የዲያቆናት መጽሐፍ ቅዱሳዊ  መመዘኛዎች እና ኅላፊነቶች

ዲያቆን ሊሆን የሚገባው ማነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዲያቆናት ተግባር ምን ይላል?

ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቢሮዎች (አገልግሎቶች)፦ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት

የዲያቆናት የአገልግሎት ቢሮን ከሽማግሌዎች የአገልግሎት ቢሮ ጋር ማነጻጸር ከላይ ላነሣናቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይረዳናል። የአማኞች ጉባኤ ዋና መንፈሳዊ መሪዎች በአዲስ ኪዳን የበላይ ተመልካቾች ወይም መጋቢዎች ተብለው የሚጠሩት ሽማግሌዎች ናቸው። ሽማግሌዎች ቃሉን ያስተምራሉ ወይም ይሰብካሉ እናም በእጃቸው ያሉትን ነፍሳት ይጠብቃሉ (ኤፌሶን 4፥11፤ 1 ጢሞቴዎስ 3፥2፤ 5፥17፤ ቲቶ 1፥9፤ ዕብራውያን 13፥17)። ዲያቆናትም እንዲሁ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ጤና ላይ ወሳኝ ሚና አላቸው፤ ነገር ግን ሚናቸው ከሽማግሌዎች የተለየ ነው። የዲያቆናት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተግባር ሽማግሌዎች በቀዳሚ ጥሪያቸው ላይ እንዲያተኩሩ የቤተ ክርስቲያንን አካላዊ እና የሎጅስቲክስ ፍላጎት ማሟላት ነው።

ይህ ልዩነት በሐዋርያት ሥራ 6፥1-6 ባለው አብነት ላይ የተመሠረተ ነው። ሐዋርያት “ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል” የተሰጡ ነበሩ (ቁ. 4)። ይህ ተቀዳሚ ጥሪያቸው ስለነበር ሐዋርያት በሥራቸው እንዲተጉ ለማድረግ ሰባት ሰዎች ይበልጥ ተግባራዊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲሠሩ ተመርጠዋል።

ይህ የሥራ ክፍፍል በሽማግሌና በዲያቆን ቢሮ መካከል ከምናየው ጋር ተመሳሳይ ነው። ልክ እንደ ሐዋርያት፣ የሽማግሌዎች ዋና ተግባር የእግዚአብሔርን ቃል የመስበክ ነው። እንደ ሰባቱ ሁሉ ዲያቆናትም ጉባኤው በሚያስፈልገው በማንኛውም አቅጣጫ ያገለግላሉ።

የዲያቆን መመዘኛዎች

የዲያቆናት መመዘኛዎችን የሚጠቅስ ብቸኛው ክፍል 1ኛ ጢሞቴዎስ  3፥8-13 ነው። በዚህ ምንባብ ውስጥ ጳውሎስ ለዲያቆናት የሚያስፈልጉ ዋና መስፈርቶችን ቢሰጥም፣ እያንዳንዱን ዝርዝር ግን አላስቀመጠም።

በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ውስጥ የዲያቆናት እና የሽማግሌ (የበላይ ተመልካቾች) መመዘኛዎች ተመሳሳይነት በጣም አስደናቂ ነው። እንደ ሽማግሌዎች ሁሉ፣ ዲያቆን የማይሰክር (ቁ 3)፣ ገንዘብንም የማይወድ (ቁ 3)፣  የማይነቀፍ(ቁ 2፣ ቲቶ 1፥6)፣ የአንዲት ሚስት ባል(ቁ 3)፣ ልጆቹን ታዛዥና አክባሪ አድርጎ በማሳደግ የገዛ ቤተሰቡን በአግባቡ የሚያስተዳድር(ቁ 4-5)  ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም የመመዘኛዎቹ ትኩረት በአገልግሎቱ ላይ የሚሰማራው ሰዉ ሥነ ምግባር ነው። ዲያቆን በሳል እና ያለነቀፋ  መሆን አለበት። በሽማግሌ እና በዲያቆን መካከል ያለው ዋና ልዩነት የስጦታና የጥሪ ልዩነት እንጂ የባህርይ አይደለም።

ጳውሎስ ዘጠኝ የዲያቆናት መመዘኛዎችን በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥8-12 ገልጿል።

1.  የተከበሩ (ቁ. 8)፦ ይህ ቃል በተለምዶ የሚያመለክተው የተከበረ፣ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው  ወይም ክብር የተገባውን ነው። “በሥርዐት የሚኖር” ከሚለው የሽማግሌዎች መመዘኛ ጋር በቅርበት ይዛመዳል (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥2)።

2. ቃላቸውን የማይለዋውጡ (ቁ. 8)፦ ሁለት ምላስ ያላቸው ፣ ለተወሰኑ ሰዎች አንድ ነገር ሲናገሩ በኋላ ግን ለሌላ ሰዎች የተለየ ነገር ይናገራሉ፤ ወይም ደግሞ አንድ ነገር ይናገሩ እንጂ ትርጉሙ ሌላ ነው። እንደነዚህ ያሉት ሁለት ገጽታ ያላቸው እና ቅንነት የጎደላቸው ናቸው። ቃላቶቻቸው ሊታመኑ አይችሉም፤ ስለዚህም ተዓማኒነት ይጎድላቸዋል።

3. የማይሰክር (ቁ. 8)፦ አንድ ሰው የመጠጥ ሱሰኛ ከሆነ ከዲያቆን አገልግሎት ኅላፊነቱ ይነሣል።  እንዲህ ዓይነቱ ሰው ራስን መግዛት ይጎድለዋል፤ ሥነ ሥርዓትም የለውም።

4. ገንዘብን የማይወድ (ቁ. 8)፦ ሰው ገንዘብን የሚወድ ከሆነ ዲያቆን ለመሆን ብቁ አይሆንም ምክንያቱም ዲያቆናት ብዙ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን የገንዘብ ጉዳዮችን ስለሚይዙ ነው።

5. የእምነትንም ጥልቅ ምስጢር በንጹሕ ኅሊና መጠበቅ (ቁ. 9)፦ ዲያቆን “የእምነትንም ጥልቅ ምስጢር በንጹሕ ኅሊና መጠበቅ” እንዳለበት ጳውሎስ አመልክቷል። “የእምነት ጥልቅ ምሥጢር” የሚለው ሐረግ፣ ጳውሎስ ወንጌልን ለመግለፅ የተጠቀመበት አንዱ መንገድ ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16)። ስለዚህ ይህ አባባል የሚያመለክተው ዲያቆናት ሳይናወጡ እውነተኛውን ወንጌል አጥብቀው እንዲይዙ ነው። ሆኖም ይህ መመዘኛ የአንድ ሰው እምነት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፣ እምነት “በንጹሕ ሕሊና” መጠበቅ እንዳለበት የሚያሳስብም እንጂ። ስለዚህም የዲያቆን ባሕሪ ከእምነቱ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።

6. ነቀፋ የሌለበት (ቁ. 10)፦ ጳውሎስ ዲያቆናት “አስቀድመው ይፈተኑ፤ ከዚያም፣ አንዳች ነቀፋ ካልተገኘባቸው በዲቁና ያገልግሉ” በማለት ጽፏል (ቁ. 10)። “ነቀፋ የሌለበት” የአንድን ሰው ሁለገብ ባሕሪ የሚያመለክት አጠቃላይ ቃል ነው። ምንም እንኳ ጳውሎስ ምን ዓይነት ፈተና መካሄድ እንዳለበት ባይገልጽም ቢያንስ የእጩው የግል ታሪክ፣ በሰዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እና የነገረ መለኮት አቋሙ መፈተሽ አለበት። ከዚህም በላይ ማኅበረ ምዕመኑ የዲያቆንን ምግባራዊ፣ መንፈሳዊ እና የአስተምህሮ ብስለት መፈተሽ ብቻ ሳይሆን፣ ሰውየው በቤተ ክርስቲያን የነበረውን የአገልግሎት ታሪክ ማጤን ይኖርበታል።

7. እግዚአብሔርን የምትፈራ ሚስት (ሴቶችም የተከበሩ) (ቁ. 11)፦ ቁጥር 11 የሚያመለክተው የዲያቆን ሚስትን ወይም ሴት ዲያቆንን ስለመሆኑ አከራካሪ ነው። ለዚህ ውይይት ስንል ጥቅሱ የሚናገረው ስለ ዲያቆን ሚስት መመዘኛ ነው ብለን እንወስዳለን። ጳውሎስ እንደተናገረው የዲያቆናት ሚስቶች “ሐሜተኞች ያልሆኑ ነገር ግን ልከኞችና በነገር ሁሉ የታመኑ” (ቁ. 11) ሊሆኑ ይገባል። ሚስትም ልክ እንደ ባሏ የተከበረች መሆን አለባት። በሁለተኛ ደረጃ እርሷ ስም አጥፊ ወይም ሐሜተኛ መሆን የለባትም። የዲያቆን ሚስትም እንደ ባሏ ሁሉ ጨዋ ወይም ልከኛ ልትሆን ይገባል። ይህ ማለት ጥሩ ውሳኔ መወሰን የምትችል እና እንዲህ ያለውን ትክክለኛ ውሳኔ ሊያደናቅፉ በሚችሉ ነገሮች የማትሳተፍ መሆን አለባት። በመጨረሻም “በነገር ሁሉ” የታመነች መሆን አለባት (1ኛ ጢሞቴዎስ 5፥10) ። ይህ መስፈርት ሽማግሌዎች “ነቀፋ የሌለበት” እንዲሆኑ ከሚያዝዘው መመዘኛ ጋር (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥2፤ ቲቶ 1፥6) እና  ዲያቆናት “ነውር የሌላቸው” (አንዳች ነቀፋ ካልተገኘባቸው) እንዲሆኑ (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥10) ከሚያዘው አጠቃላይ መስፈርት ጋር ተመሳሳይ ነው።

8. የአንዲት ሚስት ባል (ቁ. 12)፦ የዚህ አስቸጋሪ ሐረግ የተሻለ ትርጉም ባል ለሚስቱ ያለውን ታማኝነት እንደሚያመለክት መረዳት ነው። ባል “የአንድ ሴት ወንድ” ሊሆን ይገባዋል። ይህም ማለት በሕይወቱ ውስጥ በስሜትም ሆነ በአካል ከእርሱ ጋር ትስስር ያላት ሌላ ሴት መኖር የለባትም ።

9. ልጆቻቸውንና ቤተ ሰቦቻቸውን በአግባቡ የሚያስተዳድሩ (ቁ. 12)፦ ዲያቆን የሚስቱ እና የልጆቹ መንፈሳዊ መሪ መሆን አለበት።

የሞራል መመዘኛ ለሽማግሌዎች ተዘርዝሮ ግን ለዲያቆናት ባይዘረዘር፣ ራሱ መመዘኛ ለዲያቆናትም ይሠራል። ለዲያቆናት የተዘረዘሩት መመዘኛዎችም እንደዚያው ለሽማግሌዎች ያገለግላሉ። ለምሳሌ፦ ዲያቆን ቃሉን መለዋወጥ የለበትም (ቁ. 8)። ጳውሎስ ስለ ሽማግሌዎች ይህን በግልጽ አልተናገረም፤ ነገር ግን ሽማግሌዎችንም እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ጳውሎስ ሽማግሌ “ነቀፋ የሌለበት” መሆን አለበት ብሎ ስለተናገረ ይህን መስፈርትም ያካትታል።

ይህም ሆኖ በመሥፈርቶቹ መካከል ያለዉን ልዩነት በአትኩሮት ልንከታተል ይገባል። ምክንያቱም አገልግሎቱን ለመከወን የሚስማማውን ልዩ ባሕርይ እና ኅላፊነት ለመወጣት ብቁነቱን ወይም ጳውሎስ በጻፈበት ቦታ ላይ ያለውን ችግር የሚጠቁም ነው (በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ኤፌሶን)። የዲያቆንን ኅላፊነቶች ከማንሣታችን በፊት ይህ የበለጠ ግልጽ መሆን አለበት።

የዲያቆን ኃላፊነቶች

በአሁኗ ቤተ ክርስቲያን የሽማግሌዎች አገልግሎት ብዙ ጊዜ ችላ ይባላል። የዲያቆን ቢሮ ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ሰዎች ይረዱታል። በአዲስ ኪዳን መሠረት የዲያቆኑ ተግባር በዋናነት አገልጋይ መሆን ነው። ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ቃል እና በጸሎት ላይ እንዲያተኩሩ የቤተ ክርስቲያን የሎጂስቲክስና የቁሳቁስ ፍላጎትን እንዲያሟሉ ዲያቆናት ያስፈልጋሉ።

አዲስ ኪዳን ስለ ዲያቆናት ሚና ብዙ መረጃ አይሰጥም። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥8-12 የተሰጡት መስፈርቶች የሚያተኩሩት በዲያቆኑ ባሕሪ እና በቤተሰብ ሕይወት ላይ ነው። ነገር ግን የዲያቆናት መሥፈርቶች ከሽማግሌዎች ጋር ሲነጻጸሩ ስለሚሠሩት ተግባር አንዳንድ ፍንጮች ይሰጡናል። ምንም እንኳን ብዙዎቹ መመዘኛዎች አንድ ዐይነት ወይም በጣም ተመሳሳይ ቢሆኑም፣ አንዳንድ ጉልህ ልዩነቶች ግን አሉ።

በሽማግሌዎች እና በዲያቆናት መካከል በጣም የሚታወቀው ልዩነት ምናልባት ዲያቆናት “ማስተማር መቻል” የማይጠበቅባቸው መሆናቸው ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ  3፥2)። ዲያቆናት በንጹሕ ሕሊና ሃይማኖትን እንዲጠብቁ ተጠርተዋል ነገር ግን እምነትን እንዲያስተምሩ አልተጠሩም (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥9)። ይህ የሚያሳየው ዲያቆናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይፋዊ የማስተማር ሥራ እንደሌላቸው ነው።

እንደ ሽማግሌዎች ሁሉ ዲያቆናትም ቤታቸውን እና ልጆቻቸውን በሚገባ ማስተዳደር አለባቸው (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥4፣ 12)። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ ዲያቆናት ሲጠቅስ ቤትን ማስተዳደር የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከመንከባከብ ጋር የሚያወዳድረውን ክፍል ትቶታል (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥5)። ክፍሉን የመተው ምክንያት ምናልባት ዲያቆናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመግዛት ወይም የመሪነት ቦታ ስላልተሰጣቸው እና ይህ ተግባር የሽማግሌዎች ብቻ ስለሆነ ነው።

ጳውሎስ አንድ ሰው የዲያቆን አገልግሎት ከመያዙ በፊት መፈተን እንዳለበት ቢገልጽም (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥10) አዲስ ክርስቲያን ያልሆነ የሚለውን መስፈርት ግን አላካተተም። ጳውሎስ አንድ ሽማግሌ በቅርቡ ወደ ክርስትና የመጣ የከሆነ “በትዕቢት ተነፍቶ” ዲያቢሎስ በወደቀበት ፍርድ ሊወድቅ እንደሚችል ተናግሯል (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥6)። ይህንን ልዩነት በተመለከተ ያለው አንድ አንድምታ የሽማግሌነት ቦታን የሚይዙ በቤተ ክርስቲያን ላይ አመራር ስለሆኑ ለትዕቢት የሚጋለጡ መሆናቸው ነው። በተቃራኒው ግን በአገልጋይነት ቦታ ያለው ዲያቆን በዚሁ ኃጢአት ውስጥ የመግባት ዕድሉ አናሳ ነው። በመጨረሻም “የበላይ ተመልካች” (ኤጲስቆጶስ) የሚለው የማዕረግ ስም (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥2) የጉባኤውን መንፈሳዊ ደኅንነት በተመለከተ አጠቃላይ ቁጥጥርን የሚያመለክት ሲሆን “ዲያቆን” የሚለው የማዕረግ ስም ግን በሎሌነት ላይ ያተኮረ አገልግሎት ያለውን ሰው ያመለክታል።

ከእነዚህ መመዘኛ ልዩነቶች ከምናገኘው ሐሳብ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ የዲያቆናትን ተግባር በግልጽ አይናገርም። ነገር ግን በሐዋርያት ሥራ 6 ላይ ከሐዋርያት እና ከሰባቱ ጋር ተያይዞ ከሰፈረው አብነት ላይ በመመሥረት፣ ዲያቆናትን ሽማግሌዎች ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማስተማር ጥሪ እንዲፈጽሙ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርጉ አገልጋዮች ናቸው ብሎ መረዳት የተሻለ ይሆናል። ሐዋርያት አስተዳደራዊ ኃላፊነቶችን ለሰባቱ እንደሰጡ ሁሉ፣ ሽማግሌዎችም ጥረታቸውን በሌላ ቦታ እንዲያተኩሩ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ለዲያቆናት አሳልፈው መስጠት አለባቸው። በመሆኑም እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የዲያቆናትን ተግባር ከፍላጎታቸው በመነሳት የመግለጽ ነፃነት አለው።

ዛሬ ዲያቆናት ምን ዐይነት ኅላፊነት ሊኖራቸው ይችላል? ቤተ ክርስቲያንን ከማስተማር እና ከእረኝነት ጋር ያልተገናኘ ማንኛውም ነገር ላይ ኅላፊነት ሊወስዱ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉ ተግባራት የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፦

  • መገልገያዎች፦ ዲያቆናት የቤተክርስቲያኑን ንብረት የማስተዳደር ኅላፊነት አለባቸው። ይህም የአምልኮ ቦታው ለአምልኮው መዘጋጀቱን ማረጋገጥ፣ ማፅዳትን ወይም የድምጽ ሥርዓቱን ማስኬድን ይጨምራል።
  • በጎነት፦ በሐዋርያት ሥራ 6፥1-6 በየዕለቱ ለመበለቶች ከሚደረገው ስርጭት ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ዲያቆናት ለችግረኞች የሚሆንን ገንዘብ ወይም ሌላ እርዳታ ማስተዳደር ላይ ሊሳተፉ ይችላሉ።
  • ገንዘብ ነክ፦ ሽማግሌዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ነክ ጉዳዮች በበላይነት ሊቆጣጠሩት ቢገባቸውም (የሐዋርያት ሥራ 11፥30) የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን እንዲቆጣጠሩ ለዲያቆናት ቢተው ጥሩ ይሆናል። ይህም መባውን መሰብሰብ እና መቁጠርን፣ መዝገቦችን መያዝ እና የመሳሰሉትን ይጨምራል።
  • አስተናጋጆች፦ ዲያቆናት ማስታወቂያዎችን የመናገር፣ ማኅበረ ምዕመን መቀመጫ፣ ወይም የኅብረት ክፍሎችን የማዘጋጀት ኃላፊነት አለባቸው።
  • ሎጂስቲክስ፦ ሽማግሌዎች ቤተ ክርስቲያንን በማስተማርና በመጠበቅ ላይ እንዲያተኩሩ ዲያቆናት በተለያዩ መንገዶች ሊረዱ ይገባል።

ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎችን የማስተማር እና ቤተ ክርስቲያንን የመምራት ኃላፊነት ቢሰጣቸውም፣ የዲያቆናት ሚና የበለጠ አገልግሎትን ያማከለ ነው። ይኸውም የቤተ ክርስቲያንን አካላዊ ወይም ጊዜያዊ ጉዳዮችን ማስተዳደር አለባቸው። ዲያቆናት እነዚህን ጉዳዮች በማስተናገድ የጉባኤውን መንፈሳዊ ፍላጎቶች በመጠበቅ ላይ እንዲያተኩሩ ሽማግሌዎችን ነፃ ያደርጓቸዋል።

ነገር ግን ምንም እንኳን ዲያቆናት የጉባኤው መንፈሳዊ መሪዎች ባይሆኑም ባሕሪያቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ነው ዲያቆናት በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ላይ በተገለጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመዘኛዎች ላይ ተመርምረው መቅረብ ያለባቸው።

በቢንያም መርክል