ክርስቶስ እንደ ፀሓይ ብርሃን ነው | ጥቅምት 17

እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል። (ዕብራውያን 1፥3)

ብርሃን የፀሓይ ነጸብራቅ እንደሆነ ሁሉ፣ ኢየሱስም የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ነው።

እነዚህ ምሳሌዎች እንከን አልባ ባይሆኑም ለማሳያነት ይጠቅሙናል፦

  1. ፀሓይ ያለ ብርሃን ጨረሮች ኖራ አታውቅም፤ ሁለቱ ነገሮች መለያየት አይችሉም። ክርስቶስ እና እግዚአብሔር አብም እንዲሁ ናቸው። ክብሩ እና ነጸብራቁ አንድ ላይ ይኖራሉ። አብረው ዘላለማዊ ናቸው።
  1. ነጸብራቅ ማለት የሚወጣው ክብር ማለት ነው። ይህ ነጸብራቅ ከክብሩ ጋር ልዩነት የለውም፤ ክርስቶስም እንዲሁ ለብቻው የቆመ፣ ግን ከአብ ያልተለየ ነው።
  1. ስለዚህ የክብሩ ነጸብራቅ የተፈጠረ ነገር ሳይሆን አብሮ የኖረ እና ለዘላለም የሚኖር ነው። ክርስቶስም ለዘላለም ከአባቱ የተገኘ እንጂ የተሠራ ወይም የተፈጠረ አይደለም።
  1. ፀሓይን የምናያት በጨረሮቿ ምክንያት ነው። ልክ እንዲሁ፣ ኢየሱስን አየን ማለት እግዚአብሔርን ተመለከትን ማለት ነው።

ስለዚህ ይህንን ታላቅ አምላክ ኢየሱስን እንድታምኑት እና እንድትወዱት አሳስባችኋለሁ። እርሱ ህያው፣ በአብ ቀኝ የተቀመጠ፣ በኀይል እና በሥልጣን አንድ ቀን ተመልሶ የሚመጣ ነው። እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ወልድ ነው፤ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌም ነው።