የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል። (ዕብራውያን 12፥2)
አንዳንድ ጊዜ እምነት የሚሠራው ሥራ ከባድና ሊነገር የማይቻል ነው።
Miracle on the River Kwai በተሰኘው መጽሐፉ ላይ፣ ኧርነስት ጎርደን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በበርማ ባቡር ጣቢያ ስለሚሰሩ የጦር እስረኞች ቡድን እውነተኛ ታሪክ ይናገራል።
“አለቆቹ በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ከእሰረኞቹ እጅ መሣሪያዎች ይሰበሰባሉ። ታዲያ አንድ ቀን አንዱ ጃፓናዊ ዘበኛ፣ “አካፋው የታል?” ብሎ በመጮህ ማን እንደወሰደው ለማወቅ ይጠይቃል። ማንም ይሁን ማን፣ ጥፋተኛ የሆነው ሰው ወደፊት እንዲመጣ እያዘዘ በብስጭትና በንዴት እንዳበደ ሰው መጮህ ይጀምራል። ማንም ግን አልተንቀሳቀሰም። እርሱም ጠመንጃውን አቀባብሎ ወደ እስረኞቹ አነጣጠረ። “ነው? ሁላችሁም ትሞታላችሁ! ሁላችሁም ትሞታላችሁ!” በማለት ጩኸቱን ግልጽ ወደሆነ ዛቻ ቀየረ። ሊተኩስ ጫፍ ላይ ሲደርስ፣ አንድ ሰው ወደ ፊት ወጣ፤ እናም ጸጥ ብሎ በቆመበት ጠባቂው በጠመንጃው ክፉኛ ቀጥቅጦ ገደለው። ወደ ካምፑ ሲመለሱ፣ መሳሪያዎቹ እንደገና ተቆጠሩ፤ የጠፋ አካፋ ግን አልነበረም።”
ያለጥፋታችን ለሌሎች ስንል እስከመሞት ድረስ የመጽናትን አቅም ከየት ልናገኝ እንችላለን? ኢየሱስ ለእኛ ባለው ፍቅር ጸንቶ የቀጠለው ‘በፊቱ ባለው ደስታ’ ላይ በማተኮር ነው። ወደፊት በሚመጣው የከበረ በረከት እና ደስታ ታመነ፤ ይህም በመከራው ውስጥ በፍቅር ጸንቶ እንዲቀጥል አስቻለው።
ዋጋ ለሚያስከፍል መታዘዝ አቅም የሚሆነንና የሚያበረታታን ብቸኛ ነገር በፊታችን ያለውን ደስታ ማሰብ ነው። ከዚያ መንገድ የተሻለ ሌላ አማራጭ እንዳለ ካሰብን፣ ወዮልን። በሉቃስ 14፥14 ላይ፣ በዚህ ሕይወት መስዋዕትነትን ስለሚጠይቀው መታዘዝ ሲናገር፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ግብዣ ባዘጋጀህ ጊዜ ድኾችን፣ አካለ ስንኩሎችን፣ ሽባዎችንና ዐይነ ስውሮችን ጥራ፤ ትባረካለህም። እነዚህ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ፣ በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል።” በሌላ አነጋገር፣ ለክርስቶስ ስትሉ ያጣችኋቸውን ነገሮች ሁሉ ስታስቡ፣ በፊታችሁ ያለውን ደስታ በመመልከት በርቱ።
ኢየሱስ ያለ አንዳች የአጸፋ ምላሽ መከራን በመቀበል፣ ልንከተለው የሚገባንን ምሳሌ እየተወልን እንደነበር ጴጥሮስ በመልዕክቱ ተናግሯል። በፊቱ ባለው ደስታ ላይ መተማመን ነበረው፣ እርግጠኛ ነበር። ጉዳዩን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጠ (1ኛ ጴጥሮስ 2፥21)፤ በበቀል ሒሳቡን ለማወራረድ አልሞከረም። ተስፋውን በትንሣኤው ላይ አኖረ። ከአባቱ ጋር በድጋሚ በመገናኘቱ፣ እንዲሁም ሕዝቡን በመቤዠቱ በሚያገኘው ደስታ ላይ ዓይኑን ተከለ። እኛም፣ እንደጌታችን፣ እንዲሁ ልናደርግ ይገባናል።