መንገዱም ፍጻሜውም የሆነው ክርስቶስ | የካቲት 15

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው። (ገላትያ 2፥20)

እግዚአብሔር አጽናፈ ዓለሙን ለምን ፈጠረ? ለምንስ አሁን በምናየው መንገድ ያስተዳድረዋል? እግዚአብሔር ምንን እያሳካ ነው? ለዚህስ ስኬት ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ነው ወይስ የስኬቱ ፍጻሜ?

ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው የእግዚአብሔር መገለጥ ነው። ስጋን የለበሰ አምላክ ነው። በዚህ ረገድ፣ ፍጻሜ እንጂ መንገድ አይደለም።

አጽናፈ ዓለሙ ሁሉ የተፈጠረው የእግዚአብሔርን ክብር ለመግለጥ ነው። እግዚአብሔር እያሳካ ያለው ይህንኑ ነው። ሰማያትና የዓለም ታሪክም “የእግዚአብሔርን ክብር ይተርካሉ“።

ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ የተላከው ሊሰራ የሚገባን ስራ ለማሳካት ነው። ይኸውም ለውድቀት መፍትሄ ለመሆን ነው። ኀጢአተኞች በኀጢአታቸው ምክንያት ከሚመጣባቸው አይቀሬ ጥፋት ሊታደጋቸው መጣ። እነዚህ የታደጋቸው ደግሞ በዘላለማዊ ደስታ የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ፣ ያጣጥማሉ፣ እንዲሁም ለዓለም ሁሉ ያሳያሉ።

ሌሎቹ ግን በእግዚአብሔር ክብር ላይ ንቀታቸውን መከመር ይቀጥላሉ። ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ደስታ ሲል የራሱን ክብር የገለጠበት መንገዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ያለ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ማንም የእግዚአብሔርን ክብር አይቶ ሊያጣጥምና ሊያከብረው አይችልም። ያለ ክርስቶስ የአጽናፈ ዓለሙ ዓላማ ይከሽፋል። ስለዚህ ክርስቶስ መንገዱ ነው።

ነገር ግን ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራ ለኀጢአተኞች በመሞት የአብን ፍቅር እና ጽድቅ በልቀት ገልጦታል። ይህም የጸጋው ክብር – የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ቁንጮ ነው።

ስለዚህ፣ የእግዚአብሔር የዓላማው መንገድ ሆኖ እንከን የለሽ ድርጊቱን በፈጸመበት ቅጽበት፣ ኢየሱስ የዚህ ዓላማ ፍጻሜም ሆኗል። እርሱ በኃጢአተኞች ቦታ በመሞቱና ትንሳኤውም ለትንሳኤያቸው በመሆኑ፣ የእግዚአብሔር ክብር ማዕከል እና የመጨረሻው መገለጥ ሆኗል።

ስለዚህ የተሰቀለው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዓላማ መንገድም፣ ፍጻሜም ነው ማለት ነው።

ያለ እርሱ ስራ፣ ፍጻሜው — ማለትም ለሕዝቡ ደስታ የሆነው የእግዚአብሔር የክብሩ ሙላት — ሊገለጥ አይችልም ነበር።

ደግሞም በዚያው መንገድ የመሆን ሥራው፣ ፍጻሜም ሆነ ማለት ነው — እርሱ ስለእኛ እርግማን በሆነበት ጊዜ ስለእግዚአብሔር የገለጠልንን እያየን እና እያጣጣምን፣ ለዘለዓለም የአምልኳችን ትኩረት ሆኖ ይኖራል።

ኢየሱስ አጽናፈ ዓለሙ ሁሉ የተፈጠረለት ፍጻሜ ነው። ደግሞም ይህንን ፍጻሜ የጸደቁ ኃጢአተኞች ደስ እንዲሰኙበት የሚያስችል መንገድም ነው።