ገና ለነፃነት ነው | ታሕሳስ 23

ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።

ዕብራውያን 2፥14-15

ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣበት ምክንያት ከሰው በላይ የሆነ ሰው መሞቱ አስፈላጊ ስለነበር ነው። ኢየሱስ ሰው ሆነ ማለት አምላክ ራሱን የሞት ፍርደኞች እስር ቤት ውስጥ ቆለፈ እንደ ማለት ነው።

ሞት ክርስቶስ ላይ የተጋረደ አደጋ አልነበረም። ሞትን መርጦ እና ተቀብሎት ነው የመጣው። እንዲያውም የመጣበት ዋነኛው ምክንያት ያ ነው፤ “እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማርቆስ 10፥45)።

ሰይጣን በምድረ በዳ እና በጴጥሮስ አንደበት ኢየሱስን ከመስቀሉ ዓላማ ሊያስተው የሞከረውም ለዚህ ነበር (ማቴዎስ 4፥1-11)(ማቴዎስ 16፥21-23)! መስቀሉ የሰይጣን መጥፊያ ነበር። ግን እንዴት ኢየሱስ ሰይጣንን አጠፋው?

ሰይጣን “በሞት ላይ ሥልጣን” እንዳለው ዕብራውያን 2፥14 ይነግረናል። ይህ ማለት ሰይጣን ሞትን አስፈሪ የማድረግ አቅም አለው ማለት ነው። ሰይጣን “በሞት ላይ ሥልጣን” ስላለው ሰዎች በሞት ፍርሀት ተጠፍረው እንዲኖሩ ያደርጋል። ሰዎችን በኀጢአታቸው ጠፍሮ በመያዝ ሞት አስጨናቂ እንዲሆንባቸው የማድረግ ሥልጣን አለው።

ነገር ግን ኢየሱስ ይህንን ሥልጣን ከሰይጣን ነጠቀው። ትጥቅ አስፈታው። ከሰይጣን ኩነኔ የሚከላከልልንን የጽድቅ ጥሩር አለበሰን። ይህንን እንዴት አደረገ? በሞቱ፣ ኢየሱስ ኀጢአታችንን ሁሉ አጠበ። ኀጢአት የሌለበት ሰው ደግሞ በሰይጣን ሊኮነን አይችልም። ካገኘነው ምሕረት የተነሣ ከእንግዲህ ማንም ሊያጠፋን እና ሊያወድመን አይችልም። የሰይጣን ዕቅድ የነበረው የእግዚአብሔርን ተከታዮች በራሱ በእግዚአብሔር ችሎት ውስጥ የእግዚአብሔርን አገዛዝ ማፍረስ ነበር። ነገር ግን አሁን በክርስቶስ ምክንያት ኩነኔ የለብንም። የሰይጣን ክህደት ተገልብጧል። ዓለምን ሁሉ ያወከበት ተንኮሉ እንክትክቱ ወጥቷል። “ቁጣውን ለጥቂት ጊዜ እንሸከማለን፤ ምክንያቱም መጥፋቱ አይቀሬ ነው።” መስቀሉ ሰይጣንን ደርምሶታል፤ የመጨረሻውን እስትንፋሱን የሚስብበት ጊዜም ተቃርቧል።

ገና ለነፃነታችን ነው፤ ከሞት ፍርሀት ነፃ የወጣንበት።

ኢየሱስ፣ በኢየሩሳሌም ሞታችንን ሊሞት፣ በቤተ ልሔም የእኛን መልክ ይዞ ተወለደ። ይህንን ሁሉ ያደረገው ደግሞ ዛሬ በከተማችን ውስጥ ያለ ፍርሀት እንድንመላለስ ነው። አዎን፣ ፍርሀት አልባ! ለደስታችን ሥጋት የነበረው ትልቁ ፍርሀት ከተወገደልን፣ በጥቃቅኖቹ ምድራዊ ፍርሃቶች ለምን እንታወካለን? እስቲ አስቡት ለምሳሌ፤ እንዴት ብለን ነው፣ “ሞትን አልፈራም፤ ግን ከሥራ መባረርን እፈራለሁ” የምንለው? አስቡት! አይሆንም!

ሞት ከእንግዲህ ከተወገደ፣ (ሞት ስል፣ የልብ ምታችን አቁሞ የምንቀዘቅዝበት ሞት ማለቴ ነው) በርግጥም ከጥግ እስከ ጥግ ነፃ ነን ማለት ነው። ስለ ክርስቶስ እና ስለ ፍቅር ስንል ከፀሓይ በታች የትኛውንም አደጋ በድፍረት ልንጋፈጥ ነፃ ነን። ከእንግዲህ የፍርሀት ባሮች አይደለንም።

እንግዲህ ልጁ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእውነት ነፃ ትሆናላችሁ!