መለወጥ ይቻላል | ሕዳር 10

እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው። (ኤፌሶን 4፥24)

ክርስትና ማለት፥ ለውጥ ይቻላል ማለት ነው። ጥልቅና ሥር ነቀል ለውጥ። ግልፍተኛ እና ግድየለሽ የነበረ ሰው፣ በእግዚአብሔር ጸጋ ተለውጦ ርኅሩኅ ልብ ሊኖረው ይችላል። ከመራርነት እና ከንዴት ባርነት ነፃ መውጣት ይቻላል። አስተዳደጋችሁ እና ትላንትናችሁ ምንም ይሁን ምን፣ የፍቅር ሰው መሆን ይቻላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ መሆን ያለብንን እንድንሆን የሚያደርገን ወሳኙ አካል እግዚአብሔር ነው ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ ያለአንዳች ማመንታት “ … ማንኛውንም ክፋት … ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ”፤ እናም ደግሞ “እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” ይላል (ኤፌሶን 4፥31-32)። “ርኅሩኆች ሁኑ” ነው እንጂ የሚለው “ከቻላችሁ … ” ወይም “ወላጆቻችሁ ርኅሩኆች ከሆኑ . . . ” ወይም “አስከፊ ጉዳት ካልተጎዳችሁ … ” አይልም።

ይህ በሚያስደንቅ ሁኔታ ነጻ የሚያወጣ ትዕዛዝ ነው። “እኔ ልለወጥ አልችልም” ከሚል ግትር ድምዳሜ ነፃ ያደርገናል። የኋላ ታሪኬን እንደ ማይለወጥ ዕጣ ፈንታ ከመቁጠር ነፃ ያደርገኛል።

የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ደግሞ ሁልጊዜ የሚመጡት ነፃ አውጪና ሕይወትን ቀያሪ ከሆኑ እውነቶች ጋር ነው። እነዚህ እውነቶች ደግሞ ሊታመኑ የተገቡ እውነቶች ናቸው።

ለምሳሌ፦

  • እግዚአብሔር እኛን የጉዲፈቻ ልጆቹ አድርጎ ወሰደን፦ አዲስ አባት እና አዲስ ቤተሰብ አለን። ይህ እውነት ደግሞ ለቤተሰባችን ወይም ላደግንበት ማሕበረሰብ ዕጣ ፈንታ ተገዢ እንዳንሆን ነጻ ያወጣናል። “በሰማይ ያለ አንድ አባት ስላላችሁ፣ በምድር ማንንም ‘አባት’ ብላችሁ አትጥሩ” (ማቴዎስ 23፥9)።
  • እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይወደናል፦ እኛ የእግዚአብሔር “የተወደዱ ልጆች” ነን (ኤፌሶን 5፥1)። የእግዚአብሔርን ፍቅር እንድንለማመድ የተሰጠው ትዕዛዝ በአየር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” በሚለው የእግዚአብሔር አቅም ሰጪነት ላይ የተንተራሰ ነው። “ተዋደዱ!” ትዕዛዝ ነው፣ በእግዚአብሔር መወደድ ደግሞ ኅይል ነው። በእግዚአብሔር በመወደዳችን የምናገኘው ኀይል ሌሎችን የምንወድበትን አቅም ይሰጠናል።
  • እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር ብሎናል፦ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” (ኤፌሶን 4፥32)። እግዚአብሔር በክርስቶስ ያደረገው እጅግ ኅይለኛ ነገር ነው። ለውጥን የሚቻል አድርጎታል። “ርኅሩኆች ሁኑ” የሚለው ትዕዛዝ የተመሰረተው እናታችን ወይም አባታችን ካደረጉብን ነገር ይልቅ እግዚአብሔር በልጁ ያደረገልን ነገር ላይ ነው። ይህ ዐይነት ትዕዛዝ በእርግጥም መቀየር እንደሚቻል ያረጋግጣል።
  • ክርስቶስ ወደደን፤ ራሱንም አሳልፎ ሰጠን፦ “ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ” (ኤፌሶን 5፥2)። ትዕዛዙ የመጣው ሕይወት ለዋጭ ከሆነ እውነት ጋር ነው። “ክርስቶስ ወደዳችሁ”። ለሆነ ሰው ፍቅር የምታሳዩበት ዕድል አግኝታችሁ፣ የሆነ ድምጽ ከጀርባ ሆኖ፣ “አንተ እኮ ግን ሰው አትወድድም” ብሎ ሲያንሾካሹክ፣ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ፦ “ክርስቶስ ለእኔ ያለው ፍቅር አዲስ ዐይነት ሰው አድርጎኛል። ለእኔ ያለው መውደድ እውነት እንደሆነ ሁሉ፣ ሌሎችን እንድወድ ያዘዘኝ ትእዛዝም በእኔ የሚቻል ነው” በሉት።

“እኔ እኮ እንዲህ ነኝ፣ መለወጥ አልችልም፣ ይሄ ባህርይ ተወስኖብኛል” አትበሉ። ክርስቲያን ሁኑ። ለውጥ ይቻላል። እግዚአብሔር ሕያው ነው። ክርስቶስ ተነሥቷል። ተስፋዎቹ ሁሉ እውነት ናቸው።