በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውን?

በዮሐንስ አፈወርቅ (347-407 ዓ.ም.) ዘመን የነበሩ ሰዎች፣ በሮሜ 14፥23 “በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና” የሚለውን የጳውሎስን ቃላት ትርጉም ለመገደብ ሞክረዋል። ዮሐንስ አፈወርቅ ራሱም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በዚህ ክፍል ጳውሎስ ለመናገር የፈለገው በአውዱ ውስጥ ስለሚገኘው ሐሳብ እንጂ ስለ ሁሉም ነገር አይደለም።”

ሊኦን ሞሪስም ይህንን ገደብ ተከትሎ የሮሜ መልእክትን ባብራራበት መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦

“ጳውሎስ በዚህ ስፍራ አንድ ሰው አማኝ ከመሆኑ በፊት ስለሚያደርጋቸው ድርጊቶች ሳይሆን፣ አማኝ ከሆነ በኋላ በዕለት ተዕለት ምልልስ ውስጥ በእምነት ስለማያደርጋቸው ነገሮች ነው” ሲል ተናግሯል።

ሪቻርድ ሌንስኪ ግን አይደለም ይላል፤

ይህ ክፍል ስለ ክርስቲያን ወይም በእምነት ማዕቀፍ ውስጥ(adiaphora) ላሉት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ እንደሚሰፋ “የጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች መልእክት ትንታኔ” በሚለው መጽሐፉ ገልጿል።

እናንተስ ምን ታስባላችሁ?

ለመረዳት እንዲቀለን የሮሜ 14፥21-23 ዐውድ እንደሚከተለው ነው፦

ለወንድምህ መሰናክል ምክንያት የሚሆነውን ሥጋን አለመብላት፣ ወይንን አለመጠጣት፣ ወይም አንዳች ነገርን አለማድረግ መልካም ነው። እንግዲያስ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለህ እምነት በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የተጠበቀ ይሁን፤ ትክክል ነው ብሎ በተቀበለው ነገር ራሱን የማይኮንን የተባረከ ሰው ነው። ነገር ግን የሚጠራጠር ሰው ቢበላ በእምነት ስላልሆነ፣ ተፈርዶበታል፤ በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኅጢአት ነውና።

ሮሜ 14፥21-23

አውግስጢኖስ የዮሐንስ ወንጌልን ባስተማረበት ጊዜ፣ ሮሜ 14፥23 የሰውን ሁሉንም ድርጊቶች የሚመለከት ዓለም አቀፋዊ ሽፋን ያለው ጥቅስ እንደ ሆነ ተናግሯል (”የኒቂያ እና የድህረ ኒቂያ አባቶች፣ ቅጽ 7”)፦

“ጳውሎስ ‘በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና’ ሲል በክርስቶስ ከማመናችን በፊት መልካም ሥራ ስለምናደርግ ተመረጥን ማለቱ ሳይሆን፣ በክርስቶስ ከማመን የሚቀድም ምንም መልካም ነገር የለም ማለቱ ነው።”

ቶማስ ሽራይነር ከአውግስጢኖስ ጎን በመቆም፣ “ጳውሎስ በዐውዱ ውስጥ ስለተጠቀሰው ነገር(መብል) ብቻ እየተናገረ ቢሆን ኖሮ ‘የሚጠራጠር ሰው ቢበላ በእምነት ስላልሆነ፣ ተፈርዶበታል’ ብሎ ባቆመ ነበረ። ነገር ግን ጳውሎስ ‘በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና’ የሚለውን ሲጨምር፣ እየተናገረ ከነበረው ሐሳብ እንደሚሰፋ ለማሳየት እንደሆነ መረዳት እንችላለን” በማለት የሰፋ ሽፋን እንዳለው ተናግሯል።

የተፈለገውን ሐሳብ በአጠቃላይ እውነት ማሳየት

ሞሪስ፣ ጳውሎስ በሮሜ 14 ላይ በክርስቶስ ስላላመኑ ሰዎች ድርጊት አያወራም ብሏል፤ ሆኖም ግን ውሃ የማያነሳ ሙግት ነው። ምክንያቱም አጠቃላይ እውነትን በማሳየት ውስን እውነትን ማስገንዘብ የተለመደ መንገድ ነው።

ለምሳሌ እንዲህ ልንል እንችላለን፤ “እኛ ቤት ያለው ክብ የግድግዳ ሰዓት፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ ረጅሙ የሰዓት ጠቋሚ 3600 ይዞራል። ሁሉም ክብ የግድግዳ ሰዓት ውስጥ የሚገኘው ረጅም የሰዓት ጠቋሚ፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ 3600 ይዞራል።” ከእነዚህ ዐረፍተ ነገሮች  በመነሣት፣ “በአንድ ሰዓት ውስጥ ረጅሙ የሰዓት ጠቋሚ 3600 የሚዞረው የእኛ ቤት ብቻ ነው” ብንል ምክንያታዊ ያልሆነ ድምዳሜ ነው። ምክንያቱም “የእኛ ቤት ክብ የግድግዳ ሰዓት” ”በሁሉም ክብ የግድግዳ ሰዓቶች” ውስጥ ሊጠቃለል የሚችል ነው፤ ስለዚህ ልንገልጽ የፈለግነውን ውስን እውነት፣ አጠቃላይ እውነትን በማሳየት መደገፍ እንችላለን።

ጳውሎስም ያደረገው ይህንኑ ነው። “በእምነት ያልተደረገ ሁሉ ኀጢአት ነውና” የሚለው ሐሳብ አጠቃላይ እውነት ነው። ከሮሜ 14፥23 ውጪ ይህንን እውነት የሚያሳዩን በርካታ ክፍሎች አሉ። ለምሳሌ፦

  1. ጳውሎስ በሮሜ 4፥20 ላይ እምነት እግዚአብሔርን እንደሚያከብር ተናግሯል፤ “ይልቁንም በእምነቱ በመጽናት ለእግዚአብሔር ክብር ሰጠ።” እምነት የሌለባቸው ድርጊቶች ኀጢአት የሚሆኑበት ዋነኛ ምክንያት፣ እግዚአብሔርን በሚገባው መንገድ ስለማያከብሩ ነው።
  2. ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31 ላይ እንዲህ ብሏል፤ “እንግዲህ ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውም ነገር ስታደርጉ፣ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት።” ስለዚህ እግዚአብሔርን ባለማመን ውስጥ የሚደረግ የትኛውም ድርጊት፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31ን በቀጥታ መተላለፍ ነው።
  3. ዕብራውያን 11፥6 እንዲህ ይላል፤ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም።” ስለዚህ እምነት በሌለበት ሁሉ ድርጊቶቻችን እግዚአብሔርን አያስደስቱም።

መልካም ባሕርይ ኀጢአት ሲሆን

አውግስጢኖስ በክርስቶስ ያላመኑ ሰዎች ያላቸው መልካም ባሕርይ ሳይቀር ኀጢአት ነው ያለው ለዚህ ነው። ይህንን ሐሳብ በምሳሌ ግልጽ እናድርገው፤

የአንድ ታዳጊ ወጣት አባት ናችሁ እንበል። እናም ከጓደኞቹ ጋር እግር ኳስ ከመጫወቱ በፊት፣ ዘመድ ጋር ዕቃ እንዲያደርስላችሁ አዘዛችሁት። በነገራችሁት ጊዜ ተስማምቶ ነበር፤ ነገር ግን የመሄጃው ሰዓት ሲደርስ ያዘዛችሁትን ማድረግ እንደማይፈልግ ነገራችሁ። እናንተም ኳስ መጫወት የሚፈለግ ከሆነ ዕቃውን አድርሶ መምጣት እንዳለበት ትነግሩታላችሁ። እርሱም በንዴት ወጥቶ ዕቃውን አደረሰ፤ ነገር ግን ቢንያም ይህንን ያደረገው ለአባቱ ፍቅር ኖሮት ሳይሆን፣ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በመታዘዝ ሳይሆን ከጓደኞቹ ጋር መጫወት ስለሚፈልግ ነው። “መታዘዙን” ያስገደደው ለጨዋታው ያለው ፍቅር ነው። “መታዘዙን” የሚለውን በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት ውጫዊ ታዛዥነት ብቻ ስለ ሆነ ነው። ውስጣዊ የሆነ ታዛዥነት አላሳየም። የሰው ልጅ ለሰማዩ አባት ከልብ የመነጨ እና የእግዚአብሔር ፍቅር ከወለደው ታዛዥነት እስካልሆነ ድረስ፣ የትኛውም የሚያሳየው ባሕርይ የወደቀ ማንነቱ ነጸብራቅ ነው። የሚያደርገው ድርጊት ምንም ያኽል በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ልምምዶች የተሞላ ቢመስል፣ ከእምነት የሚመነጭ ስለማይሆን እግዚአብሔርን ደስ አያሰኝም።

በዋናነት ለእግዚአብሔር

የሰው ልብ ያለበትን ሁኔታ ከሰው ጋር ባለን ግንኙነት የምንለካ ከሆነ ምን ያህል አስከፊ ችግር ውስጥ እንዳለ አንረዳም። ቢንያም ዕቃውን ለዘመዶቻችሁ አድርሷል። ይሄ “መልካምነት” ነው፤ ዘመዶቻችሁም “ይጠቀማሉ።” ስለዚህ በድርጊቶቻችሁ ወስጥ የሚገኘውን ክፋት ሌሎች ሰዎችን በመጉዳት ወይም በመጥቀም ላይ ብቻ ተመሥርተን መረዳት አንችልም።

ሮሜ 14፥23 ችግራችን በመጀመሪያ ደረጃ ከእግዚአብሔር ጋር እንደ ተያያዘ በግልጽ ይነግረናል፤ ቀጥሎም ከሰዎች ጋር። ይህ የሚያሳየው የኀጢአታችንን ጥልቀትና የአዳኛችንን ታላቅነት ነው። ሰዎች ይህንን ተገንዝበው ምላሽ ሊሰጡ ይገባል።

ጆን ፓይፐር