እንደ በቅሎዋ አትሁኑ | ሚያዚያ 16

በልባብና በልጓም ካልተገሩ በቀር፣ ወደ አንተ እንደማይቀርቡት፣ ማስተዋል እንደሌላቸው፣ እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ። (መዝሙር 32፥9)

የእግዚአብሔርን ሕዝብ፣ ሁሉም ዓይነት እንስሳት ያሉበት የገበሬ እርሻ ግቢ አድርጋችሁ አስቡት። እግዚአብሔር እንስሳቱን ይንከባከባል፣ የት መሄድ እንዳለባቸው ያሳያቸዋል፣ ደግሞም ለደህንነታቸው ሲል በረት ያዘጋጅላቸዋል።

ነገር ግን በዚህ በረት ውስጥ እግዚአብሔርን የምታስቸግር በቅሎ የተባለች አንድ ባዕድ እንስሳ አለች። ምንም የማይገባት ሞኝ እና ግትር ስትሆን፣ ከሞኝነቷ እና ከግትርነቷ የትኛው እንደሚቀድም እንኳ ለመለየት ያዳግታል።

ታዲያ፣ እግዚአብሔር እንስሳቱን እንዲበሉና እንዲጠለሉ ወደ በረቱ ማስገባት የሚወደው የግል ስም እንዳላቸው ሁሉንም በማስተማርና ከዚያም አንድ በአንድ በስማቸው በመጥራት ነው። “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ” እንዳለው ማለት ነው (መዝሙር 32፥8)።

ነገር ግን በቅሎ ለዚህ ዓይነቱ መመሪያ ምላሽ አትሰጥም። ግንዛቤ የሚባል ነገርም የላትም። ስለዚህ እግዚአብሔር ወደ ሜዳ ይወጣና፣ ገመድና ልጓሙን በበቅሎዋ አፍ ውስጥ በመክተት ከመጫኛው ጋር ያያይዘዋል። ከዚያም እግሯን ጠፍንጋ እየደነፋች በረቱ ድረስ ይጎትታታል።  

እግዚአብሔር እንስሳቱ ለበረከትና ለጥበቃ ወደ እርሱ እንዲመጡ የሚፈልገው በዚህ መንገድ አይደለም።

አንድ ቀን ግን ለዚያች በቅሎ ይረፍድባታል። በበረዶ ትቀጠቀጣለች፤ ደግሞም በመብረቅ ትመታለች። እናም እየሮጠች ወደ በረቱ ስትመጣ በሩ ዝግ ይሆንባታል።

ስለዚህ፣ እንደ በቅሎ አትሁኑ። “በልባብና በልጓም ካልተገሩ በቀር፣ ወደ አንተ እንደማይቀርቡት፣ ማስተዋል እንደሌላቸው፣ እንደ ፈረስና እንደ በቅሎ አትሁኑ” ይላችኋል እግዚአብሔር።

ይልቁንም ጻድቅ የሆነ ሁሉ፣ እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ በጸሎት ወደ እርሱ ይምጣ። (መዝሙር 32፥6)

እንደ በቅሎ መሆን ማንፈልግ ከሆነ፣ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። ኃጢአታችንንም እንናዘዝ። ደግሞም እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዶሮ ጫጩቶች፣ ለእግዚአብሔር ምሪት በመታዘዝ ጥበቃውና መግቦቱ ወዳለበት በረት በደስታ እንግባ።