታዋ ተማርኮ፣ “ከአጠገብሽ የሚቀመጥ ሰው አለ?” ብሎ ጠየቃት እና አብሯት ተቀመጠ። እንዴት በአምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚገናኙ እርስ በርስ እየተያዩ ነበር።

አገልግሎቱ አለቀ፤ ለመሄድ እየተዘጋጁ፣ “ምሳ ትበያለሽ? ምሳ ብጋብዝሽ ደስ ይለኛል” አላት። በዚህ ጊዜ ፍላጎት እንደሌላት ለማሳየት “አንዳንድ ዕቅዶች አሉኝ፤ ግን አመሰግናለሁ” ብላ ምልክት መስጠት ትችላለች። ወይም በተቃራኒው “አዎ አለኝ፤ ግን ቆይ ልደውል። ዕቅዴን መቀየር የምችል ይመስለኛል። አብረን ጊዜ ብናሳልፍ ደስ ይለኛል” ብላ ምልክት መስጠት ትችላለች። በመጨረሻም መሄዱን መረጠች።

ሁለቱም መኪና ስለሌላቸው፣ በእግር ከቤተ ክርስቲያኑ 10 ደቂቃ ያህል ወደሚያስኬድ አንድ ካፌ እንዲሄዱ ሐሳብ አቀረበ። አብረው እየተራመዱ በማርሻል አርት ጥቁር ቀበቶ እንዳላት አወቀ፤ በአካባቢዋ ምርጥ ከሚባሉት መካከል እንደሆነችም ተረዳ። ወደ ካፌው ሲቃረቡ፣ ሁለት ሰዎች በድንገት መንገዳቸውን ዘግተው እንዲህ አሉት፦ “ቆንጅዬ ልጅ ናት። ቦርሳዋን እና የኪስ ቦርሳህን አምጣ! እንዲያውም በጣም ቆንጆ ስለ ሆነች፣ እርሷንም እንፈልጋለን።”

“እነዚህንማ አሳራቸውን ልታበላቸው ትችላለች” የሚለው ሐሳብ በምናቡ ብቅ አለ። ነገር ግን ከኋላዋ ከመሄድ ይልቅ እጇን ይዞ ወደ ኋላ ጎተታትና፣ “እርሷን የምትነኳት በእኔ ላይ ተረማምዳቹህ ነው” አለ። ልክ ሲጠጉ ሁለቱንም ጠለፋቸውና እንድትሮጥ ነገራት።

ራሱን እስኪስት ድረስ መቱት፤ ግን ሁለቱም ምን እንደ መታቸው ሳያውቁ፣ የተወሰኑ ጥርሶቻቸውን አወላልቃ በጀርባ አጋደመቻቸው። በዚህ ጊዜ ሰው ተሰበሰበ፤ አንድ ሰው ደግሞ ወደ ፖሊስ ደወለ። ፖሊስና አምቡላንስ ሲመጣ፣ ወደ አእምሮው እየተመለሰ ካለው ወጣት ጋር ወደ አምቡላንሱ ገባች። ወደ ሆስፒታሉ እየሄዱ መንገድ ላይ፣ “ይህ ማግባት የምፈልገው ዐይነት ወንድ ነው” ብላ አሰበች።

የዚህ ትረካ ዋናው ቁም ነገር፣ የወንድነት እና የሴትነት ጥልቅ ልዩነት፣ የበላይ ወይም የበታች የሚያደርጉ ብቃቶች እንዳልሆኑ ለማሳየት ነው። ይልቁንም፣ በልብ ላይ የተጻፉ ጥልቅ ዝንባሌዎች ወይም ፍላጎቶች ናቸው (ምንም እንኳ አብዛኛውን ጊዜ በኀጢአት እና በውድቀት ምክንያት የተዛባ ነገር ቢኖርም)። ሦስት ወሳኝ ነገሮችን ግን አስተውሉ።

በመጀመሪያ ተነሣሽነቱን የወሰደው እርሱ ነው። አብሯት መቀመጥ ይችል እንደ ሆነ ጠየቀ፤ ወደ ምሳ መሄድ ትፈልግ እንደ ሆነ ጠየቀ። ቦታውን እና እንዴት መድረስ እንዳለባቸው ሐሳብ አቀረበ። እያደረገ ያለውን በሚገባ ተረድታ፣ እንደ ፍላጎቷ በነፃነት ምላሽ ሰጠች። እሺ አለች። ይህ ማን የተሻለ የማቀድ ብቃት እንዳለው አይናገርም። እግዚአብሔር በአንድ ወንድ ልብ ውስጥ የመምራትን መነሣሣት ሲያስቀምጥ፣ በሴቷ ልብ ውስጥ ደግሞ ነገሩን አጥርታ የምትለይበትን ጥበብ ይጽፋል።

ሁለተኛ፣ እርሷን ምሳ ለመጋበዝ እንደሚፈልግ ተናግሯል፦ የሚከፍለው እርሱ ነው። እንዲህ የሚል ምልክት እየሰጣት ይመስላል፦ “ይህ የእኔ ኀላፊነት ነው። በዚህች ትንሽ የሕይወት ድራማ ውስጥ የማነሣሣት ድርሻ የእኔ ነው፤ የማቅረብ ድርሻም የእኔ ነው።” እርሷም ገብቷታል፤ እናም ተቀበለችው። የእርሱን አነሣሽነት ደገፈችው፤ የቀረበላትንም ግብዣ በደስታ ተቀበለች። በሂደቱ ውስጥ ቀጣዩን እርምጃ ወሰደች። ይሄም ማን የበለጠ ሀብታም ወይም የበለጠ ገቢ ማግኘት እንደሚችል ምንም አይናገርም። ይህ የእግዚአብሔር ወንድ የግድ ማድረግ እንዳለበት የሚያስበው ነገር ነው።

ሦስተኛ፣ እነዚያን አጥቂዎች ሲጋፈጡ፣ ራሷን በመከላከል ረገድ የተሻለች መሆኗን ከወንድነቱ ጋር አላያያዘውም። በጊዜው ወዲያው የታየው፣ እግዚአብሔር የሰጠውና ጥልቅ የሆነው እርሷን የመጠበቅ የወንድነት ስሜት ነው። በርግጠኝነት የእርሱ ችሎታ የላቀ አልነበረም፤ የማይረባ የወንድነት ኩራትም አልነበረም። ጉዳዩ የወንድነት ነበር። አይታዋለች። ታዲያ እንደ ተናቀች ሳይሆን እንደ ተከበረች ተሰማት። ወደደችውም።

መሪነትን፣ አነሣሽነትን፣ መመገብን እና ከለላ መሆንን በተመለከተ በበሳል ወንድነት ውስጥ እግዚአብሔር የሰጠው መነሣሣትና ዝንባሌ አለ። እንዲህ የማድረግ ቀዳሚ ኀላፊነት (የብቻው ኀላፊነት ባይሆንም) የወንዱ ነው።

በበሳል ሴትነት ውስጥ ደግሞ ከእንዲህ ዐይነቱ ሰው ጎን መቆምና ይህን የመሰለ አመራር፣ አቅርቦት እና ከለላን በደስታ የማጽናትና የመቀበል ከእግዚአብሔር የተሰጠ ዝንባሌ አለ፤ ከእነዚህ አንዳቸውም ቢሆኑ የእርሷን ዝቅተኛነት አያመለክቱም።

በእነዚህ ልዩነቶች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ እይታ

ይህንን የ“ኮምፕልመንተሪያን” አመለካከት በመቃወም ሊሰነዘር የሚችለው ትችት፣ እኔ ተፈጥሯዊ አድርጌ ያቀረብኳቸውን የፆታ ልዩነቶች ሁሉ ከባህል የተወረሱ እንጂ፣ ከሰው ጋር አብረው ያልተፈጠሩና ከእግዚአብሔር ያልሆኑ ልዩነቶች ናቸው የሚል ነው። “ኮምፕልመንታሪያን” ያደጉበትን ቤትና የልጅነት ወቅት የገጠማቸውን አድሎአዊነት የሚያንፀባርቁ ናቸው ይላሉ።

ይህ እውነት ሊሆን ይችላል። ሁሉም ሰው በዚህ ጉዳይ ግምቶችንና አማራጮችን ያቀርባል። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ፣ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ነገሮች ያለውን ፈቃድ በቃሉ ገልጧል ወይ? የሚለው ነው።

አስቀድመን ስለ ጋብቻ የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክፍል እንመልከት፤ ከዚያም ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚናገረውን ደግሞ እንመለከታለን። በሁለቱም ክፍሎች ክርስቶስን የሚመስሉ፣ ትሑት፣ አፍቃሪ፣ መሥዋዕት የሚሆኑ ወንዶች፦ ለመሪነት፣ ለአቅርቦት፣ እና ለከለላ ቀዳሚ ኀላፊነት እንዲወስዱ ተጠርተዋል። ሴቶች ደግሞ ከእነዚህ ወንዶች ጎን እንዲቆሙ፣ ያንን አመራር እንዲደግፉና በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተዘረዘሩት ስጦታዎቻቸው የክርስቶስን መንግሥት እንዲያሰፉ ተጠርተዋል።

የመጀመሪያው፣ ስለ ጋብቻና ስለ ቤት አስተዳደር የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ነው፦

ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ። ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጒድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና። (ከዚያም ጳውሎስ ዘፍጥረት 2፥24ን ይጠቅሳል) “ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር። (ኤፌሶን 5፥22–33)

ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተወሰዱ አራት ምልከታዎችን እነሆ፦

1. ጋብቻ ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ትዕይንት ነው። “ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ” (ቁ. 32)።

2. በዚህ ትዕይንት ውስጥ ባል ምሪትን ከክርስቶስ ይወስዳል፤ ሚስት ደግሞ ምሪትን ለቤተ ክርስቲያን ከሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ትወስዳለች። “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” (ቁ. 25)። “ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ። ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና” (ቁ. 22)።

3. ስለዚህ በቤት ውስጥ መሪነትን ራስ ከሆነው ከክርስቶስ የመውሰድ ቀዳሚ ኀላፊነት የባል ነው። እናም ይህ ስለ ኀላፊነትና ስለ መሥዋዕትነት እንጂ፣ ስለ መብትና ኀይል እንዳይደለ ግልጽ ነው፦ “ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ” ይላልና (ቁ. 25)። ጭቆና የለም። አጉል አለቅነት የለም። አምባገነንነት የለም። እብሪተኝነት የለም። በአዳኙ ፈቃድ ኩራቱ የተሰበረ፣ ደግሞም ሸክሙ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ከጌታው የተሰጠውን የመሪነት ሸክም ለመሸከም ፈቃደኛ የሆነ፣ አንድ ወንድ አለ። ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሴቶች ደግሞ ይህንን በደንብ ያያሉ፤ ደስታቸውም በዚህ ዐይነቱ ወንድ ውስጥ ይገኛል።

4. ይህ በቤት ውስጥ ያለ መሪነት ለመጋቢነት፣ ለአቅርቦትና ጥንቃቄ ለተሞላው ጥበቃ ቀዳሚውን ኀላፊነት መውሰድ ያካትታል። “የገዛ ሥጋውን (ሚስቱን ማለት ነው) የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው” (ቁ. 29)። ይመግበዋል የሚለው ቃል የምግብ አቅርቦትን ያመለክታል። ይንከባከበዋል የሚለው ቃል ደግሞ ጥንቃቄ የተሞላው ጥበቃን ያመለክታል። ክርስቶስ ለሙሽሪት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ባል ለሚስቱ እና ለቤተ ሰቡ ማድረግ የሚገባው ቀዳሚ ኀላፊነት ይህ እንደሆነ ያስባል።

ስለዚህ “ኮምፕልመንተሪያን” ለባል የሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ራስነት፣ የክርስቶስ ዐይነት አገልጋይ መሪነት፣ ጥበቃ እና ለቤት ውስጥ አቅርቦት ዋነኛውን ኀላፊነት የመውሰድ መለኮታዊ ጥሪ እንደሆነ ይደመድማሉ። ለሚስት ደግሞ የባሏን አመራር ለማክበርና ለማጽናት፣ በተጨማሪም በእርሷ ስጦታዎች መሠረት እንዲታገዝ ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መገዛት መለኮታዊ ጥሪዋ ነው። ዘፍጥረት 2፥18 “የሚስማማው ረዳት” እንደሚል ማለት ነው።

ይህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳምኑ ምክንያቶችን አሁን አላቀርብም። ይልቁንም “ኮምፕልመንታሪያን” እንዴት እንደሚያዩት የተወሰኑ ማጠቃለያ አስተያየቶችን ብቻ አሳያለሁ።

1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥12 ላይ ጳውሎስ፣ “ሴት ዝም አንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም” ይላል። በሰፊው የመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋናው የማስተዳደርና የማስተማር ኀላፊነት በመንፈሳዊ ወንድ አገልጋዮች መከወን አለበት ለማለት እንደሆነ እንገነዘባለን። ሽማግሌዎችን ከዲያቆናት የሚለዩት እነዚህ ሁለት ተግባራት ናቸው፤ እነርሱም አስተዳደር እና ማስተማር (1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥171ኛ ጢሞቴዎስ 3፥2)። ስለዚህ በጣም ግልጽ የሆነውን ይሄን ጠቅላይ ትምህርት ተግባራዊ የምናደርገው፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ወንድ አገልጋዮች መሆን አለባቸው በማለት ነው።

በሌላ አነጋገር፣ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ ስለሆነች፣ በጋብቻ ውስጥ ያየነው የራስነት እና የመገዛት እውነታዎች በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ አቻዎች አሏቸው (ኤፌሶን 5፥22-33)። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥12 ሥልጣን የሚያመለክተው፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስ ዐይነት አገልጋይ-መሪነት እና የማስተማር ዋና ኀላፊነት የመንፈሳዊያን ደግሞም መንፈሳዊ ስጦታ ያላቸው የወንድ አገልጋዮች መለኮታዊ ጥሪ እንደ ሆነ ነው። በኤፌሶን 5 ላይ ደግሞ ተገዙ የሚለው የሚያመለክተው፣ ለተቀረው የቤተ ክርስቲያን ኀብረት፣ ወንዶች ሆኑ ሴቶች፣ የሽማግሌዎችን አመራር እና ትምህርት በማክበርና በማጽናት ለክርስቶስ እንዲገዙ ነው። ይህም ክርስቶስን በማገልገል ውስጥ ወንዶች እና ሴቶች፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የአገልግሎት ዐይነቶች ይታጠቁ ዘንድ ነው።

ይህ የመጨረሻው ነጥብ በጣም አስፈላጊ ነው። ነፍሳትን ለማዳን፣ የተሰበረ ሕይወትን ለመጠገን፣ ክፋትን ለመቃወምና ችግረኞችን ለመርዳት፣ በአጭሩ የአገልጋይነት ልብ ላላቸው ወንዶች እና ሴቶች የአገልግሎት መስኮች ማለቂያ የላቸውም። እግዚአብሔር መላው ቤተ ክርስቲያን፣ ወንድም ሆነ ሴት በአገልግሎት እንዲተጉ ይፈልጋል። ማንም ቢሆን ዓለም እየነደደች፣ ተከታታይ የቲቪ ድራማና የኳስ ጨዋታዎችን በመመልከት ቤት ውስጥ ዝም ብሎ አይቀመጥም።

መጽሐፍ ቅዱሳዊው የወንድነት እና የሴትነት ምስል፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ወንድ መሆን፣ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረች ሴት ከመሆን ጋር እኩል የከበሩ ነገሮች መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ለወንዶች እና ለሴቶች የቀረበ ጥሪ ነው። ነገር ግን ቀዳሚ የመሆን ኀላፊነቱና ሸክሙ ወንዶች ላይ ስለ ሆነ እነርሱን ይበልጥ እጫናቸዋለሁ።

ወንዶች ሆይ! ለቤተ ሰቦቻችሁ የግብረ ገብ ዕይታ፣ ለእግዚአብሔር ቤት ቅንዓት፣ ለመንግሥቱ እድገት የሆነ ታላቅ መሰጠት፣ ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ግልጽ የሆነ ሕልም እና እርሱን እውን ለማድረግ ያለ ልባዊ ጽናት አላችሁን? አለበለዚያ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረችን ሴት መምራት አትችሉም። እርሷ የከበረች ፍጡር ናት!

ዛሬ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንደዚህ ያሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን ሌሎች ብዙዎች ያስፈልጋሉ። ጌታ ቤተ ክርስቲያኑን ሲጎበኝና ከልባቸው መንፈሳዊ የሆኑ፣ ትሑት፣ ጠንካራ፣ ለእግዚአብሔር ቃልና ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የተሰጡ፣ ክርስቶስን የሚመስሉ ታላላቅ የወንዶች ሠራዊትን ሲፈጥር፣ ሰፊው የሴቶች ሠራዊት በእነዚህ ወንዶች መሪነት ይደሰታል፤ ለአስደሳች አጋርነትም እጁን ይሰጣል። ይሄም የከበረ ነገር ይሆናል።

ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንድነትና ሴትነት

ግጭት እና ግራ መጋባት፣ ከውድቀት በኋላ

እግዚአብሔር በአምሳሉ ወንድ እና ሴት አድርጎ የመፍጠሩ እውነታ ስድስት አስፈላጊ ነገሮችን ይጠቁማል፦ የስብዕና እኩልነትን፣ የክብር እኩልነትን፣ የጋራ መከባበርን፣ ተናባቢነትን፣ “ኮምፕልመንታሪ”ን እና የጋራ ዕጣ ፈንታን። ለእያንዳንዳቸው ማብራሪያ ልስጥ።

የስብእና እኩልነት

የስብዕና እኩልነት ማለት፣ አንድ ወንድ እንደ ጎሬላ ደረቱ ላይ ፀጉር ስላለው ከሴት ይልቅ ያነሰ ሰው አይደለም፤ አንድ ሴትም እንደ ዓሣ ደረቷ ላይ ፀጉር ስለሌላት ያነሰች ሰው አይደለችም ማለት ነው። በስብዕናቸው እኩል ናቸው፤ ልዩነቶቻቸውም ቢሆኑ ያንን መሠረታዊ እውነት አይለውጡም።

የክብር እኩልነት

የክብር እኩልነት ማለት በእግዚአብሔር መልክ እንዳሉ ሰዎች እኩል መከበር አለባቸው ማለት ነው። ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦ “ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥17)። ሰዎች ሰው ስለሆኑ ብቻ የሚሰጣቸው ክብር አለ። አረመኔዎች ቢሆኑ እንኳ ሰው ስለሆኑ ብቻ ለክፉ ወንጀለኞችም መስጠት የሚገባን ክብር አለ። እናም ያ ክብር ለወንድም ሆነ ለሴት እኩል የተገባ ነው።

የጋራ መከባበር

የጋራ መከባበር ሲባል ወንዶች እና ሴቶች እርስ በርስ ለመከባበር እኩል ቀናዒ መሆን አለባቸው ማለት ነው። አክብሮት ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ መፍሰስ የለበትም። በእግዚአብሔር መልክ እንደተፈጠሩ ወንድና ሴት እርስ በርስ በአክብሮታዊ ፍርሀት መተያየት አለባቸው። ይህም በኀጢአት በተበላሸው ነገር ግን ፈጽሞ ባልጠፋው ክቡርነት ማለት ነው።

ተናባቢነት

ተናባቢነት ማለት በወንዶችና በሴቶች መካከል ሰላማዊ ትብብር ሊኖር ይገባል ማለት ነው። የጋራ ሥራ፣ መግባባት፣ የጋራ መረዳዳትና ደስታ ይኖር ዘንድ የግንኙነታችንን ማርሾች ዘይት የምንቀባበት መንገዶች መፈለግ አለብን።

“ኮምፕልመንታሪ”

“ኮምፕልመንታሪ” ማለት፣ የግንኙነታችን ሙዚቃ አንድ ዐይነት የመዝሙር ድምጽ ብቻ ሳይሆን፣ የተቀናጀና የተዋሐደ የሶፕራኖና የቤዝ የአልቶና የቴነር ድምጽ መሆን አለበት። ይህ ማለት የወንድ እና ሴት ልዩነቶች የተከበሩ፣ የተረጋገጡና ዋጋ የሚሰጣቸው ይሆናሉ ማለት ነው። ይህም ማለት ወንድ እና ሴት አንዳቸው በሌላኛው ውስጥ የራስን ቅጂ ለመፍጠር አይሞክሩም፤ ይልቅ ለጋራ ጥቅም የሚሆኗቸውን ልዩ ባሕርያት አንደኛው በሌላኛው ውስጥ ያንጸባርቃሉ ማለት ነው።

የጋራ ዕጣ ፈንታ

የጋራ ዕጣ ፈንታ ማለት፣ ወንድ እና ሴት በክርስቶስ በኩል ወዳለ እምነት ሲመጡ፣ “የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ የሚወርሱ” ናቸው ማለት ነው (1ኛ ጴጥሮስ 3፥7)። በሚመጣው ዘመን በእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ለእኩል ደስታ ተዘጋጅተናል።

እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በመፍጠሩ ውስጥ አንዳች አስደናቂ ነገር በሐሳቡ ነበር። አሁንም በሐሳቡ አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ ይህን ራእይ ከኀጢአት ጥፋት ለመዋጀት ያበጀው መንገድ ነው።

እርግማኑን መረዳት

በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ግጭት ምን እንደ ሆነ እና ዛሬ ወንድ ወይም ሴት መሆን ምን ማለት እንደ ሆነ ስላለው ግራ መጋባት እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ።

ዘፍጥረት 3፥16ን እንመልከት። አዳምና ሔዋን ሁለቱም በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠሩ። ቸርነቱን ባለማመን በራሳቸው ጥበብ ደስተኛ ለመሆን ከእርሱ ዘወር አሉ። ስለዚህ ቃሉን ንቀው መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ ፍሬ በሉ። እግዚአብሔርም ወደ ተጠያቂነት አምጥቶ፣ በኀጢአት ምክንያት በሰው ሕይወት ላይ የሚመጣውን እርግማን ገለጸላቸው። እግዚአብሔር ለሴቲቱ፣ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል” አላት (ዘፍጥረት 3፥16)።

ይህ የእርግማኑ መግለጫ ነው። የመከራው መግለጫ ነው እንጂ ለትዳር ምሳሌ አይደለም። እግዚአብሔር ኀጢአት የበላይ በሆነበት ታሪክ ውስጥ የሚሆነው እንዲህ ነው እያለ ነው። ነገር ግን እዚህ ጋር ትልቁ ነጥብ ምንድን ነው? ይህ ከኀጢአት በኋላ የተበላሸ ግንኙነት ተፈጥሮው ምንድን ነው?

ቁልፉ የሚመጣው በዘፍጥረት 3፥16 የመጨረሻዎቹ ቃላት እና በዘፍጥረት 4፥7 የመጨረሻዎቹ ቃላት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማወቅ ነው። በሁለተኛው ጥቅስ፣ እግዚአብሔር ቃየን በአቤል ላይ ስላለው መከፋትና ቁጣ አስጠንቅቆታል፤ እናም ኀጢአት በሕይወቱ የበላይ ሊሆን እንዳለ ነግሮታል። “ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።”

እዚህ በ3፥16 እና 4፥7 መካከል ያለው ንፅፅር በጣም የተቀራረበ መሆኑ አስደናቂ ነው። ቃላቱ በዕብራይስጥ አንድ ዐይነት ናቸው ማለት ይቻላል፤ እናንተ ግን ይህንን በአማርኛውም ማየት ትችላላችሁ። 3፥16 ላይ እግዚአብሔር ሴቲቱን፦ “ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል (ፍላጎትሽ ከባልሽ ጋር ይቃረናል)፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል” አላት። ዘፍጥረት 4፥7 ላይ እግዚአብሔር ለቃየን የኀጢአት ምኞት “ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት” አለው።

ይህን ማየት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ውስጥ ምኞት ምን ማለት እንደሆነ የበለጠ ያሳየናል። ዘፍጥረት 4፥7 ኀጢአት በቃየን ልብ ደጃፍ እንደ አንበሳ ታደባለች፣ ፍላጎቷም ከእርሱ ጋር ይቃረናል ሲል ኀጢአት ሊያሸንፈው ይፈልጋል ማለቱ ነው። እርሱን ማሸነፍና አስገዝቶ የኀጢአት ባሪያ ሊያደርገው ይፈልጋል።

አሁን ወደ 3፥16 ስንመለስ፣ በሴቶች የኀጢአት ምኞትም ውስጥ ምናልባት ተመሳሳይ ትርጉም ልናገኝ እንችላለን። “ፍላጎትሽ ከባልሽ ጋር ይቃረናል (ፍላጐትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል)” ሲል ኀጢአት በሴት ላይ የበላይነት ሲኖረው፣ ወንድን ለማሸነፍ ወይም ለመግዛት ወይም ለመበዝበዝ ትፈልጋለች ማለቱ ነው። ኀጢአትም በወንድ ላይ የበላይ ሆኖ ሲገኝ በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ ይሰጣል፤ በጉልበቱም ያስገዛታል ወይም የበላይ ይሆንባታል።

ስለዚህ በ3፥16 እርግማን ውስጥ የተገለጠው፣ አብዛኛው የሰው ልጅ ታሪክ የሚታወቅበት በወንድና በሴት መካከል ያለው አስቀያሚ ግጭት ነው። እግዚአብሔር የፈጠረው ወንድነት በኀጢአት ምክንያት ተበላሽቷል፤ ተበክሏል። እግዚአብሔር የፈጠረው ሴትነት በኀጢአት ምክንያት ተበላሽቷል፤ ተበክሏል። የኀጢአት ምንነት በራስ መደገፍ እና ራስን ከፍ ማድረግ ሲሆን፣ ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅና ከዚያም እርስ በርስ ባለ ብዝበዛ ነው። ኀጢአትም በወንድ ላይ የበላይ ሆኖ ሲገኝ በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ ይሰጣል፤ በጉልበቱም ያስገዛታል ወይም የበላይ ይሆንባታል።

ስለዚህ የተበላሸው የወንድነት ምንነት፣ ለራስ የግል ፍላጎቶች ሴቶችን ለማንበርከክ፣ ለመቆጣጠርና ለመበዝበዝ የሚደረገው ራስን ከፍ የማድረግ ጥረት ነው። የተበላሸው ሴትነት ምንነት ደግሞ ለራሷ ጥቅም ስትል ወንድን ለማንበርከክ፣ ለመቆጣጠርና ለመበዝበዝ የሚደረገው ራስን ከፍ የማድረግ ጥረት ነው። ልዩነቱ ደግሞ በዋናነት እርስ በርሳችን በምንበዛበዝባቸው በተለያዩ ድክመቶች ውስጥ ይገኛል።

በመደበኛነት፣ ወንዶች ከሴቶች የበለጠ የሰውነት ጥንካሬ ወይም አቅም ስላላቸው መድፈር፣ ማጎሳቆል፣ ማስፈራራትና ዙሪያውን ተቀምጠው መልከፍ ይችላሉ። ዛሬ የዚህ ዐይነት ነገሮች መናገር የተለመደ ነው። ነገር ግን ሴቶችም ልክ እንደዚሁ ኀጢአተኞች መሆናቸውም እውነት ነው። እኛ በእግዚአብሔር መልክ ያለን ወንድና ሴት ነን። ኀጢአተኞች ወንድና ሴትም ነን። ሴቶች የወንዶችን ያህል የሰውነት ጥንካሬ ወይም አቅም ላይኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን ወንድን የምትገዛበት መንገድ ታውቃለች። ብዙ ጊዜ በንግግሯ ልታጠምደው ትችላለች። እና ንግግሯ ያልተሳካላት ከሆነ፣ የምኞቱንና የኩራቱን ድክመት መጠቀምን ታውቅበታለች።

ኀጢአተኛ ሴት ኀጢአተኛ ወንድን ለመቆጣጠር ስላላት ኀይል ጥርጣሬ ካደረባችሁ፣ በዓለም ላይ ያለውን ቁጥር አንድ የሽያጭ ገበያን ለአፍታ አስቡ። የሴቶች ምስል፣ በመላው ዓለም ላይ ያለን የወንዶችን ድክመት በመጠቀም፣ ማንኛውንም እና የትኛውንም ነገር ለወንዶች ለመሸጥ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እና እየዋለ ያለ ነገር ነው። እውነት ነው፤ የሴቶች በኀጢአተኛ ወንዶች መበዝበዝ ብዙውን ጊዜ ከባድና እና ኀይለኛ ከመሆኑ የተነሣ፣ ጎልቶ የሚታይ ነገር ነው። ነገር ግን በቀላል ዕይታ ወንዶችም በኀጢአተኛ ሴቶች መበዝበዛቸው በማኅበረሰባችን ውስጥ ተስፋፍቶ በጉልህ የሚታይ ነገር መሆኑን ማየት ይቻላል። ልዩነቱ የምዕራቡ ዓለም ማኅበረሰብ ኀጢአት በተሞላ መንገድ አንደኛው ጠማማነት ላይ ማዕቀብ ይጥላል፤ ሌላኛውን ግን ይፈቅዳል (አንዳንድ ማኅበረሰቦች ደግሞ ተቃራኒውን ያደርጋሉ)።

በአስደናቂ ውዝዋዜ ውስጥ ያሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች

ከኀጢአት በፊት፣ ወንድና ሴት ለመኖር ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ ጥገኛ በነበሩበት ጊዜ፣ እርሱ ያቀደው ዛሬ ያለውን ዐይነት የግንኙነት ዐይነት አልነበረም። ዛሬ በጾታዎቹ መካከል ያለው ውጥረት፣ በእግዚአብሔር ላይ የማመፅ ውጤት ነው። ታዲያ እግዚአብሔር የፈለገው እንዴት እንዲሆን ነበር? ኀጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱ በፊት በአዳምና በሔዋን መካከል ያለው ግንኙነትስ ምን ይመስል ነበር? የመልሱን የተወሰነ ክፍል አይተናል። በዘፍጥረት 1፥27 መሠረት በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረዋል፤ ስለዚህ የነበራቸው ግንኙነት በስብእና እኩልነት፣ በክብር እኩልነት፣ በጋራ መከባበር፣ በተናባቢነት፣ በ”ኮምፕልመንታሪ” እና በጋራ ዕጣ ፈንታ መመራት እንደነበረበት አይተናል።

ነገር ግን ያ የመልሱ የተወሰነ ክፍል ብቻ ነው።

አብረው ለሚወዛወዙ ወንድ እና ሴት ተወዛዋዦች እንዲህ እንደ ማለት ነው፦ “አስታውሱ! ሁለታችሁም በየፊናችሁ የተሳካላችሁ ተወዛዋዦች ናችሁ፤ ሌሎች በእኩል ደረጃ ነው የሚያዩአችሁ፤ ምርጥ አድርጋችሁ መፈለግ አለባችሁ፤ አንዳችሁ የሌላችሁን እንቅስቃሴ ማሟላት አለባችሁ፤  ጭብጨባውንም ደግሞ በጋራ እንደምትካፈሉት አትርሱ” እንደ ማለት ነው።

እንዲህ ዐይነቱ ምክር በጣም አስፈላጊ ነው፤ የውዝዋዜውን ውበት በጥልቀት የሚነካ ነው። ነገር ግን ሊያቀርቡት ስላሰቡት ውዝዋዜ የሚያውቁት ይህ ብቻ ከሆነ ሊያደርጉት አይችሉም። እንቅስቃሴዎቹን ማወቅ አለባቸው። የተለያዩ አቋቋማቸውን ማወቅ አለባቸው። ማን እንደሚወድቅ እና ማን እንደሚይዝ፣ ማን እንደሚሮጥ እና ማን እንደሚቆም ማወቅ አለባቸው። የውዝዋዜ እና የድራማ ዋና ይዘት ተጫዋቾቹ ማድረግ ያለባቸውን የተለያየ እንቅስቃሴ ማወቃቸው ነው።

በመድረክ ላይ የተለያዩ ኀላፊነታቸውን ካላወቁ፣ ድራማ አይኖርም፤ ዳንስም አይኖርም።