እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? (ዕብራውያን 2፥3)
መዳናችሁ እጅግ ታላቅ እንደሆነ ይሰማችኃል? ወይስ ችላ ትላላችሁ?
ለድነታችሁ ታላቅነት ምላሽ ትሰጣላችሁ? ወይስ ኑዛዜያችሁን ወይም የመኪናችሁን የባለቤትነት መብት ወይም የቤታችሁን የይዞታ ካርታ በምታዩበት መንገድ ነው የምትለኩት? አንድ ጊዜ ፈርማችሁታል፤ የሆነ ቦታ በፋይል መሳቢያ ውስጥ አለ፤ ነገር ግን በአእምሯችሁ ውስጥ በጣም ትልቅ ነገር አይደለም። ስለ እሱ እምብዛም አታስቡም። በእናንተ ላይ በየቀኑ ተጽእኖ የለውም። በሌላ አነጋገር፣ ችላ ብላችሁታል።
ነገር ግን ታላቁን መዳናችሁን ችላ ስትሉ፣ በርግጥ ችላ እያላችሁ ያላችሁት ምንድን ነው? “ታላቁን ድነት ቸል አትበል!” ሲል የሚናገረው ይኸው ነው።
- በእግዚአብሔር መወደድን ቸል አትበል።
- ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ይቅር መባልህን፣ ተቀባይነት ማግኘትህን፣ መጠበቅህን፣ መጠንከርህን እና መመራትህን ቸል አትበል።
- መስቀል ላይ የዋለውን የክርስቶስን ሕይወት ቸል አትበል።
- በእምነት የተገኘውን ነፃ የጽድቅ ስጦታ ቸል አትበል።
- የእግዚአብሔር ቁጣ መወገድን እና የእግዚአብሔርን የእርቅ ፈገግታን ቸል አትበል።
- በውስጣችን የሚኖረውን መንፈስ ቅዱስን እና የሕያው ክርስቶስን ኅብረትና ወዳጅነት ቸል አትበል።
- በኢየሱስ ፊት ላይ የበራውን የእግዚአብሔርን ክብር ብርሃን ቸል አትበል።
- ወደ ጸጋው ዙፋን በነፃ መግባትን ቸል አትበል።
- የማይጠፋውን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል መዝገብ ቸል አትበል።
ይህ በእርግጥም ትልቅ መዳን ነው። ይህን ቸል ማለት ክፋት ነው። እንዲህ ታላቅ የሆነውን ድነት ቸል አትበሉ። ምክንያቱም፣ ቸል ብትሉ ከፍርድ ማምለጫ የሚኖር ይመስላችኃልን? ጸሃፊው፣ “እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን?” ሲል የጠየቀው ይህንኑ ነው።
ስለዚህ፣ ክርስቲያን መሆን በአበክሮ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነው። ደስታ የራቀው ጉዳይ ሳይሆን በቁምነገር የሚያዝ ጉዳይ ነው። በታላቁ መዳናችን ደስተኛ መሆንን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርገን ልንይዘው ይገባል።
በዚህች ዓለም ምክንያት ወደ ጊዜያዊ እና ራስን አጥፊ ወደሆነው የኃጢአት ተድላ መንገድ ዞር አንልም። የዚህ መዳን ዋነኛ ግብ የሆነውን በእግዚአብሔር ያለንን ዘላለማዊ ደስታ ቸል አንልም። ከእንደዚህ ዐይነት ታላቅ መዳን ተታሎ ከመሄድ፣ ዓይኖቻችንን ጎልጉለን ማውጣትን እንመርጣለን።