እግዚአብሔርን አታገልግሉት | ግንቦት 8

በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና። (2ኛ ዜና መዋዕል 16፥9)

እግዚአብሔር በምድር ላይ እየፈለገ ያለው ምንድን ነው? ረዳቶችን? አይደለም። የወንጌል ወይም የክርስትና ጥሪ የ “ረዳት ሰራተኛ እንፈልጋለን” ጥሪ አይደለም።

እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሠሩለትን ሰዎች ለቅጥር እየፈለገ አይደለም። “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና” (2ኛ ዜና መዋዕል 16፥9)። ታላቁ ሠራተኛ እርሱ ነው። መከራን መሸከም የሚችል ሰፊ ትከሻ ያለው እርሱ ነው። ጠንካራው እርሱ ነው። ይህንንም ሁልጊዜ ሊያሳየን ይፈልጋል። እግዚአብሔርን ከሌሎች አማልክት የሚለየው ነገር ይህ ነው፦ እርሱ ለእኛ ይሠራል። “ከጥንት ጀምሮ፣ በተስፋ ለሚጠባበቁት የሚደርስላቸው፣ እንደ አንተ ያለውን አምላክ ያየ ዐይን፣ ያደመጠ ጆሮ ፈጽሞ አልነበረም” (ኢሳይያስ 64፥4)።

ታዲያ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ምንድነው? እርሱ የሚፈልገው ይፈልጋል ብለን የምናስበውን ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ እስራኤላውያን ብዙ መሥዋዕት ይዘውለት መጥተው እንኳ ሲቆጣቸው እናያለን፦ “እኔ ግን ኰርማህን ከበረት፣ ፍየሎችንም ከጕረኖ የምፈልግ አይደለሁም፤ የዱር አራዊት ሁሉ፣ በሺሕ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና። … ብራብ ለአንተ አልነግርህም፤ ዓለምና በውስጧ ያለውም ሁሉ የእኔ ነውና” (መዝሙር 50፥9-1012)።

ታዲያ እግዚአብሔርን ሳናሳንሰው ልንሰጠው የምንችለው ነገር የለም ማለት ነው?

በእርግጥ አለ። የሚያስጨንቁንን ነገሮች፣ ፍላጎቶቻችንን፣ እንዲሁም ፈቃዱን ማድረግ እንችል ዘንድ ኀይልን እንዲሰጠን የጩኸት ልመናችንን ሁሉ ልንሰጠው እንችላለን።

ትዕዛዙም ይህ ነው፦ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” (1ኛ ጴጥሮስ 5፥7)። እግዚአብሔር የእርሱን በቂ መሆን እና እርሱን መደገፋችንን የሚያሳይን ምንም ነገር ብንሰጠው በደስታ ይቀበለናል።

ክርስትና በመሰረቱ ከበሽታ የማገገም ሕይወት ነው። በሽተኞች ሐኪሞቻቸውን አያገለግሉም። ነገር ግን በሚገባ እንዲያክሟቸው እምነት ይጥሉባቸዋል። የተራራው ስብከት የሐኪማችን አንድ አካል እንጂ፣ የአሠሪያችን የቅጥር ስምምነት አይደለም።

እንዲያውም ሕይወታችን የተንጠለጠለው ለእግዚአብሔር ባለመሥራት ላይ ነው። “አንድ ሰው ሥራ ከሠራ ደመወዙ እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ተገቢ ዋጋው ይቈጠርለታል። ነገር ግን ለማይሠራው፣ ኀጥኡን ሰው ጻድቅ በሚያደርግ በእግዚአብሔር ለሚያምን ሰው፣ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ 4፥4-5)።

ሠራተኞች የሰሩበትን ወይም የሚገባቸውን ደመወዝ ይከፈላቸዋል እንጂ ምንም ስጦታ አያገኙም። ስለዚህ፣ ጽድቅን እንደ ሥጦታ ለመቀበል የምንፈልግ ከሆነ፣ በሥራ ለማግኘት ከመጣር መቆጠብ አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ ሠራተኛው እግዚአብሔር ነው። የጸጋ ሰጪ በመሆኑ ደግሞ ከኛ የሚያገኘው ክብር እንጂ፣ የአገልግሎታችን ተጠቃሚነትን አይደለም።