ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው (ሮሜ 9፥8)።
የብሉይ ኪዳኑን አብርሃም እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ አድርጋችሁ አስቡት። ጌታ “እባርክሃለሁ፤ አገልግሎትህንም አሳድገዋለሁ” ይለዋል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቷ መካን ናት፤ ልጆችንም አላፈራችም።
ታዲያ አብርሃም ምን ያደርጋል? በእግዚአብሔር ተዓምራዊ ጣልቃ ገብነት ላይ ተስፋን ማጣት ይጀምራል። እያረጀ ነው። ሚስቱም መካን እንደሆነች ነው። ስለዚህ በእግዚአብሔር ተስፋ የተሰጠውን ልጅ ያለ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ለማግኘት ይወስናል። የሚስቱ አገልጋይ ከሆነችው አጋር ጋር ይተኛል (ዘፍጥረት 16፥4)። ነገር ግን ውጤቱ “የተስፋው ልጅ” ሳይሆን፣ “ከሥጋ የሆነው ልጅ” እስማኤል ይሆናል።
በዘፍጥረት 17፥16 ላይ እግዚአብሔር አብርሃምን፣ “ከእርሷም [ከሚስቱ ከሳራ] ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ” ብሎ ያስደንቀዋል። አብርሃም ግን፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” ሲል ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል (ዘፍጥረት 17፥18)። የራሱ የሆነው የሥጋ ጥረቱ የእግዚአብሔር ተስፋ ፍጻሜ እንዲሆን ይፈልጋል። ነገር ግን እግዚአብሔር ደግሞ እንዲህ ይላል፤ “ይሁን እሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች” (ዘፍጥረት 17፥19)።
ሳራ ግን 90 ዓመት ሞልቷታል። ዘመኗን ሁሉ መካን ነበረች፤ በዚያ ላይ ደግሞ ልጅ የመውለጃ ጊዜዋ አልፏል (ዘፍጥረት 18፥11)። አብርሃም ደግሞ 100 ዓመቱ ነው። የተስፋውን ልጅ ለማግኘት ብቸኛው ተስፋው ተዓምራዊ የሆነ የአምላክ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው።
“የተስፋው ልጅ” መሆን ማለት፣ “ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ” ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር መወለድ ማለት ነው (ዮሐንስ 1፥13)። በዚህ ዓለም ላይ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው የሚቆጠሩት፣ በተሰጠው የተስፋ ቃል በተዓምራዊ መንገድ የተወለዱት ብቻ ናቸው። በገላትያ 4፥28 ላይ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ እናንተም [ክርስቲያኖች] እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ።” “የተወለዳችሁት ከመንፈስ” እንጂ ከሥጋ አይደለም (ገላትያ 4፥29)።
በድጋሚ አብርሃምን እንደ አንድ መጋቢ አስቡ። እግዚአብሔር እንደገባለት ቃል ኪዳን ቤተ ክርስቲያኗ እያደገች አይደለም። አምላካዊውን ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ታክቶታል። ስለዚህም “አጋር” ወደ ሆነው የሰው ብልሃት ይዞርና ያለ ተዓምራዊው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ “ሰዎችን ለመማረክ” ይወስናል።
ነገር ግን ይህ ቤተ ክርስቲያን የይስሐቆች ሳይሆን የእስማኤሎች ቤተ ክርስቲያን ነው የሚሆነው። የእግዚአብሔር ልጆች ባልሆኑ የሥጋ ልጆች ቤቱ ይሞላል። እንዲህ ካለው ገዳይ ስኬት እግዚአብሔር ይጠብቀን። ለወንጌል በሚያስፈልገው መንገድ ሁሉ ሥሩ። ሳትታክቱ ሥሩ! ነገር ግን፣ ሁልጊዜም፣ ወሳኝ ወደሆነው ተዓምራዊ የጌታ የማዳን ሥራ ተመልከቱ። “ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤ ድል ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ምሳሌ 21፥31)።