የክርስትናን አንድ ተግባር ትርጉሙን ግልጽ ልናደርግበት ከምንችላቸው መንገዶች ውስጥ አንደኛው ከዚህ ተግባር ውስጥ ምን ያህሉን ዲያቢሎስ ሊያደርገው እንደሚችል በማጤን ነው።
ለምሳሌ፣ የሚያድን እምነት መያዝ ምን ማለት እንደ ሆነ ያዕቆብ ሲያብራራ፣ “አንድ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህ፤ መልካም ነው፤ አጋንንትም ይህንኑ ያምናሉ፤ በፍርሀትም ይንቀጠቀጣሉ” (ያዕቆብ 2፥19)። በሌላ አገላለጽ፣ የሚያድን እምነት አጋንንት ካላቸው እምነት የላቀ መሆን አለበት። ስለዚህ ይህንን ልብ በማለት ማድረግ የሚችሉት ምን እንደ ሆነ አጢኑ። አጋንንት ሊያደርጉት ለሚችሉት ዐይነት የእምነት ትርጉም ወይም እነርሱ ያላቸው የእምነት ዐይነት ተመችቷችሁ አትቀመጡ።
“የዲያብሎስ መርሕ” አተረጓጎም
ለብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐውዶች ጠቃሚ የሆነ የትርጓሜ መርሕ በዚህ ውስጥ እናገኛለን። ይህም መርሕ የአንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ትርጉም ለመረዳት በምትጥሩበት ጊዜ፣ ከዚህ ትእዛዝ ውስጥ ምን ያህሉን ዲያቢሎስ ሊፈጽመው ይችላል ብላችሁ ጠይቁ። ከዚያም ዲያቢሎስ ሊያደርገው የሚችለውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ካስቀመጠው የላቀ ትእዛዝ ጋር እኩል አለማድረጋችሁን ርግጠኛ ሁኑ። ለአማኞች የተሰጠው እያንዳንዱ ክርስቲያናዊ ኀላፊነት፣ ዲያቢሎስ ሊያደርገው ከሚችለው የሚልቅ ኀላፊነት ነው። እምነታችን፣ መታዘዛችን፣ እና መፍራታችን ከሰይጣን እምነት፣ መታዘዝ እና መፍራት ሊበልጥ ይገባል።
በ 1ቆሮንቶስ 12፥3 ላይ ጳውሎስ፣ “በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር፣ ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚል እንደሌለ እነግራችኋለሁ” ይላል። ስለዚህ የዲያቢሎስን መርሕ እዚህ ጋር ስንተገብረው፣ በዓለም ሁሉ እና በአጋንንታዊው ዓለም ላይ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ ዲያብሎስ ምንም ጥርጣሬ እንደሌለው እናያለን። ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ ያውቃል። አጋንንቱም ይህንን ያውቃሉ።
በማቴዎስ 8፥29 ላይ አጋንንቱ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ” ደግሞም በማርቆስ 1፥24 ላይ ጋኔኑ ለኢየሱስ፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኛ ምን ትሻለህ? ልታጠፋን መጣህን? እኔ ማን እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ፤ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱስ ነህ!” ይለዋል። “የእግዚአብሔር ልጅ” እና “የእግዚአብሔር ቅዱስ” የሚሉት መጠሪያዎች የኢየሱስን ጌትነት የሚያመላክቱ ናቸው። “ልታሠቃየን” እና “ልታጠፋን” መጣህ በማለት ኢየሱስ ሊያደርገው የሚችለውን በመናገራቸው ውስጥ ነገሩ የበለጠ ግልጽ ሆኖ ይታያል። ከእርሱ ይልቅ ኢየሱስ ኀያል እንደ ሆነ ደግሞም ያሉት የነጻነት ቀናት ጥቂት እንደ ሆኑ ዲያብሎስ ያውቃል፣ ደግሞም ያምናል።
ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ ዲያብሎስ ያምናል
ስለዚህ ዲያብሎስ፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል እንደሚችል ግልጽ ነው። በርግጥም ደግሞ ይላል። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፥3 ላይ፣ “በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር፣ ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚል እንደሌለ እነግራችኋለሁ” የማለቱን ትርጉም ለመረዳት ጠቃሚ ነው። ዲያብሎስ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ማለት የሚችል ስለ ሆነ፣ ኢየሱስ ጌታ ነው የማለት ኀላፊነት ፈጽሞ ኀያል እንደ ሆነ ከማመን እና ከማወጅ የሚልቅ ነው። ዲያብሎስ ይህንን ያምናል እንዲሁም ያውጃል።
በሮሜ 10፥9 ላይ ተመሳሳይ ነገር ከጳውሎስ ንግግር እንመለከታለን። “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ።” ክርስቲያኖች ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ የሚመሰክሩ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣው ጭምር በልባቸው እንደሚያምኑ እንመለከታለን።
ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣ ዲያብሎስ ያምናል
እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው ዲያብሎስ ያምናል? አዎን ያምናል። ብዙ ኀይሉን የሚያጠፋው “የክርስቶስ የክብሩን ወንጌል ብርሃን” ሰዎች ማየት እንዳይችሉ ልቡናቸውን ለማሳወር ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4)። ይህም ክብር፣ በወንጌል ውስጥ የሚያበራው የተሰቀለው እና ከሞት የተነሣው የክርስቶስ ክብር ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሣው ዲያብሎስ ያውቃል።
ስለዚህ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ የመመስከር እና እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣው የማመን ኀላፊነት፣ ዲያብሎስ ከሚመሰክረው እና ከሚያምነው የሚልቅ ነገር መሆን አለበት። ዋና ሐሳቤ፣ “የዲያብሎስ መርሕ” ብዬ የጠራሁት ይህ መርሕ ጳውሎስ እያሰበ ወዳለው እውነታ ዘልቆ ለመግባት ጥሩ የትርጓሜ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል የሚል ነው።
የአጋንንት እምነት እና የሚያድን እምነት
ሮሜ 10፥9 ጥልቅ የሆነው እውነታ ምን እንደ ሆነ ፍንጭ ይሰጠናል፤ “እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ።” እውነት ነው፣ በአፍ መመስከር እና በልብ ማመን የሚሉት ሐሳቦች የተወሰዱት ከዘዳግም 30፥14 ነው። ይሁን እንጂ የጳውሎስ ሐሳብ ምንድን ነው? ጥያቄው ይህ ነው።
“በልብህ” በሚለው ቃል ውስጥ ጳውሎስ እያስተላለፈ ያለው መልእክት፣ ኢየሱስ በማዳኑ በእናንተ ላይ ጌታ እንዲሆን በሚፈቅድ መልኩ የእርሱን ጌትነት በደስታ ትመሰክራላችሁ ትንሣኤውንም በሐሴት ትይዙታላችሁ። ይህንንም ደግሞ ጳውሎስ በሮሜ 6፥17 ላይ፣ “በሙሉ ልብ የታዘዛችሁ በመሆናችሁ” በማለት ከተናገረው የምንረዳው ነው። ይህም በማጉረምረምና በቸልተኝነት ሳይሆን በደስታ መታዘዝ ማለት ነው። እንዲሁም ከልብ በደስታ የሆነ ነገርን ማድረግ፣ “በቅሬታ ወይም በግዴታ” የሆነን ነገር ከማድረግ ጋራ ያነጻጽረዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥7)። ዲያብሎስም ትንሣኤውን እና የኢየሱስን ጌትነት የሚቀበለው ልክ እንደዚህ በቅሬታ እና በግዴታ ነው።
ስለዚህ ወደ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፥3 እንመለስ፤ “በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር፣ ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው” የሚል እንደሌለ እነግራችኋለሁ።” ጳውሎስ እዚህ ጋር እያለ ያለው፣ ያለ መንፈስ ቅዱስ የለውጥ ሥራ፣ ማንም ኢየሱስን እንደ ከበረ ሀብቱ በማየት በደስታ እና በሐሴት፣ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ሊል አይችልም የሚል ነው። ዲያብሎስ የእግዚአብሔርን ኀይል ያምናል፤ እንዲሁም በመጨረሻ እግዚአብሔር ድል እንደሚያደርገው ያምናል። ይሁን እንጂ ይህንን እውነት እጅግ ይጠላዋል። ይህንን እውነት ልንወድደው የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። ክርስቲያኖችም ያደረገን ይህ እንጂ ዲያብሎስ የሚያምናቸውን ነገሮች ማመናችን ብቻ አይደለም።
በክርስቶስ መኖር
በቅርቡ በ2ኛ ዮሐንስ ላይ ባየኋቸው እነዚህ ቃላት ቆም እንድል ሆኛለሁ፤ “በክርስቶስ ትምህርት የማይኖርና ከትምህርቱ የሚወጣ ሁሉ አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት የሚኖር ግን አብም ወልድም አለው” (2ኛ ዮሐንስ 1፥9)። ይህ ነገር እጅግ በጣም ወሳኝ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። እግዚአብሔር የለንም ማለት ያለ እግዚአብሔር እንጠፋለን ማለት ነው።
ስለዚህ “በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ መኖር” ምን ማለት እንደ ሆነ አሰላሰልኩ። ዘላለማዊ ሕይወቴ በዚህ ላይ የተንጠለጠለ ነው። የማላደርገው ከሆነ እግዚአብሔር አይኖረኝም። የማደርገው ከሆነ ደግሞ አብም ወልድም ይኖሩኛል። ስለዚህ የዲያብሎስን መርሕ እዚህም ላይ በመተግበር፣ ዲያብሎስ በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ሊኖር የሚችለው በምን መልኩ ነው? ስል ጠየቅሁ። የአእምሮው ብቃት ላቅ ያለ ነው። የማስታወስ አቅሙ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ነው። የኢየሱስ ትምህርቶች ሁሉ ሲሰጡ በዚያ ነበር። ስለዚህ “በማስታወስ” እና እውነት እንደ ሆኑ “በማመን” ረገድ በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ እንደሚኖር አስባለሁ። ይህም ማለት፣ በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ ኑሩ ብሎ ዮሐንስ ሲናገር አስታውሱት እና እውነት እንደ ሆነ እመኑት ከማለት የበለጠ ነገር እየተናገረ ነው ማለት ነው።
ዲያብሎስ የኢየሱስን ትምህርት ሲያስታውስ እና እውነት እንደ ሆነ ሲያምን፣ ይጠላዋል። የክርስቶስን ትምህርት አይወደውም። በእርሱ ደስ አይሰኝበትም፣ እንደ ከበረ ነገርም አይቆጥረውም። ነገር ግን እንደ ኢየሱስ እና ዮሐንስ አስተሳሰብ፣ በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ መኖር ወይም የኢየሱስን ትምህርት መጠበቅ የሚመነጨው ኢየሱስን ከመውደድ ነው።
ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም (ዮሐንስ 14፥23-24)።
“የዲያብሎስን መርሕ” በመጠቀም በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ መኖር በተግባር እንዴት እንደ ሆነ የመመርመር ጉዞ ጀመርኩ። ዲያብሎስ ሊያደርገው ከሚችለው ነገር የበለጠ መሆን አለበት። በርግጥም ከዚያ የበለጠ ነው። ከሁሉም በላይ የምንወደው የእርሱ ትምህርት ስለ ሆነ ከእርሱ ጋር መጣበቅ፣ እንደ ከበረ ነገር መያዝ እና መታዘዝን ይጨምራል።
አስደንጋጭ ሕክምና ያስፈልጋል
ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ በሺዎች የሚቆጠሩ የስም ክርስቲያኖችን፣ “እምነታችሁ ከዲያብሎስ እምነት በምን የተለየ ነው? በክርስቶስ ትምህርት “መኖራችሁስ” ከዲያቢሎስ በምን ይለያል?” ብለው መጋቢዎቻቸው ቢጠይቋቸው በሚገባ እንደሚጠቅማቸው እምነቴ ነው። የስም ከርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን አማኝም የእኔ ጸሎት ዲያብሎስ ሊደግፈው ወይም ራሱ ሊያደርገው ከሚችለው ዐይነት ጸሎት (በርግጥም ዲያብሎስ እግዚአብሔርን አንዳንድ ነገሮች በሉቃስ 22፥31 ይጠይቃል) በምን የተለየ ነው ብሎ መጠየቁ መልካም ነው። የሰው ልጆች ስለ ምግብ እና ልብስ ደግሞም ስለ ጤና እና ሰላም እንዲሁም ስለ ስኬት እና በትምህርት ጥሩ የፈተና ውጤት ስለ ማግኘት እና የመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ቢጸልዩ ሰይጣን ምንም ችግር የለበትም።
በእነዚህ የጸሎት ዐይነቶች ሰይጣን የማይረበሽበት ምክንያት፣ ዳግም ካልተወለዱ ሰዎች ጋር የምንጋራቸው መሻቶች ስለ ሆኑ ነው። ምግብ እና ልብስ እንዲሁም ጤና እና ስኬት ለመፈለግ ዳግም መወለድ አያስፈልግም።
ይሁን እንጂ ዲያብሎስ፣ “ስምህ ይቀደስ” ብሎ መቼም አይጸልይም፤ ሌሎችም እንደዚያ ብለው እንዲጸልዩ አያግዛቸውም። ወይም “ጌታ ሆይ ስምህ እንዲከብር እና እንዲገንን፣ እንዲደነቅ እና እንዲፈራ አድርግ!” አይልም። ዲያብሎስ፣ “ጌታ ሆይ የሚያድነው መንግሥትህ የጨለማውን ኀይል ረትቶ እንዲሰፋ አድርግ” ብሎ አይጸልይም፤ ሌሎችም እንደዚያ ብለው እንዲጸልዩ አይጎተጉትም። “ስለ ኀጢአቴ ይቅር በለኝ፣ ኀጢአቴን እጠላዋለሁ ደግሞም እናዘዛለሁ። አባት ሆይ ይቅር እንድትለኝ በኢየሱስ ስም እለምንሃለሁ” ብሎ ዲያብሎስ መቼም አይጸልይም።
ስለዚህ በእምነት ጉዳይ ላይ፣ በክርስቶስ ትምህርት ውስጥ የመኖር ግዴታ ላይ፣ በጸሎት ሕይወታችን ላይ እና ሌሎች ብዙ ኀላፊነቶች ላይ የዲያብሎስ መርሕን አተረጓጎም መጠቀም መልካም ነው።
ያለዚህ ጥቂት አስደንጋጭ አገልግሎት ዓለማዊ ክርስቲያኖች እና የስም ክርስቲያኖች እምነታቸው፣ ለክርስቶስ ትምህርት ያላቸው ታዛዥነት፣ እንዲሁም ጸሎታቸው ከዲያብሎስ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን በጭራሽ ላያውቁ ይችላሉ።