“(በዚህ መልኩ) መንፈሳዊ መረዳት በዋነኛነት የሰማዩን ነገር ምግባራዊ ውበት መቅመስን በውስጡ ይይዛል” (ጆናታን ኤድዋርደስ፣ Religious Affections)።
ጆናታን ኤድዋርድስ ለእኔ እንደሆነልኝ፣ እኔም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ለነፍሳቸው ጥቂት እንኳ ብጠቅም ደስታዬ ምንኛ ታላቅ ይሆን ነበር። እርሱም ሆነ እኔ ልክ ሐዋርያቱ እንደ ነበሩት እስትንፋሰ እግዚአብሔርን የያዙ የእግዚአብሔር ቃል አቀባዮች አይደለንም። ይሁን እንጂ በአንድ መልኩ ከእነርሱ ጋር አብረን “የእግዚአብሔር ምስጢር ባለ ዐደራዎች” ነን (1ኛ ቆሮንቶስ 4፥1)። እኚህ ባለዐደራዎች የቤቱን ባለቤት ንብረት የሚያስተዳድሩ አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ለቤተሰቡ አባላት ጥቅም በሚያመጣ መልኩ የሚያስተዳድሩም ናቸው።
ኤድዋርድስም እንደ አንድ ጥሩ ባለዐደራ በአንድ ወቅት ተሰውረው ስለ ነበሩት አሁን ግን ስለ ተገለጡት የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራዎች ስለ ሆኑት ስለ እነዚህ “ምስጢሮች” ይናገራል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉ አስተማሪዎች ሊያደርጉ ባልቻሉት ልክ ለ40 ዓመታት ነፍሴን ሲያነቃቃልኝ ነበር። ሲ.ኤስ. ሉዊስ የዓለምን ውበት እንዳይ እንዳነቃኝ ሁሉ ኤድዋርድስ ደግሞ የእግዚአብሔርን ውበት እንዳይ አንቅቶኛል።
እግዚአብሔርን እና ቃሉን የምመለከትበትን እይታ የቀየረልኝን አንድ መንገድ ላሳያችሁ። ምናልባት ተመሳሳይ ነገር እናንተም ሊታያችሁ ይችላል።
ሁለት ዐይነት ዕውቀቶች
ብዙዎቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን በአእምሮ በማወቅ እና በመንፈስ በማወቅ መካከል ልዩነት እንዳለ በሚገባ ያልተብራራ ምልከታ አለን። “መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ከእግዚአብሔር መንፈስ የሆነውን ነገር ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ነገር ለእርሱ ሞኝነት ነው በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ፣ ሊረዳው አይችልም” እንደሚል 1ኛ ቆሮንቶስ 2፥14ን አንብበናል። 3ኛ ዮሐንስ 11፣ “ክፉ የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም” እንደሚል አንብበናል። ምንም ሳይለውጠን በኀጢአታችን ውስጥ እንዳለን ከሚተወን ምሁራዊ ዕይታ የሚበልጥ ዐይነት ማየት እንዳለ ደግሞ ተረድተናል።
በዮሐንስ 17፥3 ላይ፣ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተን… ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” የሚለውን የኢየሱስን ጸሎት አንብበናል። ከዚህም ደግሞ በመነሣት እንዲህ ያለው ዕውቀት ዲያብሎስ ካለው ዐይነት ዕውቀት እንደሚለይ ደምድመናል። ይህኛው ዐይነት ማወቅ ሕይወት ነው።
መንፈሳዊ መረዳት
ለእኔ እነዚህን ሁለት ዐይነት ዕውቀቶች (ምሁራዊ እና መንፈሳዊውን) በአንድ በመያዝ ደግሞም የተበታተኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በመሰብሰብ፣ ወደ ሚገባቸው ብሩህነት ያመጣቸውና ለሕይወት ሁለንተናዊ ክፍል ያላቸውን ጠቀሜታ ያሳየኝ ጆናታን ኤድዋርድስ ነው።
አእምሮ በምርምር ክፍሉ ብቻ ከሚረዳበት ጽንሰ ሐሳባዊ ግንዛቤ እና አእምሮ ስሜትን ከሚያስተናግድበት ልባዊ ስሜት መኻል ልዩነት እንዳለ ግልጽ ሊደረግ ያስፈልጋል። አንደኛው፣ መላምታዊ የምርምር ዕውቀት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፣ ከምሁራዊ ትንተና የዘለለ ስሜትን የሚያካትት የማስተዋል ዕውቀት ነው። በማስተዋል ዕውቀት ውስጥ ልብ ዋነኛ ተገዢ ነች ወይም ነፍስ የምትመለከት ብቻ ሳትሆን ይልቁንም ዝንባሌ ያላትና ደስ የምትሰኝ አሊያም ደስ የማትሰኝ አካል ነች። (Religious Affections, ገጽ 272 ከተጨማሪ አጽንዖት ጋር)
ቆላስይስ 1፥9 ላይ መንፈሳዊ መረዳት በሚለው ሐረግ ላይ ኤድዋርድስ አትኩሮቴን ወሰደው። “ከዚህ የተነሣ እኛ ደግሞ ይህን ከሰማንበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም።” ቀጠል ያደርግና የሚከተለውን አስተያየት ያስቀምጣል፦
በፍጥረቱም ይሁን በዐይነቱ መንፈሳዊ ያልሆነ ሰው ካለው ዕውቀት ሙሉ ለሙሉ የተለየ የመለኮታዊ እውቀት መረዳት የሚባል ነገር አለ፤ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ መረዳት በማለት የሚጠራው የመለኮታዊ ዕውቀት መረዳት እንዳለ በግልጽ ያሳያል። (ገጽ 270)
መንፈሳዊ መረዳት ምንድን ነው? ከምሁራዊ እና ፅንሰ ሐሳባዊ ወይም መላምታዊ ዕውቀትስ የሚለየው በምንድን ነው? ኤድዋርድስም ሲመልስ እንዲህ ይላል፦ “በልብ የስሜት ሕዋስ ውስጥ የመለኮታዊ ነገሮችን ቅድስና ወይም የምግባራዊ ልዕልናን የላቀ ውበት እና ጣፋጭነትን ያካትታል ይላል። ይህም የሃይማኖትን ነገር ከመለየት እና ከማወቅ ገጽታው ጋር አብሮ የሚፈስስ ደግሞም በዚያ ላይ የሚመሠረት ነው (ገጽ 272)።
አዲስ ቋንቋ፣ ከካልቪን ባሻገር
“የልብ የስሜት ሕዋስ” እና “የቅድስና ውበትና ጣፋጭነት” የሚሉት ቃላት ለእኔ አዲስ ነበሩ። ኤድዋርድስ ሲናገር መንፈሳዊ ዕውቀት ብዙውን ጊዜ በማጣጣም፣ በማሽትት ወይም በመቅመስ ይገለጻል ይላል (ገጽ 272-73)። መንፈሳዊ ዕውቀትን በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያንም ይሁን ከኮሌጅ እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተማርኩት ቋንቋ እንዲህ ያለውን አልነበረም።
እኛ በመምህራኖቻችን የተቀረጽን ነን። ለምሳሌ፦ ጆን ካልቪን እና ጆናታን ኤድዋርድስ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ዕውቀትን በመስጠት ስላለው ድርሻ ሲናገሩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ውስጥ የሌለ አዲስን መረጃ እንደማይሰጠን የሚያብራሩበትን መንገድ በንጽጽር እንመልከት።
ካልቪን፦
ቃል የተገባልን የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ከተቀበልነው የወንጌል አስተምህሮ፣ ተነድተን እንድንጠፋ ሊያደርገን የሚችል አዲስ መገለጦች የሚመሠርት ወይም አዲስ ዐይነት አስተምህሮዎች የሚፈጥር አይደለም። ይልቁንም አገልግሎቱ ወንጌል የሚያዝዘውን ትምህርት በአእምሯችን ላይ ማተም ነው።
ኤድዋርድስ፦
መንፈሳዊ መረዳት በውስጡ ምንም ዐይነት አዲስ የአስተምህሮ ዕውቀትን አይይዝም። ወይም ከዚህ በፊት ያልተነበበ እና ያልተሰማ አዲስ ዐይነት ምክረ ሐሳብ አይለግስም። ምክንያቱም እንዲህ ያለው አዲስ ምክረ ሐሳብ መንፈስ ለአእምሮ ከሚሰጠው አዲስ ጣዕም ወይም እርካታ እና መጣፈጥ ፈጽሞ የተለየ ነገር ስለሆነ ነው። (ገጽ 278)
የካልቪንም ሆነ የኤድዋርድስ ማብራሪያዎች እውነተኛ፣ ትክክለኛ፣ እንዲሁም አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ድምጸታቸው ይለያያል። መንፈሳዊ መረዳትን በመስጠት ረገድ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ፣ “ወንጌል የሚያዝዘውን ትምህርት በአእምሯችን ላይ ማተም” እንደሆነ ካልቪን ይናገራል። ኤድዋርድስ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ለአእምሯችን አዲስ ጣዕምን ወይም የውበት እና የጣፋጭነት እርካታን መስጠት ነው ይላል።
የካልቪን ቃላት በአእምሮ፣ አስተምህሮ፣ መታተም ዓለም ውስጥ የሚሽከረከሩ ናቸው። የኤድዋርድስ ቃላት ደግሞ መታተም ራሱ ልምምዱ ምን እንደሚመስል የሚመረምር ሲሆን ውበትን እና የሚጣፍጥ ነገርን መቅመስ ነው ሲል ይገልጸዋል።
አዲስ ዕይታ
በመዝሙር 34፥8 ላይ “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንድለማመድ ኤድዋርድስ ዓይኖቼን ከፈተ። ፍጥረታዊ አእምሮ የሌለው የማየት እና የመቅመስ ዐይነት አለ።
ለምሳሌ፦ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4 ላይ የማያምኑትን ሰዎች “የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስ፣ የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ” ሰይጣን እንደከለከላቸው ጳውሎስ ይናገራል። ይህም መታወር የበራበት ብቸኛው መንገድ በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን ስላበራ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥6)።
ስለዚህ ከፍጥረታዊው ማየት የተለየ መንፈሳዊ ማየት አለ። በመንፈስ የምናየው “የክርስቶስ የክብሩን ወንጌል ብርሃን” ነው። ብርሃን እናያለን። ነገር ግን የተፈጥሮ ብርሃን አይደለም። ይልቁንም የመለኮት ክብር ብርሃን ነው። የምንመለከተው የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን የክርስቶስን ክብር ነው።
በዚህም ጉዳይ ኤድዋርድስም የሚከተለውን ይናገራል፤ “አዲሱ መንፈሳዊ የስሜት ሕዋስ” የሚመለከተው የመለኮታዊ ነገሮችን ተፈጥሮ ታላቅ ውበት እና ልህቀት ነው… በዚህ መልኩ ነው መንፈሳዊ መረዳት በዋነኛነት በውስጡ ይህንን የሚይዘው። (271-272)
አዲስ ቅምሻ
ይህ መንፈሳዊ ዕይታ መንፈሳዊ ቅምሻም ተብሎ ተገልጾአል። “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ።” “ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው” (መዝሙር 119፥103)። በድነታችሁ እንድታድጉ፣ “አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥2-3)።
የኤድዋርድስን Religious Affections የተሰኘውን መጽሐፍ እስካነብብ ድረስ፣ እንደዚህ ያሉ ቃላት ስላላቸው ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ፣ የሥነ ዕውቀት እና መጋቢያዊ አንድምታቸው ምን እንደሆነ ብዙም ቦታ አልሰጣቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ለድኅነት እና ለአዲስ ልደት እንዲሁም ከሕያው እግዚአብሔር ጋር ስላለ ኅብረት ምንነት ያላቸውን አንድምታ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ እስክረዳ ድረስ ኤድዋርድስ ታገለኝ።
ለምሳሌ፣ ስለ መዝሙር 119 ኤድዋርድስ የሚከተለውን ጽፏል፦
በዚህ መዝሙር ላይ የቅድስና ልህቀት የመንፈሳዊ ጣዕም፣ እርካታ፣ ፍላጎት እና ደስታ ቀጥተኛ አካል ሆኖ ተገልጾአል። የእግዚአብሔር ባሕርይ የቅድስናው ኀያል እወጃ እና ነጸብራቅ የሆነው እንዲሁም ለፍጥረት የቅድስና ትእዛዝ ሆኖ የቀረበው የእግዚአብሔር ቃል፣ በቁጥሮቹ ሁሉ ውስጥ እንደ ምግብ እና መዝናኛ እንዲሁም የጸጋው ባሕርይ የፍቅር፣ የፍላጎት፣ የእርካታ እና ደስታ ማረፊያ አካል ሆኖ የቀረበ ሲሆን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከወርቅ እንዲሁም አለ ከተባለው ወርቅ አብልጦ ዋጋ የሚሰጥ ደግሞም ከማር እና ከማር እንጀራ የጣፈጠ ነው። (ገጽ 260 አጽንዖት የተጨመረበት)
ሙሉ በሙሉና ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ አዲስ
እኚህ ቃላት ለትክክለኛ አስተሳሰብ ተምሳሌቶችና ዘይቤዎች አይደሉም። ይልቁንም የልዕለ ተፈጥሮአዊ ውጤት ትክክለኛ አስተሳሰብን የሚያመለክቱ ናቸው። ማለትም መንፈሳዊ ስሜቶች ሲሆኑ የከበረ አድርጎ መያዝ፣ ታላቅ ዋጋ መስጠት፣ ፍስሓ ማድረግ፣ ማጣጣም፣ መርካት የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ የነፍስ ምግባሮች መሠረታቸው አዲስ መንፈሳዊ ማመዛዘን፣ መንፈሳዊ ስሜት እና መንፈሳዊ መረዳት ነው። ይህ አቅም ከዳግም ውልደት በፊት አይኖርም። በመንፈስ ቅዱስ የሚመጣ ነው።
አእምሮ አዲስ ዐይነት መረዳት ወይም ስሜትን ይይዛል። እዚህም ጋር የምንመለከተው አእምሮ የያዘውን አዲስ መንፈሳዊ ስሜት ነው። ይህም ከዚህ በፊት አእምሮ በውስጡ ይዞት ከሚያውቀው ማንኛውም ዐይነት ስሜት በሙሉ ባሕሪው የተለየ ነው። ሰዎች ማርን በማየት እና በመዳሰስ ብቻ ስለ ማር ጣፋጭነት የሚኖራቸው መረዳት የተለየ እንደሆነ ሁሉ መቅመስ ከሌሎች ስሜቶች በተለየበት መልኩ በእውነተኛ ቅዱሳን ያለ አንድ መንፈሳዊ እና መለኮታዊ መረዳት መንፈሳዊ ባልሆነ ሰው ካለ ማንኛውም ዐይነት መረዳት ፈጽሞ የተለየ ነው። (ገጽ 205 – 206)
ያለዚህ “አዲስ መንፈሳዊ የአእምሮ ስሜት” ድኅነት የለም። ዳግም መወለድ ማለት ይሄ ነው። እራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ከሚጠሩት ውስጥ ምን ያህሉ ይሆን በእግዚአብሔር ደስ የመሰኘት መንፈሳዊ አቅም የሌላቸው? ይህንን ልናውቅበት የምንችለው አንደኛው መንገድ የቤተክርስቲያን መጋቢዎች እና አስተማሪዎች በ1ጴጥሮስ 2፥2-3 ላይ “እንደ ሆነ” በሚለው ቅድመ ሁኔታ ላይ አጽንኦት በመስጠት ነው።
“ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።”
እያንዳንዱ መጋቢ “እንደ ሆነ” የምትለውን ቃል ክብደት ሰጥቶ ሊያሰላስላት ይገባል። ጴጥሮስ እያለ ያለው “ቀምሳችሁ ከሆነ” የቃሉን ወተት መጠጣት ወደ ድነት ይመራል ነው። ሰምታችሁ ከሆነ ወይም ዐውቃችሁ ከሆነ አሊያም ወስናችሁ ከሆነ አይደለም የሚለን። ይልቁንም ቀምሳችሁ ከሆነ ነው አጽንዖቱ።
ከዛሬ 60 ምናምን ዓመት በፊት ወደ ሕይወቴ ገብቶ አዲስን ሕይወት ስለ ሰጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ለስልሳ ዓመታት “የመለኮትን ምግባራዊ ውበት” ጣዕም በውስጤ ደግሞ ደጋግሞ ስላነቃቃ አመሰግነዋለሁ። ለእናንተም ይህን እንዲያደርግላችሁ ጸሎቴ ነው። “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ።”
በ ጆን ፓይፐር