ለመመለስ የተጠሩ | ጥር 29

እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን። (ሰቆቃወ 5፥21)

እግዚአብሔር ራሱ፣ ሕዝቡን ከኃጢአትና ካለማመን ካልመለሰ፣ የመመለስ ምንም ተስፋ የላቸውም።

የሰቆቃወ ኤርምያስ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ጨለማ የሆነው መጽሐፍ ነው። ራሱ እግዚአብሔር የዓይኑ ብሌን የሆነችውን እስራኤልን፣ ኢየሩሳሌምን አጥፍቷት ነበር።

  • እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤ ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤ መሠረትዋን እንዲበላ፣ በጽዮን እሳት ለኰሰ። (ሰቆቃወ 4፥11)
  • ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤ እንደ ጠላት አረዳቸው። (ሰቆቃወ 2፥4)
  • ከኃጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል። (ሰቆቃወ 1፥5)
    ከዚያ መጽሐፉ እንዴት ነው የሚያልቀው?

ሊኖር በሚችለው ብቸኛ የተስፋ ቃል ያልቃል፦

  • እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን። (ሰቆቃወ 5፥21)

የእኔም – የእናንተም ብቸኛ ተስፋችን ይህ ነው።

ኢየሱስ ለጴጥሮስ እንዲህ ብሎታል፦ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ” (ሉቃስ 22፥31-32)።

ከተመለስህ ሳይሆን፣ በተመለስህ ጊዜ። ስለ አንተ ጸልያለሁ። ስለዚህም ትመለሳለህ። በተመለስክም ጊዜ ከጥፋት የሚመልስህ የእኔ ጸጋ ይሆናል።

ውድ ክርስቲያኖች ሆይ! ይህ የእናንተም እውነታ ነው። በእምነት ለመጽናታችሁ ብቸኛ ተስፋችሁ ይህ ነው።

… በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። (ሮሜ 8፥34)

ይመልሰናል። ስለዚህም፣ “እንዳትወድቁ ሊጠብቃችሁ … ለሚችለው፣ ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለምም ድረስ ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ሥልጣን ይሁን” (ይሁዳ 1፥24-25)። አሜን!