ክርስቲያን ሆይ! ነገ ማለዳ ስትነቃ አማኝ ሆነህ ለመቀጠልህ ምን ዋስትና አለህ? እንዲሁም ኢየሱስን እስክትገናኘው ድረስ ባሉ ሁሉ ማለዳዎችስ?
መጽሐፍ ቅዱሳዊው መልስ ይህ ነው፦ እግዚአብሔር ያደርገዋል!
ይህ ነገር ይዋጥላችኋል? ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ላይ የተደገፈ መሆኑን መቀበል ዕረፍት ይነሳችኋል? ይህ ነገር ደስታችሁ እና መዝሙራችሁ ነው ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህንን ማመን በእውነቱ ትልቅ አንድምታ አለው። በዚህ ጉዳይ ላይ የእግዚአብሔር ቃል አእምሯችሁን ይቅረጽ።
መጽናት አለብን
“አለብን” የሚለው ቃል በራሱ፣ የወንጌል ቃል አይደለም። ቃሉ በራሱ የማስፈራራት እና የሸክም ስሜት አለው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻውን አልተቀመጠም። “አለብን” ከ”እርሱ ያደርገዋል” እና “አኛ እናደርጋለን” ከሚሉ ቃላት ጋር ተያይዞ መጥቷል። “አለብን” ወደ “እናደርጋለን” የተሸጋገረው “እግዚአብሔር ስለሚያደርግ” ነው።
እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል (ማርቆስ 13፥13)።
ብንጸና፣ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን። ብንክደው፣ እርሱ ደግሞ ይክደናል (2 ጢሞቴዎስ 2፥12)።
ወንድሞች ሆይ፤ … የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወድዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው (1 ቆሮንቶስ 15፥1-2)።
እግዚአብሔር ይጠብቃችኋል
በእምነት መጽናት፣ ልክ ጤንነት አንድ ጊዜ በሚወሰድ ክትባት እንደሚጠበቅ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረግነው የእምነት ምስክርነታችን ብቻ የሚሆን አይደለም። እምነት የሚጸናው ታላቁ ሐኪም የማጽኛ ሥራውን በየቀኑ ስለሚሠራ ነው። በክርስቶስ ማመናችንን የምንቀጥለው ከተለወጥንበት (conversion) ጊዜ በተራረፉ በሽታን በሚዋጉ ሕዋሳቶቻችን(antibodies) ሳይሆን፤ እግዚአብሔር ሕይወትን የሚሰጥ፣ እምነትን የሚጠብቅ ሥራውን በየቀኑ ስለሚሠራ ነው።
እንዳትወድቁ ሊጠብቃችሁና ያለ ነቀፋና በደስታ በክብሩ ፊት ሊያቀርባችሁ ለሚችለው። (ይሁዳ 1፥24)
በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ። (ፊልጵስዩስ 1፥6)
ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ። (ኤርምያስ 32፥40)
[ክርስቶስ] እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንቶ ይጠብቃችኋል። ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። (1ኛ ቆሮንቶስ 1፥8-9)
ጌታ … ወደ ሰማያዊው መንግሥቱም በሰላም ያደርሰኛል። (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥18)
እንጸናለን
እግዚአብሔር ስለሚያደርገው እስከ ፍጻሜው መጽናት አለብን ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻውም እንጸናለንም። በእምነት በኩል ከጸደቅን፣ እንከብራለንም። መክበራችን የተረጋገጠ ነው።
አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው። (ሮሜ 8፥30)
ለዚህ ዋስትና አራት ምላሾች
- ጣሉት
ራስን የመታደግ ቀንበርን አንስተን እንጥላለን። መፍጨርጭር አቁመን የነፍስ አድን ሠራተኛው ከሚነደው ቤት ውስጥ ተሸክሞ እንዲያወጣን እንፈቅዳለን። እኛ አንችልም። እርሱ ይችላል፤ ያደርጋልም። “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ (ኤርምያስ 10፥23)።”
- ሐሴት አድርጉ
ቻርልስ ስፐርጅን እንዲህ ብሎ ሲናገር ልባችሁ ይህንን ሐሴት መልሶ አያስተጋባምን? “ኦ ወዳጆቼ፣ እነዚያን የማይበገሩትን “ይሆናል” እና “አደርጋለሁ” ፣ እነዚያን ሞት እና ሲኦል ሊያንገዳግዷቸው ያልቻሉት የማይናወጡት ምሰሶዎች፣ እነዚያን የ“ይሁን አለ፣ ሆነም” አምላክ “ይሆናል” እና “አደርጋለሁ”ን ባሰበች ቁጥር የአንድ ሰው ልብ እንዴት ባለ ደስታ ትሞላለች። “የጠራችሁ የታመነ ነው፤ እርሱም ያደርገዋል” (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥24)።
- ዕረፉ
“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፥28)። ቀንበሩ ልዝብ፣ ሸክሙም ቀሊል የሆነበት ምክንያት፣ “እሸከማችኋለሁ፣ በእኔም ታርፋላችሁ” ብሎ እግዚአብሔር ስለ ተናገረ ነው። “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ” (ኢሳይያስ 46፥4)።
- ድፈሩ
የወደፊት ሕይወታችሁ ሁሉን ቻይ እና ጠባቂ በሆነው አምላካችሁ የተጠበቀ እንደሆነ ካወቃችሁ፣ የምድር እና የሲኦል ዛቻ ዝናውን ከማስፋፋት ሊያስቆሟችሁ አይችሉም። ጳውሎስ ከ “ያጸደቃቸውን አከበራቸው” የመዘዘው ድምዳሜ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል(ሮሜ 8፥31)?” የሚል ነበር። ስለዚህም ለ“ችግር፣ ሥቃይ፣ ስደት፣ ራብ፣ ዕራቍትነት፣ አደጋ፣ ሰይፍ (ሮሜ 8፥35)” ደረታችንን እንሰጣለን። ምክንያቱም ምንም ነገር በክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም (ሮሜ 8፥39)።