የዘገዩ ነፃ መውጣቶች | ጥር 25

ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እሥራት ተፈታ። (ሐዋርያት ሥራ 16፥26)

በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ሕዝቡን ከትንሽ ጉዳት ያድናል። ከሁሉም ጉዳት አይደለም። ይህ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም አለዚያ ከጉዳታችን ተነሥተን እግዚአብሔር ረስቶናል ወይም አልተቀበለንም ብለን እንደመድም ነበር።

ስለዚህ ጳውሎስና ሲላስ በሐዋርያት ሥራ 16፥19-24 ነፃ ሳይወጡ በቁጥር 25-26 ነፃ ስለወጡ እንበረታታ።

በመጀመርያ ነፃ መውጣት አልነበረም፦

– “ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለ ሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው” (ቁጥር 19)

– “ገዦቹም ልብሳቸውን ገፈፏቸው” (ቁጥር 22)

– እነርሱም “ክፉኛ ደበደቧቸው” (ቁጥር 23)

– የወህኒ ቤት ጠባቂው “እግራቸውን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው” (ቁጥር 24)

ከዚያ ግን ነፃ መውጣት፦

እኩለ ሌሊት አካባቢ ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩና እየዘመሩ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ነበር፤ … ድንገትም የወህኒ ቤቱን መሠረት የሚያናውጥ ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ ሆነ፤ ወዲያውም የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፈቱ፤ የሁሉም እሥራት ተፈታ (ቁጥር 25-26)።

እግዚአብሔር ቀድሞ ሊያስቆመው ይችል ነበር። ምክንያት ስለነበረው ይህን አላደረገም። ጳውሎስና ሲላስን ይወዳቸዋል።

ጥያቄ፥ ሕይወታችሁን በጳውሎስ የችግርና ከዚያም ነፃ የመውጣት የሕይወት አካሄድ መሠረት ብታዩት የት ጋር ናችሁ? ተገፎ በመመታት ጊዜ ወይስ ከእሥር ተፈቶ በር በተከፈተበት ጊዜ?

ሁለቱም የእግዚአብሔር ጊዜያት ናቸው። እርሱ አልተዋችሁም፤ አልረሳችሁም (ዕብራውያን 13፥5)።

በችግር ጊዜ ከሆናችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ዘምሩ። ነፃነት እየመጣ ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው፤ በሞትም ቢሆን የሚመጣው። “እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሁን፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ” (ራእይ 2፥10)።