ልባችሁን አታደንድኑ | ሕዳር 6

ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደሆነ እንረዳለን። (ዕብራውያን 3፥​18–19)

ምንም እንኳን የእስራኤል ሰዎች ቀይ ባህር ሲከፈል የተመለከቱ እና በደረቅ መሬት በባህሩ ውስጥ የተራመዱ ሕዝብ ቢሆኑም፣ በተጠሙበት ቅጽበት ልባቸው በእግዚአብሔር ላይ እልከኛ ይሆን ነበር፤ እንደሚንከባከባቸውም ለማመን ፈቃደኛ አልነበሩም። በእርሱ ላይ የሚያጉረመርሙ እና በግብፅ የነበራቸው የባርነት ሕይወት ይሻላል የሚሉ ሕዝብ ነበሩ።

የዕብራውያን መጽሐፍ የተጻፈውም ይህ በድጋሚ እንዳይከሰት ነው። አቤት! ስንት ክርስቲያን ነን ባዮች ከእግዚአብሔር ጋር መንገድ ይጀምሩ ይሆን? ኅጢአታቸው እንደሚሰረይላቸውና ከሲኦል አምልጠው ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚሄዱ ሲነገራቸው፣ እነርሱም “የሚጠቅመኝ ከሆነማ፣ አምናለሁ” ብለው የሚመጡ ብዙ ናቸው።

ከዚያ በኋላ ግን በሳምንቱ፣ ወይም በወሩ፣ ወይም በዓመቱ፣ ወይም በዐሥረኛው ዓመት፣ ፈተና ይመጣል፤ በምድረ በዳ ውሃ የሌለበት ወቅት። ከመና ጋር ድካም ይመጣል። ከዚያማ፣ በዘኍልቍ 11፥5-6 ላይ እንደተገለጸው፣ ቀስ በቀስ ጠፊ የሆነውን የግብጽን ተድላ ወደ መናፈቅ ይመለሳሉ። “በግብፅ ያለ ምንም ዋጋ የበላ ነው ዓሣ እንዲሁም ዱባው፣ በጢኹ፣ ኵራቱ፣ ነጭ ሽንኩርቱ ትዝ ይለናል። አሁን ግን የምግብ ፍላጎታችን ጠፍቶአል፤ ከዚህ መና በስተቀር የምናየው የለም!” ይላሉ።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ መሆን ምነኛ አስፈሪ ነው? ቀድሞ ለክርስቶስ፣ ለቃሉ፣ ለጸሎት፣ ለአምልኮ፣ ለወንጌል፣ ለእግዚአብሔር ክብር የነበራችሁ መሰጠት እና የመኖር ፍላጎት አሁን እንደሌላችሁ መመልከት እጅግ አስፈሪ ነገር ነው። ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ የዚህ ዓለም አላፊ ተድላዎች የበለጠ ማራኪ ሆኖ ማግኘት ያስደነግጣል።

ምናልባት አሁን ያላችሁበት ሁኔታ ይህ ከሆነ፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን እንድታደምጡ እለምናችኋለሁ። “እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደሆነ እንረዳለን” የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ከኅጢአት ማታለል ንቁ። ታላቁ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህን የሆነውን ኢየሱስን ተመልከቱ፤ በእርሱም መታመናችሁንና ተስፋ ማድረጋችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።

ከእግዚአብሔር ጋር መንገድ ጀምራችሁ ካልሆነ፣ እባካችሁ አሁን ተስፋችሁን በእርሱ ላይ አድርጉ። ከኅጢአትና ራስ ላይ ከመደገፍ ተመለሱ። እምነታችሁን በታላቁ አዳኝ ላይ አድርጉ። እንድታምኑና እንድትጸኑ፣ በሕይወትም እንድትኖሩ ይህ ተጽፎላችኋል።