ከእንግዲህ በኋላ የመርገም ጨርቅ አይኖርም | ግንቦት 2

“ሁላችን እንደ ረከሰ ሰው ሆነናል፤ የጽድቅ ሥራችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው።” (ኢሳይያስ 64:6)

እግዚአብሔር የትኛውንም ዓይነት፣ ትልቅ ወይም ትንሽ ሊባል የሚችል ኃጢአት ሊታገስ ስለማይችል፣ የትኛውም መተላለፋችን ቅድስናውን በመንካት እኛን ለፍርድ ማጋለጡ የማይቀር እውነት ነው (ዕንባቆም 1:13ያዕቆብ 2:10-11)።

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአሁን ጊዜ፣ የሰው ልጅን ውድቀት ያመጣው ኃጢአት አልባ ፍጥረት መሆን አለመቻሉ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ምህረቱ የገባውን ቃል አለመታመኑ ነው። በተለይም ደግሞ አንድ ቀን አዳኝ እንደሚልክ፣ ይህም አዳኝ ለሕዝቡ ፍፁም ጽድቃቸው እንደሚሆን፣ እግዚአብሔር የገባውን ቃል ተስፋ አለማድረጉ ነው። “እግዚአብሔር ጽድቃችን ነው” ሲል ተናግሮ ነበር (ኤርምያስ 23:633:16)። የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን የሚድኑት በዚህ መልኩ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ለመታዘዛቸው ምክንያት የሆነው ይህ እምነት ነበር። መታዘዛቸው ደግሞ ለዚህ እምነታቸው ማስረጃ ነበር።

ሰዎች፣ “ብቸኛ ዋጋ ያለው ጽድቅ ከክርስቶስ የተቀበልነው ጽድቅ ነው” ብለው ሲናገሩ መስማት እጅግ ግራ የሚጋባ ነው። እርግጥ ነው፣ መዳናችን የሚረጋገጠው ክርስቶስ ለእኛ በሰጠን ጽድቅ ብቻ እንጂ፣ በእኛ ቅድስና ወይም ፍፁምነት አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ “ጨርሶ በሰው ልጆች ውስጥ እግዚአብሔርን ሊያስደስት የሚችል ጽድቅ የለም” በማለት በቸልተኝነትና በንቀት ይናገራሉ። ይህ ግን ልክ አይደለም።

ለዚህ አባባላቸውም እንደ ማስረጃ የሚጠቅሱት ኢሳይያስ 64:6ን ነው፦ “የጽድቅ ሥራችን እንደ መርገም ጨርቅ ነው” ይላል።

ነገር ግን፣ የዚህን ክፍል አውድ ስንመለከት፣ ማንኛውም በሰዎች የሚደረግ የፅድቅ ስራ ተቀባይነት የለውም እያለ አለመሆኑን እንረዳለን። እዚህ ጋር ኢሳይያስ እየተናገረ ያለው ሥራቸው የግብዝነት ስለሆኑ ሰዎች ነው። ይህም ደግሞ ጽድቅ ሊባል አይችልም። ደግሞም ይህን ከማለቱ በፊት በኢሳይያስ 64:5 ላይ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፦ “በደስታ ቅን ነገር የሚያደርጉትን፣ መንገድህን የሚያስቡትንም ትረዳለህ።”

የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ ፍፁም የሆነው የክርስቶስ የጽድቅ ሥራ በአብ ፊት የእነርሱ ተደርጎ ካልተቆጠረላቸው ተቀባይነት አለማግኘታቸው እጅግ የከበረ እውነት ነው (ሮሜ 5:191ኛ ቆሮንቶስ 1:302ኛ ቆሮንቶስ 5:21)። ይህ ማለት ግን፣ በእነዚህ በክርስቶስ በጸደቁ ሰዎች ውስጥ — ምንም እንኳ ፍጹም ባይሆንም — “የመርገም ጨርቅ” ያልሆነን የጽድቅ ሥራን ግን እግዚአብሔር አይፈጥርም ማለት አይደለም።

ይልቁንም እግዚአብሔር በእርሱ ፊት ክቡር የሆነውን ይህንን ጽድቅ በሰዎች ውስጥ ይፈጥራል። እንደውም በክርስቶስ ለመዳናችን እና የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን እንደማስረጃ ይፈልገዋል። ልብ በሉ፤ ይህ ቅድስና የመዳናችን መሰረት ሳይሆን ማስረጃ ነው። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 1:10-11 ላይ እንዲህ ሲል ይጸልያል፦ “ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚእብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው።” እኛም ይህንን ፀሎት ልንፀልይ ይገባናል።