የዩኒቨርስቲ ቆይታችሁን አታባክኑት

ምንም እንኳ ወደ 21 ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ ቢኖሩም ትኩረቴን የሳበው ግን የቁጥሩ ትልቅነት አልነበረም። ይልቁንም የወቅቱ ወሳኝነት እንጂ። በሕይወታችን ወሳኝ በሆኑ በእነዚህ ወቅቶች ላይ ሕይወትን የሚያቀኑ መረዳቶች፣ ሕይወትን የሚመሩ ዐላማዎች እንዲሁም ለሕይወት ዐቅም የሚያስታጥቁ ኀይሎች የሚገኙበት እና ሥር የሚሰድዱበት ጊዜ ነው።

ጉርምስና የሚባለው ነገር ሁልጊዜ የነበረ ነገር አይደለም። የዘመናዊው ዓለም ፈጠራ ነው።

ታዳጊና ጉርምስና የሚባሉ የዕድሜ ክልሎች የ20ኛው ክፍለ ዘመን ግኝቶች ናቸው። ይህም የሆነው የትምህርት በጅምላ መስፋፋትን፣ የሕጻናት ጉልበት ሕግ መርቀቅን፣ የትልልቅ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች መስፋፋትን፣ የሸማችነት በጅምላ መንሰራፋትን እና የመገናኛ ብዙኀን ላይ የተደረጉ ለውጦችን ተከትሎ ነው። በተመሳሳይ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት፣ በታዳጊ የዕድሜ ክልልና በጎልማሳ የዕድሜ ክልል መካከል የማንነትን፣ የወጣትነትን፣ የግንኙነትንና የሕይወትን ኀላፊነቶች ብሎም ባሕርይ እና ዝንባሌ አዲስ ትርጉም የሚሰጥ አዲስ የዕድሜ ክልል በማኅበረ ሰባችን ውስጥ ብቅ ብሏል። ከዚህ አዲስ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የመጣው የዕድሜ ክልል “ጎረምሳ” እና “ወጣት” የመሳሰሉ የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውታል።

የዕድሜ ክፍፍልን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ማኅበረ ሰባዊ ፍላጎትን፣ የአቻ ግፊትን፣ የትምህርት ፍላጎቶችን፣ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትንና መገናኛ ብዙኅኑ በሚሰጠው ራስን የመረዳት መለኪያ ላይ የሚመሠረት አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መምጣትን ተከትሎ ይህን ወቅት የማባከኑ ዕድል ከፍተኛ ነው።

መረዳትን፣ ዐላማንና ኀይልን ማግኘት

“ማባከን” ስል እንዲሁ በመዝናናት ብቻ መበተን ማለቴ አይደለም። ይልቁንም ሕይወትን የሚያቀናውን መረዳት፣ እንዲሁም ያለ ምንም ጸጸት ቋሚ አቅጣጫን የሚሰጠውን ዐላማ ደግሞም በሕይወት ሙሉ ዐልፎም እስከ ወዲያኛው ድረስ በፍሬያማነት ተሸክሞ የሚወስድን ኀይል ማግኘት አለመቻል ማለቴ ነው። ይህን ማድረግ አለመቻል በዩንቨርስቲ ሕይወት ውስጥ ከሚኖሩ ብክነቶች ሁሉ የከፋ ብክነት ነው።

ሕይወትን የሚያቀኑ መረዳቶች። ሕይወትን የሚመሩ ዐላማዎች። ለሕይወት ዐቅም የሚያስታጥቁ ኀይሎች። በሚሊየን ለሚቆጠሩ ተማሪዎች እነዚህ መዋቅሮች የሚመሠረቱት በዚህ የሕይወት ወቅት ላይ ነው። ልክ ሮኬት መነሻው ላይ በስሕተት ከተወነጨፈ መመለሱ ይቅርና ማርስ ላይ እንኳ ማረፍ እንደማይችለው ሁሉ፣ የሕይወት ሮኬት መስመሯን ስታ ትቅበዘበዛለች፤ መጀመሪያ በሚያነቃቁ ብርሃኖች ተከብባ ኋላ ላይ ግን ወደማያበቃ ጨለማ ውስጥ ትገባለች።

ይህ መረዳት፣ ዐላማና ኀይል ምንድን ነው?

  • ሕይወትን የሚያቃናው መረዳት የእግዚአብሔር ቃል የሕይወትን ሁሉንም ክፍል የሚቀርጽ ብቸኛውና ሙሉ ለሙሉ ታማኝ የሆነው የጥበብ ምንጭ እንደ ሆነ ማወቅ ነው።
  • ሕይወትን የሚቃኘው ዐላማ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብርና ዝና ማጉላት የሁሉም ነገር ግብ እንደ ሆነ ማወቅ ነው።
  • ለሕይወት ዐቅም የሚሰጠው ኀይል በመንፈስ ቅዱስ ቸር ጸጋ ላይ በየዕለቱ መደገፍ በሕይወት ዘመን ሙሉ ፍሬያማ ለመሆን ቁልፍ እንደ ሆነ ማወቅ ነው።

እውነት ነው እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ብዙ ሰዎች እነዚህን ነገሮች የሚያውቁት በዕድሜያቸው ብዙ ከገፉ በኋላ ነው። ለዚህም ደግሞ ምሥጋናን እሰጠዋለሁ። ይሁን እንጂ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ለመልካምም ይሁን ለክፉ እነዚህን መዋቅሮች በዩንቨርስቲ ውስጥ እያሉ የሚገነቡት መሆኑ አስደናቂ ነው።

ለታላቅ መነቃቃት መጸለይ

በቅርቡ You’ve Got Libya: A Life Serving the Muslim World. የሚል መጽሐፍ አነበብኩ። ፍሮንቲየርስ የሚባለውን ድርጅት የመሠረተው የግሬግ ሊቪንግስቶን ግለ ታሪክ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በሕይወት ምክሮች የተሞላ ነው። እምነትን የሚንጥ፤ ተስፋን የሚሰጥ መጽሐፍ ነው። ታሪኩም ስለ አንድ ወሳኝ ጊዜ ይናገራል። በዩንቨርስቲ ሳሉ ለአገራት ጸሎት በሚደረግበት ወቅት ጆርጅ ቬርወር የተባለ አንድ ባለ ራዕይ ወጣት ምንም ዐላማ ላልነበረው ግሬግ ሊቪንግስቶን የተባለ ወጣት፣ “አንተ ሊቢያን ትይዛለህ” አለው። እግዚአብሔር እነዚህን ሁለት ተማሪዎች ወስዶ “ኦፕሬሽን ሞቢላይዜሽን” እና “ፍሮንቲየርስ”  የተባሉ ሁለት ታላላቅ የሚሽነሪ ኀይል የሆኑ ድርጅቶችን እንዲመሠርቱ ሲጠቀምባቸው እነዚህ የትምህርት ዓመታት ምንኛ ወሳኝ እንደ ሆኑ የሚመሰክሩ ናቸው።

አእምሮዬንና ልቤን በእነዚያ ዓመታት ስለ ማረከልኝ እግዚአብሔርን አመሠግነዋለሁ። በ18 እና 25 መካከል ባለው ጊዜ መሠረቱ ተመሥርቶ ነበር። እንዴት ያለ ስጦታ ነው፤ ይህ ሁሉንም የሚያቅፍ መረዳት ምንጭ፣ ሁሉን የሚመራ፣ ጸጸት ፈጽሞ የሌለበት ዐላማ እንዲሁም የማይደክም የእኔ ያልሆነ ኀይል ነው።

ደግሞም ተማሪዎችን የሚያገለግሉ እንደ ክሩ፣ ኢንተርቫርሲቲ፣ ናቪጌተርስ፣ ካምፓስ አውትሪች ያሉ ሰፊ የወንጌል አገልግሎቶችን እንዲሁም እንደ ፓሽን፣ አርባና እና ክሮስ ያሉ ኮንፍረንሶችን ደግሞም ቁጥር ስፍር የሌላቸውን የክርስቲያን ትምህርት ቤቶችን እግዚአብሔር ሲባርክ ማየት ስለ ቻልን ትልቅ መታደል ነው። አሁን ደግሞ በ”ዲዛየሪንግ ጋድ” አማካይነት በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን መድረስ መቻል እንዲሁም የቤተልሔም ኮሌጅና ሴሚናሪ አስተዳዳሪ በመሆኔ ያለው ደስታ የማልጠብቀው ሕይወትን የሚያረካ ስጦታ ነው።

እ.አ.አ በ2025 ዓ.ም. እንደ አንድ ጽሑፍ ግምት መሠረት በከፍተኛ ትምህርት ላይ የሚሆኑ 262 ሚሊየን ተማሪዎች በዓለም ዙሪያ ይኖራሉ። በእውነት ሕይወትን የሚያቀኑ መረዳቶች፣ ያለምንም ጸጸት ሕይወትን የሚመሩ ዐላማዎች፣ እንዲሁም የማይወድቁ ሕይወትን ሙሉ ዐልፎም እስከ ወዲያኛው ድረስ ዐቅም የሚያስታጥቁ ኀይሎች መነቃቃት እግዚአብሔር እንዲያመጣ አብራችሁኝ ጸልዩ። ለሚሊየን ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ፣ የክርስቶስ ክብርና የመንፈስ ቅዱስ ኀይል የላቀ ተጨባጭ እውነታቸው ይሁን።

በጆን ፓይፐር