ኢየሱስን ወድዶ መቀበል | ሚያዚያ 18

እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው። (1ኛ ዮሐንስ 5፥3–4)

እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ብቻ እንዳልሆነ አስተውሉ። እግዚአብሔርን መውደድ፣ “የእርሱን ትእዛዛት መጠበቅ ሸክም አይደለም” የሚል ልብ መኖር ጭምር ነው። ዮሐንስም እያለ ያለው ይህን ነው። ነገር ግን ይህን እውነት ከፍቅር ጋር ከማያያዝ ይልቅ ከዳግም ልደትና ከእምነት ጋር ያያይዘዋል። ከዚያም ቀጥሎ “ምክንያቱም” የሚልን ቃል በመጠቀም፣ የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሸክም የማይሆኑበት ምክንያት ይናገራል፦ “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል” ይላል። ስለዚህ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ያለ ሸክም መጠበቅ እንድንችል ዓለማዊ መሰናክሎችን የሚያሸንፈው ዳግም ልደት ነው ማለት ነው።

በመጨረሻም አክሎ፦ “ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው” ይላል። ስለዚህ፣ ዳግም ልደት እምነትን ስለሚወልድ፣ ከሸክም ነፃ ሆነን ትዕዛዝን እንድንጠብቅ ዓለማዊ መሰናክሎችን ያሸንፋል ማለት ነው። የአዲሱ ልደት ​​ተአምር፣ እግዚአብሔር ለእኛ በክርስቶስ በኩል የሆነውን ሁሉ፣ እጅግ የሚያረካ አድርጎ የሚቀበል እምነትን ይፈጥራል። ይህም እምነት ለእግዚአብሔር መታዘዝን ከዓለም ፈተናዎች ይልቅ የሚወደድ ያደርገዋል። እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ይህ ነው።

በ18ተኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው እውቁ ፓስተርና የስነ-መለኮት ምሁር ጆናታን ኤድዋርድስ፣ ይህን ጥቅስ ለመረዳት ባደረገው ጥናት እንዲህ ይላል፦ “የሚያድን እምነት የሚያመለክተው … ፍቅርን ነው … ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር፣ ትዕዛዛቱን እንዳንጠብቅ የሚያደርጉንን መሰናክሎች እንድናሸንፍ ያስችለናል። ይህም የሚያሳየው፣ ፍቅር በሚያድን እምነት ውስጥ ዋናው ነገር መሆኑና፣ እንዲያውም ታላቅ ውጤት የሚገኝበት ሕይወቱ እና ኀይሉ መሆኑን ጭምር ነው።”

ይህ አባባል ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ በርካታ ጥቅሶች ጆናታን ኤድዋርድስ የሚለውን ይደግፋሉ።

በሌላ አነጋገር፣ በክርስቶስ ማመን ማለት እግዚአብሔር ለእኛ በሆነልን ነገር መስማማት ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ በክርስቶስ በኩል ለእኛ የሆነውን ሁሉ ወድደንና ፈቅደን በደስታ መቀበል ማለት ነው። ጆናታን ኤድዋርድስ፣ “እውነተኛ እምነት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ክርስቶስ ለምስኪን ኃጢአተኞች ስለሆነው የተናገሩትን በሙሉ ወድዶ መቀበል ነው” ብሎ ተናግሯል። ይህ “ወድዶ መቀበል” ደግሞ ክርስቶስን — ከምንምና ከማንም በላይ የሚያስበልጠው — አንዱ የፍቅር ዓይነት ነው።

ስለዚህ፣ በአንድ በኩል፣ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ ያስችለናል በሚለው ሃሳብ እና (1ኛ ዮሐንስ 5፥3)፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ እምነታችን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዳንታዘዝ የሚያደርጉንን ዓለማዊ መሰናክሎች ያሸንፋል (ቁጥር 4) በሚለው ሃሳብ መካከል ምንም ዓይነት ተቃርኖ የለም ማለት ነው። ለእግዚአብሔር አብ እና ለክርስቶስ ያለ ፍቅር በእምነት ውስጥ የተካተተ ነው።

ከዚያም ዮሐንስ ታዛዥ ስለሆነው እምነት ሲናገር፣ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ የሚያምን” ሲል ይገልጸዋል (1ኛ ዮሐንስ 5፥5)። ይህ እምነት አሁን ያለውን ኢየሱስን፣ ክቡር መለኮታዊ አካል እንደሆነ፣ ደግሞም የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ “ወድዶ የሚቀበል” ነው። ይህ ማለት ግን “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ከሚለው እውነት ጋር መስማማት ማለት ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም አጋንንትም በዚያ ይስማማሉ። “እነርሱም ‘የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ፤ ከእኛ ምን ጕዳይ አለህ? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን?” እያሉ ጮኹ’ ይላል ማቴዎስ 8፥29። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማመን ማለት የእውነታውን አስፈላጊነት ደግሞም የእውነታውን ዋጋ “ወድዶ መቀበል” ማለት ነው። ይህም ማለት በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትና እግዚአብሔርም በእርሱ በኩል ለእኛ በሆነው ሁሉ መርካት ማለት ነው። 

“የእግዚአብሔር ልጅ” ማለት ኢየሱስ ከአባቱ አጠገብ በመሆን፣ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀው አካል ነው ማለት ነው። ስለዚህም፣ ያስተማረው ሁሉ እውነት ነው፤ የገባውም ቃል ሁሉ ጸንቶ ይቆማል፤ ነፍስንም የሚያረካው ታላቅነቱ በፍፁም አይለወጥም።

ታዲያ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማመን ይህን ሁሉ የራስ ማድረግ፣ በደስታ አምኖ መቀበል፣ በዚያም ደግሞ መርካትን ይጨምራል።