“ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” (ማቴዋስ 6፥33)
በሚያስፈልገን ጊዜ የሚገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ከምንም በላይ በቂ መሆኑን ከሚያሳዩ ኃያል ምስክርነቶች ውስጥ አንዱ፣ የብዙ ሚስዮናውያን ህይወትን የሚመራው “የእምነት መርህ” ነው። ለምሳሌ ያክል፣ የባህር ማዶ ሚስዮናውያን ህብረት የሆነውን Overseas Missionary Fellowship – OMF) መጥቀስ እንችላለን።
ለሚሲዮናዊ ሥራ የተለያዩ ዓይነት አካሄዶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንዱን ለማወደስ የግድ ሌላውን መንቀፍ አይኖርብንም። ታዋቂዎቹ የወንጌል ሚስዮናውያን ሃድሰን ቴይለርን እና ጆርጅ ሚውለር ለወንጌል ስራ ገንዘብ ሲያስፈልጋቸው የሰጪዎችን ልብ ለመቀስቀስ ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት ወደ ሰዎች ሳይሆን ወደ እግዚአብሔር ነው። የእነዚህን ሁለት ሰዎች ፈለግ የተከተሉ ሚስዮናውያንም ይህንን በማድረግ ይታወቃሉ።
OMF International በቻይና፣ ከዚያም በእስያ፣ ብሎም በበርካታ የዓለም ክፍሎች የወንጌል ሚስዮናውያንን የሚያሰማራ ድርጅት ነው። የOMF International መስራች የልጅ ልጅ የሆነው ጄምስ ቴይለር፣ በእግዚአብሔር የወደፊት ጸጋ ላይ የሚኖረን እምነት የሚመሰረተው ባለፈው ጸጋ ላይ መሆኑን በመረዳት፣ ይህ እምነት እንዴት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ያስረዳል። እንዲህ ይላል፦
የምንጀምረው እምነት ላይ በመመሥረት ነው። እግዚአብሔር እንዳለ እናምናለን። መኖሩን በተለያዩ መንገዶች እርግጠኛ ሆነናል። ነገር ግን ከየትኛውም መንገድ በላይ፣ የእግዚአብሔርን ጸጋ የምናውቀው በመንፈሱ ዳግም በመውለዱ እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እርሱን ወደማወቅ በማምጣቱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ለመነሳቱ ታሪካዊ ማስረጃ እንዳለ ስለምንናውቅ በእርሱ ለማመን ጠንካራ መሠረት እንዳለን እናምናለን። አንድ ሰው፣ ሞቶ እንደሚነሳ ከተናገረ በኋላ እንዳለው ካደረገው፣ ያ ሰው በሌላ ነገር ሁሉ ፍጹም እምነት ሊጣልበት ይችላል ብለን እናምናለን። ስለዚህ፣ ለነፍሳችን ዘላለማዊ መዳን ብቻ ሳይሆን፣ የዕለት እንጀራችንን እና ለስራው የሚያስፈልገንን የገንዘብ አቅርቦት ሁሉ እንደሚያዘጋጅልን ሙሉ በሙሉ እናምናለን።
OMF International በአስፈላጊ ጊዜ የሚገለጠውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ክብር ለማጉላት፣ በእግዚአብሔር አስደናቂ ታማኝነት የተሞሉ ምስክርነቶችን በየጊዜው ያሳትማል። “እግዚአብሔር እንደሚያደርግ ለተናገራቸው ነገሮች ሁሉ ልንታመነው እንደሚገባ ለመመሥከር ወጪዎቻችንን ሁሉ እንዴት እንደሚሸፍን እናሳያለን። ጥቃቅን እና ተደጋጋሚ የሚባሉ ወጪዎችን ሳይቀር የምግብ፣ የሕክምና፣ የአውሮፕላን ቲኬት ወጪዎችን ሁሉ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት ለበርካታ የሚስዮናዊ ቡድኖች ሙሉ መደበኛ ድጋፍ እግዚአብሔር እንዴት እንዳሟላ በማካፈል፣ በእርግጥም እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም፣ እምነት ሊጣልበት የሚገባ አምላክ መሆኑን እናውጃለን።”
አያችሁ፣ OMF International — በንግግራቸው እና በድርጊታቸው በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ያሳያሉ፣ ስለታማኝነቱም ያከብሩታል። ሃድሰን ቴይለር እንዲህ ይላል፦ “ሕያው የሆነ አምላክ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስም ተናግሯል። ያለውን ሁሉ ያደርጋል። ቃል የገባውንም ሁሉ ይፈጽማል።”
በእምነት የተኖሩ ሕይወቶች የእግዚአብሔርን ተዓማኒነት የሚያሳዩ ትልልቅ መስታወቶች ናቸው።